ያላቆመው የአፍሪቃውያን ስደት | ወጣቶች | DW | 22.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ያላቆመው የአፍሪቃውያን ስደት

በህገ ወጥ መንገድ ከአፍሪቃ ወደ አውሮፓ እንሰደዳለን ብለው አሁን ድረስ በሊቢያ እስር ቤቶች የሚማቅቁ አሉ። ሌሎች ደግሞ በረሃ እና ባህር አቋርጠው አውሮጳ ለመግባት ሲሉ ህይወታቸውን አጥተዋል። ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ በየጊዜዉ ቢነገርም ሰዎች ግን አሁን ድረስ ይሰደዳሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00

ያላቆመው የአፍሪቃውያን ስደት

የናይጄሪያ ኤዶ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ቤኒን ሲቲ በሰዎች ህገ ወጥ ዝውውር ማዕከልነት ትታወቃለች። ወደ ሊቢያ ሊሰደድ ያሰበ ናይጄሪያዊ በዚህ ከተማ በቀላሉ ደላላ ያገኛል። የዶይቸ ቬለዋ ኤዲት ኪማኒ ወደዚህ ስፍራ ተጉዟ ለምን ብዙዎች መሰደዱን እንደሚመርጡ ጠይቃለች። « እዚህ ቢኒን ሲቲ ውስጥ ባደረኩት ክትትል ለመረዳት የቻልኩት በ 1980ዎቹ በርካታ ሴቶች ጣሊያን ሀገር የቲማቲም እርሻ ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር ነው። እነሱም ሴተኛ አዳሪ ሆነው ቢሰሩ ከሚከፈላቸው ገንዘብ የበለጠ ማግኘት እንደሚችሉ በመረዳታቸው ወደዚህ ስራ ተሰማርተዋል። ኋላም ወደ ቤኒን ሲቲ መጥተው ሌሎች ሴቶችን ይህንን በማስተማር ገንዘብ ያገኙ ነበር።  ይህም የህገ ወጥ ዝውውርን ፣ የወሲብ ንግድን የመሳሰሉትን ፈጥሯል። ይሁንና መንግሥት ጉዳዩን በቅርብ ይከታተላል። ይሁንና ሰዎች እዚህ መኖር እንዲችሉ ኢኮኖሚው በቂ ያልሆነበት ምክንያት ግልፅ አይደለም። » ትላለች ኤዲት። 
በርግጥ ቤኒን ሲቲ ለመኖር አመቺ አይደለችም ወይስ ሀገሪቷን ለቀው የሚሄዱት ሰዎች ናቸው ገፅታዋን መጥፎ ያደረጓት? ኤዲት የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን ጠይቃለች።

« በዚህ ከተማ ያለው ትልቁ ችግር፣ የወጣቶች ተቋማት ለወጣቶች አይደለም የተሰጡት። ወጣቱ መብቱን መገንዘብ  አልቻለም። ምክንያቱም ስግብግብ ስለሆኑ እድሉን አይሰጡም። ምንም ዋስትና የለም። ከባንክ እንኳን ብድር መጠየቅ አልችልም።»
«ጣታችንን ወደ መንግሥት መጠቆም ማቆም ያለብን ይመስለኛል። አንዳንዶቻችን መንግሥት መጥፎ ነው እንላለን። ነገር ግን አንዳንዶች ስልጣኑን ቢያገኙ ያንኑ ነገር የበለጠ መጥፎ እንደሚያደርጉት አምናለሁ። ማህበረሰባዊ ለውጥ የሚገኘው በተናጥል እና ማህበረሰቡን በማበረታታት ነው። ስለዚህ ራሳችን ወጣቶቹ የተሻለ ነገር ለማድረግ ከተበረታታን በመሪዎቹ ቦታ እንሆን እና ነገሮች ይሻሻላሉ።»
« እንደ እኔ አመለካከት ቤኒን ሲቲ ጥሩ የመኖሪያ ቦታ ናት። ነገር ግን መንግሥት በቂ እየሰራ አይደለም። የደህንነቱ ሁኔታ አስተማማኝ ስላልሆነ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምረን ነው የምንሯሯጠው።»
በርካታ የአፍሪቃ ወጣቶች  የምዕራባውያን ሀገራትን በቀላሉ ስራ የሚገኝባቸው ፣ ጥሩ ህይወት የሚኖርበት አድርገው ነው የሚመለከቱት። ከነዚህ አንዱ ዛሬ ስፔን የሚኖረው ናይጄሪያዊ ኬሌቺ ጉድላክ ነው። የሳህራን በረሃ እና የሜዲትራንያንን ባህር ሊያቋርጥ ሲል የሚገጥሙትን ፈተናዎች ሳያገናዝብ ነበር በወቅቱ ለጉዞ የተነሳው። ዛሬ ይህንን ተሞክሮውን « ከሞት ጋር ቁማር » በተሰኘው መፅሀፉ ይተርካል። « ቸልተኝነት ዋናው ምክንያት እንደሆነ ተረድቻለሁ። ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚደረገው ጉዞ ቀላል እና ሳምንት ወይም 2 ሳምንት የሚፈጅ ተደርጎ ይታሰባል። ይህ እንዳልሆነ በጉዞዬ የተረዳው ጊዜ ይህንን ቸልተኝነት ማስቆም አለብኝ ብዬ ተነሳሁ። ለዚህ ነው ይህንን መፅሀፍ የፃፍኩት። አፍሪቃውያን እንደዚህ አይነት ጉዞ ከማድረጋቸው በፊት ሁለት ጊዜ እንዲያስቡበት።»


 ጉዞው ምን ይመስል ነበር?« ወደ ገሃነም የሚደረግ ጉዞ ነበር ማለት እችላለሁ። ጥሩ ጓደኛዬን በሞት አጥቻለሁ። በረሃ ላይ ህይወቱ ሲያልፍ ተመልክቼያለሁ። እኔ እራሴ እድለኛ ሆኜ ነው እንጂ ልሞት ነበር። ወጣት ልጅ ስትደፈር አይቼያለሁ። መሳሪያ ደቅነውብን ስለነበር ምንም ማድረግ አልቻልንም። እነዛ አራት ቀናት በርሃ ላይ በጣም መጥሮ ነበሩ።»  
ጉድላክ ህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች  በሳምንት ቢበዛ በ 2 ሳምንት ውስጥ አውሮፓ መድረስ እንደሚችል እንዳሳመኑት እና ገንዘብ እንደከፈላቸው ይናገራል። ለጉዞ ያስፈልግሃል ያሉትን ማስረጃዎች ጉድላክ እንዳሟላም  በኒዠር በኩል አድርጎ ወደ ሰሀራ በረሃ ከበርካታ ስደተኞች ጋር ጉዞ ጀመረ። አልጄሪያን አቋርጦም ከብዙ ፈተና በኋላ ሞሮኮ ደረሰ። ከዛም የሜዲትሪያንን ባህር ማቋረጥ ነበረበት። የመጀመሪያ ሙከራው አልተሳካም። 36 ሰዎችን አሳፍራ የነበረ አንዲት ጀልባ ስትሰምጥ ጉድላክ ከተረፉት 13 አንዱ ነበር። ገንዘብ ሞሮኮ ላይ አጠራቅሜ በሁለተኛ ሙከራዬ ተካሳልኝ የሚለው ጉድላክ አውሮፓ እስኪገባ የፈጀበት ጊዜ ግን 3 ዓመት ነበር። ምን እንደሚጠብቀው  አስቀድሞ ቢያውቅ ኖሮ ጉዞውን ይጀምር ነበር?« በፍፁም! በፍፁም! መፅሀፉን አፍሪቃ ውስጥ ያነበቡ ሰዎች እንኳን ፃፍክ እኛም ጉዞ ልንጀምር ነበር፤ ካነበብነው በኋላ ግን ለመቅረት ወስነናል እያሉ ያመሰግኑኛል። »
ይሁንና ጉድላክን የሚያመሰግኑት ብቻ አይደለም ያሉት። የDW የፌስ ቡክ ተከታታይ ራውል ጉንዛለስ ለምሳሌ ወጣት አፍሪቃውያን ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ ምክር መለገስ ከሚችሉ ሰዎች ውስጥ አትካተትም። ምንም እንኳን የሚያስፈራ ጉዞ ብታደርግም አሁንም ስፔን ነው የምትኖረው። ትክክለኛ ይሆን የነበረው፤ አውሮፓ ደርሶ ፤ እንዳሰበው ሆኖ ስላላገኘው ወደ ሀገሩ ከተመለሰ ሰው ነው። ይላል። ለዚህ ጉድላክ ምላሽ ሰጥቷል።« የራውልን አመለካከት እቀበላለሁ። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ባለው አልስማማም። ሶስት ዓመት በፈጀብኝ ጉዞዬ የነበረኝ ተሞክሮ ከባድ ነበር። ለዚህም ነው አፍሪቃ ያሉ ሰዎች ሊያዳምጡኝ የሚገባው። እዚህ የደረስኩት እድለኛ ስለሆንኩ ብቻ ነው። ይሁንና ገላዬ በሙሉ ጠባሳ ነው።  በጉዞዬ ወቅት የገጠሙኝ ብዙ ጠባሳዎች አሉ። አሁን ድረስ ያሳለፍኩትን ጉዞ ሳስብ ያቃዠኛል። ባህር ላይ፣ በርሃ ላይ የሞቱትን ሰዎች በዓይኔ አይቻቸዋለሁ። ስለዚህ ታሪኬ ዋጋ ያለው እና ጉዞው ምን ይመስል እንደነበር ለአፍሪቃውያን  መንገር የምችል ትክክለኛው ሰው ነኝ ብዬ አምናለሁ።» 
ስለሆነም ምክሩን አላቋተጠም።«መምጣት የለባቸውም። ጨርሶ ማሰብም የለባቸውም። ከሚገጥማቸው ፈተና አንፃር አፍሪቃ ውስጥ ያላቸው ህይወት ይሻላል። አሁን ድረስ ብዙ ሰዎች ሊቢያ ውስጥ ስላለው አስጨናቂ ሁኔታ ይነግሩኛል። የሌሎቹንም ተሞክሮ አሰባስቤ አንድ መፅሀፍ ማድረግ እፈልጋለሁ። ስለዚህ የምመክራቸው ጉዞውን አታድርጉ፤ ጥሩ አይደለም። ትክክልም አይደለም።»


የ 27 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ወጣት መሀመድ ግን መሰደድን አሁንም ድረስ እንደአማራጭ ያያል። መሀመድ የሌሎች አፍሪቃውያንን ተሞክሮ ብቻ ሳይሆን ጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጅቡቲ ወደ የመን ሲጓዙ ባህር ሰምጠው 57 ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን ሰምቷል። በዚህም አዝኗል። እሱም ከተጓዘ ይህ ሊገጥመው እንደሚችል ያውቃል።
የ DW 77ከመቶው አዘጋጅ ክፍል ለምን ወጣት አፍሪቃውያን በሊቢያ የስደተኛ እስር ቤቶች እና በባህር ላይ የሚገጥማቸውን ፈተና እያወቁ ብዙዎች ህይወታቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥሉ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ አወያይቶ ነበር። 
የጥቂቶቹን አስተያየቶች ፥
ሄንሊ ኤኳና ኤኩዌሎ ከኬፕታውን ደቡብ አፍሪቃ ፦ ሜዲትራኒያን ባህር ላይ ህይወታቸው የሚያልፍ ወጣቶች ብዙ ግንዛቤ የሌላቸው ናቸው። አውሮፓ ገነት ናት ብለው ያስባሉ። ግን ተሳስተዋል። ያላቸው የግንዛቤ እጦት ነው ህይታቸውን እስከማጣት የዳረጋቸው። 
« ኤዲ ኤዲ ከዩጋንዳ ፣ ከአፍሪቃ ወደ ምዕራብ ሀገራት ህዝባቸው የሚሰደዱ ሀገራት ምክንያቱ ግልፅ ነው። ተጠያቂዎቹም እጅግ ስግብግብ የሆኑት የአፍሪቃ መሪዎች ናቸው»
ጎቱ ፌቨር ከጋና፤ ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ማሻገሩ ራስ ወዳድነት ነው ይላል።»

ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ 

Audios and videos on the topic