1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያለ ጠበቃ የቀጠለው የአቶ ታዮ ደንደኣ የፍርድ ቤት ክርክር

ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 2016

አቶ ታየ ደንደኣ ለችሎቱ ባቀረቡት ጥያቄ ሁለት የእጅ ስልኮቻቸው፣ አንድ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እና «መደመር ሲመረመር» የሚል ረቂቅ ጽሁፍ እንዲመለሱላቸው ጠይቀው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡ አቶ ታዬ ደንደኣ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ሲኖሩበት ከነበረው ቤት ያለ አግባብ መበተናቸውን በቅሬታቸው አክለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4igiv
በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ
በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣምስል Geberu Godane

የቀድሞ ሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ የአቶ ታዬ ደንደዓ የፍርድ ቤት ውሎ

የቀድሞ ሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ የአቶ ታዬ ደንደዓ የፍርድ ቤት ውሎ 

በእሥር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ ዛሬም ያለ ምንም ጠበቃ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡የቀድሞ ባለስልጣኑ ተከሳሽ ጠበቆቻቸው ላይ ከመንግስት የሰላ ማስፈራሪያ በመድረሱ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ከዚህ በፊት ሰኔ 18 ቀን 2016 ኣ.ም. ጉዳያቸውን ለሚመለከት ችሎት ገልፀው ነበር፡፡ አቶ ታዬ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ያስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገመንግስትና ሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ላይ ሲቀርቡም ያለ ጠበቃ ነው፡፡ይህንኑን ተከትሎ ችሎቱ ለአቶ ታዬ በመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው ይፈልጉ እንደሆን ተጠይቀው፤ በመንግስት የሚቆምልኝ ጠበቃ አልፈልግም የሚል ምላሽ ለችሎቱ ሰጥተዋል፡፡ 

የአቶ ታዬ ደንደአ የክስ መቃወሚያ ውድቅ መሆን
የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ አባል የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ ከአንድ ወር በፊት ለችሎት ቀርበው እንዳስረዱት “አቃቤህግ እና ሰዎቻቸው” ባሏቸው አንድም ጠበቃ እንዳይቆምላቸው በጠበቆቻቸው ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሷል፡፡ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ልደታ ያስቻለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የክሳቸውን ሂደት የተከታተሉት አቶ ታዬ፤ ዛሬም ያለ ምንም ጠበቃ ችሎቱ ፊት መቅረባቸውን ካስረዱ በኋላ ፍርድ ቤቱ በሕገ-መንግስታዊ አሰራሩ መሰረት በመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው ይፈልጉ እንደሆን ጠይቋቸዋል፡፡ በዚህን ወቅትም አቶ ታዬ መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው እንደማይፈልጉ ለችሎቱ አስረድተው የክስ ሂደቱ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

 ይሁንና ከዚህ በፊት ከሳሽ አቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን የሰነዶች እና ሰው ማስረጃን በመንተራስ በዛሬው እለት ብይን ለመስጠት የተያዘው ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ባቀረበው የተደራረቡ መዝገቦች መብዛት ምክንያት አሁንም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙን አስረድቷል፡፡
ከዚህ በፊትም ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ የነበረው ችሎቱ ባሉት ተደራራቢ መዝገቦች ምክንያት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚስፈልገው በማስረዳት በመዝገቡ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ የፖለቲከኛ ታዬ ደንደዓ መታሰር

በተከሳሽ የቀረቡ የመብት ጥያቄዎች

ችሎቱ የዛሬው ዋና ጉዳይ የሆነውን ብይን የመስጠት ጉዳዩን ዳግሞ ቀን ማራዘሙን ተከትሎ በዚያ ላይ ቅሬታ ያላሰሙት ተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደዓ፤ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ያቀረቡዋቸው የመብት ያሉት ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘታቸውን አማረው አንስተዋል፡፡ “የተከበረው ፍርድ ቤት ላይ ጫና መኖሩን አውቃለሁ” ያሉት አቶ ታዬ “ያቀረብኳቸው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አሉ” በማለት በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 13 መሠረት አስፈጻሚ አካላት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ማስከበር ብቻ ሳይሆን “የማክበርም ግዴታ አለባቸው” በማለት ከዚህ በፊት ለችሎቱ ያቀረቡዋቸው “የንብረቶቼ ይመለስልኝ” ጥያቄዎቻቸው በፍርድ ቤት ተደጋጋሚ ትዕዛዞች ቢሰጥባቸውም እስካሁን አልተፈጸሙም በማለት አማረው አንስተዋል፡፡ 

በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ታዬ ደንደኣ
በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ታዬ ደንደኣምስል Shewangizaw Wegayehu/DW


ይሁንና ችሎቱ ከፌዴራል ፖሊስ ተላከልኝ ብሎ ዛሬ ለተከሳሹ ያነበበው ደብዳቤ በኤግዝብትነት ያልተያዙ ንብረቶች በተከሳሹ ባለቤት በኩል እንዲወሰዱ ፈቅዷል፡፡ ሆኖም በችሎቱ ላይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የታደሙት የአቶ ታዬ ባለቤት ከዚህ በፊት ወደ ፌዴራል ፖሊስ ሄደው ንብረቶቹ በፖሊስ የተያዙት በኤግዝብትነት መሆኑ ተገልጾላቸው መጽሃፉን ብቻ መውሰድ እንደሚችሉ እንደተነገራቸውና ከፖሊስ ዳግሞ የተደወለላቸው ገና ትናንት ከሰዓት ዘጠኝ ሰዓት መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ ችሎቱም ይህንኑን ካደመጠ በኋላ ነገ ዳግም ወደ ፖሊስ አምርተው በኤግዝብትነት ያልተያዙ ንብረቶቹን መቀበል እንደሚችሉ አዟል፡፡   
ተከሳሹ ከዚህ በፊት ለችሎቱ ባቀረቡት ጥያቄ በምርመራ ወቅት በኤግዚቢትነት ያልተያዙ ብዙ ንብረቶች ቢመለሱም ሁለት የእጅ ስልኮቻቸው፣ አንድ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እና መደመር ሲመረመር የሚል ረቂቅ ጽሁፍ ንብረቶቻቸው በመሆናቸው እንዲመለሱላቸው ጠይቀው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡ የአቶ ታዬ ደንደአ የክስ መቃወሚያ ውድቅ መሆን
አቶ ታዬ ደንደኣ “ህዝብ እናገልግል፣ ህዝብ እንዳይዘረፍ ብዬ ከመሟገት ውጪ ያጠፋሁት ጥፋት የለም” ብለው ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ያለ አግባብ ሲኖሩበት ከነበረው ቤት መበተናቸውን በቅሬታቸው አክለዋል፡፡

በአቶ ታዬ ደንደዓ ላይ የቀረበው ክስ ጭብጥ


የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደአ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስት እና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው ከመንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ የገቡትን የ“ኦነግ ሸነ እና ፋኖ” ዓላማን ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፤ በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መሰል ይዘት ያለው መልእክቶችን አስተጋብተዋል የሚል ሶስት ክሶች ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ተከሳሹ ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሣሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5:00 ሰዓት ላይ በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ከሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና ከ60 ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል መባሉም ይታወቃል።
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ