ያልሰመረው የሊቨርፑል የ24 ዓመታት ህልም | ስፖርት | DW | 12.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ያልሰመረው የሊቨርፑል የ24 ዓመታት ህልም

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዘንድሮ እንደ ሊቨርፑል ልቡ የተሰበረ ቡድን የለም። 24 ዓመታት ጠብቀውም ዋንጫ የመጨበጥ ህልማቸው እንደ ጉም በኗል። ማንቸስተር ሲቲ በሦስት ተከታታይ የጨዋታ ዘመን ለ2ኛ ጊዜ ዋንጫውን ማን ደፍሮ ከእጄ ሊነጥቅ ብሏል። የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች፣ የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ፣ የስፔን ላሊጋና የጣሊያን ሴሪኣ ቅኝት ተደርጎባቸዋል።

በፕራግ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 6ኛ ድረስ ተከታትለው በመግባት ዓለምን አስደምመዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ከ24 ዓመታት በኋላ ዋንጫ የመጨበጥ ህልሙ መክኗል። ክሊችኮ የቡጢ ጓንቱን ለወንድሙ አደራ ሰጥቶ በዩክሬን ፖለቲካ ሲጠመድ፤ ካናዳዊው ቡጢኛ የዓለም ከባድ ሚዛን ቀበቶ ባለድል ለመሆን በቅቷል። ኢትዮጵያውያት አትሌቶች በፕራግ ማራቶን ድል በድል ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ቡድን ሀገር ቤት በደቡብ አፍሪቃ ድል ተነስቷል። የሜዳ ቴኒስና የመኪና ሽቅድምድም ውጤቶችን የሚቃኙ ዜናዎችንም አካተናል።

ሊቨርፑሎች ልክ ከዛሬ አንድ ወር በፊት ማንቸስተር ሲቲን በሜዳቸው አንፊልድ ላይ 3 ለ 2 ሲረቱ ዋንጫ የመጨበጥ የ24 ዓመታት ህልማቸው ዕውን መሆኑ የማይቀር መስሎ ነበር። በ15ኛው ቀን ግን አንድ ሰው ጉድ አደረጋቸው። ይህ ሰው በሊቨርፑል የ14 ዓመታት ቆይታው የቡድኑ የቁርጥ ቀን ልጅ በመባል ይታወቃል። ቡድኑ የዋንጫ ባለቤት እንዲሆን ከማንም በላይ ለዓመታት ላቡን ጠብ አድርጎ ታግሏል። ወሳኙ ቀን ሲደርስና የመጨረሻዎቹ ቀናት ሲቃረቡ ግን የዕድል ነገር ሆነና የቡድኑን ዕጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ተጫዋችም ሆነ። ሽቴቫን ጄራርድ።

የሊቨርፑሉ ሽቴቫን ጄራርድ

የሊቨርፑሉ ሽቴቫን ጄራርድ

ሊቨርፑል በደጋፊው ፊት፤ አንፊልድ ሜዳ ላይ በቸልሲ 2 ለባዶ በተሸነፈበት ወሳኝ ጨዋታ የመጀመሪያዋን ግብ ዴምባ ባ ከመረብ ያሳረፈው፤ ልውስውስ ኳስ ከጄራርድ እግር ሾልካ ከደረሰችው በኋላ ነበር። ጄራርድ ከመሀል ተከላካዩ የፓሪሱ ወጣት ማማዶ ሣካሆ የተላከለትን ቀላል ኳስ በቅጡ መቆጣጠር ተስኖት ሲብረከረክ ፈጣኑ ዴምባ ባ በቀላሉ ከመረብ ሊያሳርፋት ችሏል። መቼም ሊቨርፑሎች ጄራርድን የተረገመ አይሉት ነገር ለዓመታት የቁርጥ ቀን ልጃቸው ሆኖ ክፉ ደጉን እያየ አብሯቸው ዘልቋል።

ለሊቨርፑል የከፋው ነገር የተከሰተው ግን ክሪስታል ፓላስን 3 ለባዶ እየመሩ የማታ ማታ እኩል ለእኩል በመውጣት ነጥብ የመጣላቸው ነገር ነበር። እናም ከእዛች ምሽት በኋላ የሊቨርፑሎች ከ24 ዓመታት በኋላ ዋንጫ የመጨበጥ ተስፋ በመጨረሻው ጨዋታ ውጤት ላይ ብቻ የተመሰረተ ሆነ። በመጨረሻው ጨዋታ ኒውካስልን አሸንፈው ማንቸስተር ሲቲ እንዲሸነፍ መፀለይ ነበረባቸው። የመጀመሪያው ተሳካ። ሊቨርፑሎች ኒውካስልን 2 ለ1 አሸነፉ። ሁለተኛው ፀሎታቸው ግን አልሰመረም። ማንቸስተር ሲቲ ዌስትሐምን 2 ለዜሮ አሰናብቶ «የእርግብ አሞራ» እያለ ወደ ማንቸስተር ከተማ ገሰገሰ።

ማንቸስተር ሲቲ

ማንቸስተር ሲቲ

የሊቨርፑሉ የቁርጥ ቀን ልጅ የ33 ዓመቱ አማካይ ሽቴፋን ጄራርድም ሆነ የቡድኑ ዋንጫ የመጨበጥ የ24 ዓመታት ህልም እንደ በጋ ጉም ዐየር ላይ ባክኖ ቀረ። ማንቸስተር ሲቲም «የነብርን ጅራት…»እንዲሉ በሦስት ተከታታታይ ዓመታት ውስጥ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የእንግሊዝ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ማን ጀግና ሊያስጥለኝ ብሏል። ሊቨርፑሎች ከዋንጫ ባለቤቱ ማንቸስተር ሲቲ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብለው 84 ነጥብ በመሰብሰብ ፕሬሚየር ሊጉን በሁለተኛነት አጠናቀዋል። ቸልሲ 82 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ፣ አርሰናል በ79 ነጥብ አራተኛ ወጥተዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ የቀድሞ ግርማ ሞገሱን አጥቶ በ64 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተወስኗል።

ኖርዊች ሲቲ፣ ካርዲፍና ፉልሐም ከፕሬሚየር ሊጉ ወራጅ ሆነዋል። በተለይ ፉልሐም ከ13 ዓመታት የፕሬሚየር ሊግ ቆይታው በኌላ ወራጅ መሆኑ የቡድኑን ደጋፊዎች ልብ ሳያደማ አይቀርም። ሦስቱ ወራጅ ቡድኖችን የሚተኩ ሁለት ቡድኖች ታውቀዋል። ላይስተር ሲቲ እና በርንሌይ ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ብቅ ይላሉ። ከእነዊጋን፣ ደርቢኮንቲ፣ ኪው ፒ አርና እንዲሁም ብሪንግቶን ሆቭ አልቢዮን አሸናፊው ሦስተኛው ወደ ፕሬሚየር ሊግ የሚቀላቀል ቡድን ይሆናል።

የሐምቡርግ ተጫዋቾች

የሐምቡርግ ተጫዋቾች

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋም ፓዴርቦን የተሰኘ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቡንደስ ሊጋው ማለፍ ችሏል። ፓዴርቦን ማለፉ እንደተረጋገጠ ፓዴርቦን ከተማ ብቻ ሳትሆን መላው የፓዴርቦን አውራጃ በፌሽታ ተውጦ ማምሸቱ ታውቋል። የ24 ዓመቱ ክሮሺያዊ የፓዴርቦን አማካይ ማሪዮ ቭራንቺክ ቡድኑ ማለፉ እንደታወቀ ደስታውን በእዚህ መልኩ ነው የገለጠው፦

«ለመግለፅ ያዳግታል፤ የተሰማኝን መግለፅ አልችልም። ጠንክረን ነው የሰራነው። አሁን ከፓዴቦርን ነዋሪዎች ጋር መፈንጠዝ ነው። ከእዚህ በላይ ደስታ የለም። ታሪክ ሰርተናል»

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የወራጅ ቀጠና ውስጥ የነበሩት ኑርንበርግና ብራውንሽቫይግ ላለመውረድ የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ነበረባቸው። ሆኖም ኑረንበርግ ከትናንት በስትያ በሻልካ 4 ለዜሮ እንዲሁም ቀደም ሲል 2 ለባዶ በመሸነፉ ቡንደስሊጋውን ተሰናብቷል። አይንትራኅት ብራውንሽቫይግም በሆፈንሐይም 3ለ 1 እና አንድ ለምንም በመረታቱ ኑረንበርግን ተክትሎ ከቡንደስሊጋው ወርዷል።

ሐምቡርግ በማይንስ ከትናንት በስትያ 3 ለ 2 ቢሸነፍም ከእዚህ ቀደም አንድ እኩል በመውጣቱ በመውረድና ባለመውረድ አጣብቂኝ ውስጥ ነው የሚገኘው። እናም የሐምቡርግ ዕጣ ከቡንደስ ሊጋው በታች ስቫይተ ሊጋ ውስጥ ሦስተኛ ከሚወጣው ቡድን ጋር የፊታችን ሐሙስ እና እሁድ በሚያደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ይወስናል። የሀምቡርጉ አሰልጣን ሚርኮ ስሎምካ የማይንሱን ጨዋታ መሸነፍ አልነበረብንም ይላሉ በቁጭት። ምክንያቱም፥

የፓዴርቦርን ተጨዋች መሬት ላይ ተዘርግቶ

የፓዴርቦርን ተጨዋች መሬት ላይ ተዘርግቶ

«ምክንያቱም የመጀመሪያውን አጋማሽ ጥሩ ተጫውተን ነበር። ጥሩ ዕድሎችም ነበሩን። ጨዋታችን ድንቅ የሚባል ቢሆንም ልንጠቀምበት አልቻልንም። በሌላ መልኩ ሲታይ ደግሞ የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ተዳክመናል። ተጨዋቾቹ የልፋታቸውን ቢያገኙ ደስ ይል ነበር። ለእዚያ እንግዲህ ከሐሙስ ጀምሮ መበርታት ነው። »

የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ የውድድር ዘመን ሳይጠናቀቅ ገና በጊዜ የዋንጫው ባለቤት መሆኑን ያረጋገጠው ኃያሉ ባየር ሙንሽን ሽቱትጋርትን ከትናንት በስትያ 1 ለዜሮ አሸንፏል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሔርታ ቤርሊንን 4 ለዜሮ አንኮታኩቶ በቡንደስ ሊጋው ሁለተኛነቱን አስጠብቋል። ሦስተኛው ሻልካ ወራጁ ኑረንበርግን ከትናንት በስትያ 4 ለአንድ ረትቷል። በቡንደስ ሊጋው አራተኛ በመሆን ያጠናቀቀው ባየር ሌቨርኩሰን ቬርደር ብሬመንን 2 ለ1 አሸንፎ የሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ተፎካካሪነቱን አስጠብቋል።

አትሌቲኮ ምድሪድ፤ የዋንጫ ግስጋሴ

አትሌቲኮ ምድሪድ፤ የዋንጫ ግስጋሴ

በስፔን ላሊጋ የመሪው አትሌቲኮ ማድሪድና የባርሴሎና ግጥሚያ ቅዳሜ ማታ ይጠበቃል። 89 ነጥብ ሰብስቦ ላሊጋውን የሚመራው አትሌቲኮ ማድሪድ የዋንጫው ባለቤት ለመሆን በሦስት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ከሚከተለው ባርሴሎና ጋር አቻ መውጣት ብቻ ይበቃዋል። ካታሎኒያ ውስጥ በሜዳው ካምፕ ኑ የሚጫወተው ባርሴሎና ግን ማሸነፍ ይጠበቅበታል፤ ምናልባት በደጋፊ ፊት መጫወቱ ይረዳው ይሆናል። አትሌቲኮ ማድሪዶች ግን ከ18 ዓመታት በኋላ በስፔን ላሊጋ የመጀመሪያቸው ሊሆን የሚችለውን የዋንጫ ባለቤት የመሆን ድል በዋዛ የሚለቁ አይመስልም። 24 ዓመታት ጠብቆ ድንገት ጉድ የሆነውን ሊቨርፑልን ለተመለከተ ግን የኳስ ነገር ብሎ የሚያልፈው ነው የሚመስለን።

የዘረኝነት ድርጊቶች በተደጋገሙበት የጣሊያን ሴሪኣ፤ 99 ነጥቦችን መሰብሰብ የቻለው መሪው ጁቬንቱስ ትናንት ሮማን 1 ለ ዜሮ በማሰናበት በሴሪ ኣው አዲስ ታሪክ ሰርቷል። ጁቬንቱስ በኢንተር ሚላን ተይዞ የነበረውን የነጥብ ክብርወሰን በመስበር 99 ማድረስ ችሏል። በደረጃ ሰንጠረዡ ሮማ 85 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ሲሆን፤ ናፖሊ በ75 ነጥቦች ሦስተኛ ነው። ኢንተር ሚላን ከፊዮሬንቲና በአራት ነጥብ ዝቅ ብሎ 60 ነጥቦች ላይ ተወስኗል።

ኤስ ሚላን በአታላንታ 2 ለአንድ በተሸነፈበት የትናንትናው ጨዋታ ዳግም የዘረኝነት ድርጊት ተከስቷል። የኤስሚላኑ ተከላካይ ኬቪን ኮንስታንት ላይ ሙዝ ተወርውሮበታል። ኬቪን የፈረንሣይ ዜግነት ያለው ትውልደ ጊኒያዊ ተጨዋች ነው። ከሁለት ሣምንት በፊትም በተመሳሳይ የባርሴሎናው ጥቁር ተጫዋች ዳኒ አልቬስ ከተመልካቾች የተወረወረበትን ሙዝ አንስቶ መብላቱ ይታወሳል። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ማኅበር FIFAፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር የጣልያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተመልካቾች የሚፈፀሙትን የዘረኝነት ድርጊቶች በተመለከተ አንዳች ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ዛሬ ጠይቀዋል።

የFIFAፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር

የFIFAፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያት ሯጮች ቼክ ሪፐብሊክ መዲና ፕራግ ውስጥ ትናንትበተካሄደው ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር ከ1ኛ እስከ 6ኛ ድረስ ተከታትለው በመግባት ድል መቀዳጀታቸውን ትናንት ዘግበናል። በፕራጉ የማራቶን ሩጫ ውድድር ፍሬህይወት ዳዶ በ 2:23:34 በመግባት አንደኛ ስትወጣ፤ ፋንቱ ኢቲቻ፣ እሸቴ በክረ፣ ፀሐይ ደሳለኝ፣ ሹኮ ገኔሞ እና ቆንጂት ጥላሁን ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ተከታትለው በመግባት በዓለም መድረክ አይበገሬነታቸውን አሳይተዋል። በፕራጉ ዓለምአቀፍ ማራቶን የወንዶች የሩጫ ፉክክር ኬኒያዊው ፓትሪክ ኪፕየጎን በ 2:08:07 በማጠናቀቅ አንደኛ ሲወጣ፤ የሀገሩ ልጅ ኤቫንስ ንያሳንጎ በሁለተኛነት ተከትሎ ገብቷል። የዚምቧብዌው ኩትበርት ማንዛ ሦስተኛ በወጣበት በእዚሁ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አበበ ካሳው እና አስማረ ወርቅነህ በ8ኛ እና በ10ኛ ደረጃ አጠናቀዋል።

ስድስት ኢትዮጵያውያት ሯጮችተከታትለው በመግባት ፕራግ ላይ ሲያሸንፉ፤ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ በደቡብ አፍሪቃ አቻው 2 ለባዶ መሸነፉም ተዘግቧል።

ቡጢ

በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ካናዳዊው ቤርማን ስቲቨርን በስድስተኛው ዙር ክሪስ አሬዎላን ሁለት ጊዜ በማብረክረክ በዳኛ ውሳኔ ማሸነፍ ችሏል። የ35 ዓመቱ ካናዳዊ ቡጢኛ የአሬዎላን ግንባር በቀኝ እጁ በምታት ነው አንገዳግዶ በመጣል ያሸነፈው። ክሊችኮ በዩክሬይን ፖለቲካ ተጠምዶ የቡጢ ጓንቱን በሰቀለበት በእዚህ ዓመት ግጥሚያ ካናዳዊው ከ5 ዓመታት በኋላ በአሜሪካን ምድር የዓለም ከባድ ሚዛን ቡጢን በማሸነፍ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል። ቭላድሚርና ቪታሊ ክሊችኮ የተባሉት ወንድማማቾች የከባድ ሚዛን ባለድል ሆነው ለስድስት ዓመታት ለብቻቸው መዝለቃቸው ይታወቃል።

ራፋኤል ናድል

ራፋኤል ናድል

ቴኒስ

ዝነኛው የሜዳ ቴኒስ ባለድል ስፔናዊው ራፋኤል ናድል ትናንት የማድሪድ ውድድሩን ለአራተኛ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። ራፋኤል ተፎካካሪው ካይ ኒሺኮሪን 6 ለ4 እና 3 ለዜሮ ነው ያሸነፈው። ቀደም ብሎ በሴቶች የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ማሪያ ሻራፖቫ ሲሞና ሀሌፕን 6 ለ 2 እና 6 ለ3 አሸንፋለች።

የመኪና ሽቅድምድም

የፎርሙላ አንድ ተፎካካሪ የመርሴዲስ አሽከርካሪዎቹ ሌዊስ ሐሚልተን እና ኒኮ ሮዝበርግ በስፔን ግራንድ ፕሪክስ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት ለአራተኛ ጊዜ በተከታታይ ማሸነፍ ችለዋል። የፌራሪው አሽከርካሪ ስፔናዊው ፈርናንዶ አሎንሶ ሦስተኛ ወጥቷል። በሬድ ቡል የውድድር መኪናው የሚታወቀው ጀርመናዊው ሰባስቲያን ቬትል በአራተኛነት አጠናቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic