ያልተቋጨዉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድርና የዉጭ ጣልቃገብነት በሊቢያ | አፍሪቃ | DW | 11.01.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ያልተቋጨዉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድርና የዉጭ ጣልቃገብነት በሊቢያ

ሰሞኑን ኢትዮጵያና ግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በአዲስ አበባ ከተማ ለአራተኛና ለመጨረሻ ጊዜ ያደረጉት ድርድር ግብፅ ከአሁን ቀደም ያልቀረቡ አዳዲስ ሀሳቦችን በማንሳቷ ዉይይቱ ያለመቋጫ ተጠናቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:12

ትኩረት በአፍሪቃ

ኢትዮጵያና ግብፅ በአዲስ አበባ ከተማ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያካሄዱት ድርድር ለአራተኛ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደ በመሆኑ ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል ተስፋ የተጣለበት ነበረ።ሆኖም ግን በግብፅ በኩል ከአሁን ቀደም ያልቀረቡ አዳዲስ ሀሳቦች በመነሳታቸዉ ዉይይቱ ያለመቋጫ ተጠናቋል።

ግብፅ ካቀረበችዉ አዲስ የድርድር ሀሳብ መካከል የግድቡ ሙሌት ጊዜዉ  ከ12 ዓመት እስከ 21 ዓመት እንዲሆን መጠየቋ ነበር።በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ጊዜዉ ከ4 ዓመት እስከ 7 ዓመት ይሁን የሚል ሃሳብ አቅርባ ነበር።በድርቅ ጊዜ የውኃ አለቃቅ እና አሞላል ሂደቱ ምን ይምሰል የሚለው ጉዳይም ኢትዮጵያን እና ግብፅን ያላግባባ ሁለተኛዉ ጉዳይ ነበር። ሌላዉና ሶስተኛዉ የልዩነት ሀሳብ ደግሞ የድርቅ ብያኔ /definition/ ነበር። ግብፅ የውኃ መጠኑ «ከ40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በታች ሲሆን ድርቅ ነው »ተብሎ የተሻለ ውኃ ይለቀቅልኝ ስትል ኢትዮጵያ በበኩሏ የውኃ መጠኑ ከ35 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በታች ሲሆን«ድርቅ» የሚለው ብያኔ መሰጠት አለበት የሚል መከራከሪያ አንስታለች።

በከፍተኛ ድርቅ ወቅት የሚለቀቀዉ የዉሃ መጠንም ለሀገራቱ ሌላዉ አከራካሪ ጉዳይ ነበር።ኢትዮጵያ  እስከ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ይለቀቃል የሚል ሀሳብም ስታቀርብ። ግብፅ በበኩሏ ወደ 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ከፍ እንዲል ጠይቃለች።

ለድርድሩ አለመሳካት ኢትዮጵያ የግብፅ አቋም መሰናክል መፍጠሩን ብትገልፅም ግብፅ በኩሏ ኢትዮጵያን በመዉቀስ አንዱ በአንዱ ላይ ጣት ተቀሳስረዋል።

በጉዳዩ ላይ ዶቼ ቤለ ያነጋገራቸዉ በአባይ ተፋሰስ ሃገራት ትብብር በሆነው ናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት አቶ ተፈራ እንደሚሉት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በተከታታይ ባደረጓቸው ውይይቶች የሚያግባባ ደረጃ ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት አላቸዉ።

 የአባይ ጉዳይ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር የተያያዘ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ተፈራ፤ ሁሉም የተሻለ ጥቅም ለማግኘት የሚሄድበት አካሄድ እንዳለ ነገር ግን ይህ እንደማያዋጣ አመልክተዋል።

«አባይ የጋራ ሃብት ነው፤ ይህን የጋራ ሃብት ሦስቱም አገሮች በፍትሃዊነት ሊጠቀሙበት ይገባል። ይህ ሲደረግ የቆየው ጥረትም ምንም እንኳ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ምድር እና በኢትዮጵያ ወጪ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሃብት የሚገነባ ቢሆንም፤ ሃብቱ ከሚያጋጨው ይልቅ ተቻችሎ በጋራ ሃብቱ ለመጠቀም ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ይጠበቃል።» ነው ያሉት።

ከዚህ ውጪ «አንዱ በሌላው ላይ ጫና የሚያሳድርበት፤ ወይም አንዱ ተጠቃሚ ሌላው ደግሞ ተመልካች የሚሆንበት አሠራር ሊኖር አይገባም፤» እናም ሁሉም ይህን ይገነዘባሉ ብለዋል። የግድቡን ፕሮጀክት በተመለከተ ሱዳን እና ግብፅ ያላቸው አመለካከት ለየቅል መሆኑን ያነሱት አቶ ተፈራ፤ ለሱዳን ዋናው አሳሳቢው ጉዳይ ግድቡ ተገቢውን የጥራት እና ጥንካሬ ደረጃ ጠብቆ መገንባቱ መሆኑንም አንስተዋል።

በያዝነው ሳምንት በሦስቱ ሃገራት መካከል ለሁለት ቀናት አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው ውይይት፤ የሦስቱ ሀገራት መሪዎች ባለፈው ዓመት የካቲት ወር አዲስ አበባ ባካሄዱት ስብሰባ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው የቴክኒክ ምክክሮችን በማድረግ በህዳሴ ግድብ ሙሌት እና አለቃቀቅ ጉዳይ ላይ አማራጭ ሃሳቦችን እንዲያቀርቡ በሰጡት መመሪያ መሰረት የተከናወነ የመጨረሻው ስብሰባ ነበር።

በመጪው ሳምንት ዋሽንግተን ላይ በሚካሄደው የውሃ ሚኒስትሮቹ ስብሰባ እስካሁን የተደረጉ የቴክኒክ ምክክር ሂደት የሚገመገምበት ብቻ እንደሚሆን ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የተገኜዉ መረጃ ያሳያል።

ሊቢያ ፤ሀያላኑ የሚፋለሙባት የጦር ሜዳ
በነዳጅ ዘይት ሀብቷ የምትታወቀዉ ሰሜን አፍሪቃዊቷ ሀገር ሊቢያ በጎርጎሮሳዊዉ 2011 ዓ/ም በአመፅ ሀገሪቱን ለበርካታ አመታት ያስተዳደሯትን ሙአመር ጋዳፊን ከስልጣን ካወረደች ወዲህ ሰላም ርቋታል። ሀገሪቱ ትሪፖሊ በሚገኜዉ ህጋዊ መንግስትና በምስራቃዊ ትሪፖሊ በኩል በጀነራል ካሊፋ ሃፍታር በሚመራዉ የአማፂ ቡድን መካከል የርስበርስ ጦርነት ዉስጥ ገብታለች። የርስበርስ ጦርነቱ ከተከሰተ ወዲህም ሊቢያ የብዙ ዓለም ዓቀፍ ሀይሎች መፋለሚያ የጦር ሜዳ ሆናለች። ግብፅና የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች በጀነራል ከሊፋ ሀፍታር የአማፂ ቡድን በኩል ፤ቱርክና ኳታር በተባበሩት መንግስታት ዕዉቅና በተሰጠዉ በትሪፖሊዉ መንግስት በኩል ቆመዋል። 

10.2011 DW-AKADEMIE Medienentwicklung Afrika Libiyen Lage Vor Ort 3


በቅርቡም ቱርክ የትሪፖሊዉን የፋይዝ አስ ሲራጅ መንግስት ከአማጽያን እከላከላለሁ በሚል ወታደሮቿን ወደ ሊቢያ አዝምታለች። የቱርክን ወታደራዊ ጣልቃገብነት የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የእንግሊዝ ፣የፈረንሳይ፣ የጣሊያንና የጀርመን መንግስታት እንዲሁም የአዉሮፓ ህብረት ተቃዉመዉታል። 
የአዉሮፓ ህብረት የዉጭ ጉዳይ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦረል ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የሊቢያን ቀዉስ ያባብሳል ብለዋል።በዚህ የተነሳ በሀገሪቱ የተኩስ አቁም ስምምነትና የዉጭ ጣልቃ ገብነትን ህብረቱ መግታት ይፈልጋል በማለት ገልፀዋል።
« ማንኛዉም አባባሽ ሁኔታዎች  የውጭ ጣልቃገብነት ጨምሮ  ግጭቱን ይበልጥ እንዲባባስ ከማድረጉም በላይ ሊቢያ ዉስጥ ለሚገኙ ተራ ሰዎች የበለጠ ስቃይ  ያስከትላል ፣ በአገሪቱ ውስጥም የመከፋፈል አደጋ እንዲባባስና እንዲጨምር ያደርጋል።»
አማፂ ቡድኑ በቅርቡ 30 ሰዎች የተገደሉበትን የአየር ጥቃት በወታደራዊ አካዳሚ ፈፅሟል በሚል እየተወቀሰ ቢገኝም ቡድኑ ግን ወቀሳውን አልተቀበለዉም። የሁለቱ ሀይሎች ፍጥጫ የሀገሬዉን ሰዎች ህይወት ምስቅልቅሉን አዉጥቶታል።በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችም እንዲሁ።
በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ መሀል የመኖሪያ ህንፃዎች ወደፍርስራሽነት ተቀይረዋል።በነዚህ ግድግዳዎቻቸዉ በተሸነቋቆረና መስኮት በሌለባቸዉ ፍርስራሽ ህንፃዎች  170 የሚሆኑ ስደተኞችና ቤተሰቦቻቸዉ ይኖሩበታል። በስደት ሊቢያ የሚገኙት አቶ አብዱል ሃቲ በየቀኑ በዚህ ቦታ ያልፋሉ።  ሁኔታዉ ለዕርሳቸዉ ልብ የሚሰብር ነዉ።
«እዚህ የሚገኙ ሰዎችና  ህፃናት ልጆቻቸዉ ምቹና ሙቀት ያለበት ቦታ መኖር ሲገባቸዉ በዚህ ቦታ የተጎሳቆለ ኑሮን ለመቋቋም ተገደዋል።»
የጀነራል ካሊፋ ሃፍታር ጦር ትሪፖሊን ማጥቃት ከጀመረ ካለፈዉ ሚያዚያ ወዲህ  140 ሺ ሊቢያዉያን ጦርነቱን ሸሽተዉ ተሰደዋል። ከነዚህም መካከል ሰሚራ አሊ አንዷ ነች።ሁኔታዉን በጣም አሳዛኝ ነዉ ትላለች።


»ሚሳይሎች ቤቶቻችንን አወደሙ። መስኮቶቻቸዉንም ሰበሩ።ይህ በጣም አሳዣኝ ነዉ። የአካባቢዉ ሰዎች ሁሉም ተሰደዋል። በአጠገባችን ሮኬት ሲወረወር የልብ በሽተኛዉ ወንድ ልጄ አለቀሰና ራሱን ሳተ።»
ጀነራል ሃፍታር በግብፅና በተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች በመደገፍ ትሪፖሊን ለመያዝ እየተቃረቡ ሲሆን ። ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ የሩሲያ ወታደሮች በሌላ ወገን ተሰልፈዋል። በኳታርና በቱርክ የሚደገፈዉ የትሪፖሊዉ የፋይዝ አስ ሲራጅ መንግስት በልላ በኩል ይፋለማሉ።በሊቢያ የቱርክ ሰዉ አልባ አዎሮፕላኖች ባለፈዉ ህዳር ቢያንስ 200 ጥቃቶችን ፈጽመዋል። በቅርቡም ወታደሮቿ ገብተዋል።በዚህ የተነሳ የሊቢያ ጦርነት የርስበርስ መሆኑ ቀርቶ ዓለማቀፋዊ ይዘት እየያዘ መጥቷል።የሀገሬዉ ዜጎችና የስደተኞች ስቃይና መከራም በዚያዉ ልክ ጨምሯል። ሊቢያ ሁለተኛዋ ሶርያ እንዳትሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዲፕሎማሲዊ ጥረቶች እየተጨመሩ ቢመጡም ብዙም ተስፋ ሰጪ ዉጤቶች ያላቸዉ አይመስሉም። በሊቢያ መንግሥት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመዉ « የበርሊን ፕሮሰስ » የተሰኜ የትብብር ማዕቀፍ ከመስከረም ወር ጀምሮ በችግሩ ላይ ሲሰራ ቆይቷል።ትብብሩ በበርሊን ጀርመን በተያዘዉ ወር በሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች መካከል ዉይይት ለማካሄድ አቅዷል።  የሊቢያ የሀገር ዉስጥ ሚንስትር ፋቲ ባሻሃጋ ግን በድርድሩ ተስፋ የቆረጡ ይመስላል።


«ዉይይቱን ማካሄድ በጣም አስቸጋሪ ነዉ።ሀፍታር የተባለዉ ሰዉ የሚቀበለዉ አይመስለኝም።ምክንያቱም ስልጣንን በሀይል መዉሰድ ስለሚፈልግ እሱ የሚያዉቀዉ ጥቃትና ግጭት ብቻ ነዉ።»በዚህ መሰሉ የሀያሉ ፍጥጫ መሀል ግን ሰሚራ አሊን የመሳሰሉ ንፁሃን ዜጎች ከህፃናት ልጆቻቸዉ ጋር የችግሩ ገፈት ቀማሽ እየሆኑ ነዉ።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic