ያለ አሣሪ ውል የተበተነው የኮፐንሄገኑ ጉባዔና ቀጣዩ ተስፋ፣ | ዓለም | DW | 21.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ያለ አሣሪ ውል የተበተነው የኮፐንሄገኑ ጉባዔና ቀጣዩ ተስፋ፣

መንግሥታት ለረጅም ጊዜ ዝግጅት አድርገውበት ነበር ፣ ለተፈጥሮ አካባቢ የሚቆረቆሩ የመንግሥታት ያልሆኑ ድርጅቶችም ፕላኔታችንን ለመታደግ ሰፊ ጥረት ይደረግ ዘንድ ከመወትወት የቦዘኑበት ጊዜ አልነበረም፣ የለምም።

default

አሁን በመጨረሻ ኮፐንሃገን ላይ በተቋጨው አንዳች አሣሪ ህግ በሌለበት ስምምነት ያዘኑትና የተናደዱትም እነዚሁ ወገኞችና በዛ ያሉት የሞቃት አገሮችና ደሴቶች መንግሥታት ናቸው። ኀያላኑ «ተልባ ቢንጫጫ» ዓይነት አቋም ይዘው መቅረባቸው የአዳጊ ዎቹ አገሮች ተወካዮችም በጉባዔው መቅድም፣ እንደ አንበሳ አግሥተው፣ ኮፐንሃገን ሲደርሱ እንደ አይጥ ሲጥ በማለታቸው፣ ስብሰባው ዓለማችንን የሚታደግ አንዳች ረብ ያለው ውጤት ሳያስመዘግብ እንዲበተን አድርጎታል። የዓለም የሙቀት መጠን ከ 2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ እንዳይጨምር ሲባል፣ አማካዩ የሙቀት መጠን ተወስዶ ነው። በተፈጥሮ ሞቃት የሆነውን ከምድር ሰቅ በሰተደቡብና ሰሜ ን 23,5 ዲግሪ ገደማ (2,630 ኪሎሜትር) ራቅ ብለው የሚገኙትን ሞቃት የዓለም ክፍሎች መቀነት አይመለከትም ። ሰለዚህ አማካዩ የዓለም የሙቀት መጠን 2 ዲግሪ ከደረሰ በእነዚህ ሞቃት ቦታዎች 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ ይደርሳል ማለት ነው። ይህ ደግሞ አንዳንድ ታዛቢዎች ሲናገሩ እንደሚሰማው «ለአፍሪቃ ሞት ወይም ጥፋት »ነው።

(በኮፐንሄገኑ ጉባዔ የተሳተፈችው፣)የዶቸ ቨለ ባልደረባ፣ ሔለ የፕሰን እንደምትለው ግን፣ ዕድገትም፣ ውድቀትም የጋራ ነው። አንዱ ፣ የሌላው፣ ምንጊዜም ጥገኛ ነው። የኮፐንሄገኑ የአየር ንብረት ጥበቃ -ነክ ጉባዔ አክትሟል። ዓለም አቀፍ የጋራ ስምምነት ሊገኝ ይችላል ተብሎ የታሰበውም ከሽፏል። የተገኘው ውጤት፣ እንደታሰበው አይደለምና!

አንድ የማይታበል ሐቅ ከኮፐንሄገኑ «ቤላ» የስብሰባ አዳራሽ ውጭ የዓለም ኅብረተሰብ ፣ የረጅም ጊዜ የጋራ የመቆርቆር ስሜቱን ሲያዳብር ቆይቷል። በዓለም ዙሪኢ፣ ጭንቀቱ፣ ሥጋቱ፣ ያው፣ ተመሳሳይ ነው። የአየር ጠባይ ለውጥ፣ የአየር ንብረት ቀውስ ያስከትላል የሚለው ሥጋት፣ ፣ አንድ ዓይነት ነው። ብሩኅ ተስፋ ማሳደሩንም የዚያኑ ያህል ይጋራሉ።

አንድ ከካሜሩን የመጡ፣ የመንግሥት ያልሆነ ድርጅት ተወካይ እንደተናገሩት፣ ከአገራቸው ከመነሣታቸው በፊት፣ እናታቸው፣ «ኮፐንሄገን!ኮፐንሄገን! የሚባል ቃል በተደጋጋሚ ፣ እስኪሰለቸኝ በመስማት ላይ ነኝ፣ ምንድን ነው እሱ? የኢንዱስትሪ ምርት ነው? ጥሩ ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ። ልጃቸውም፣

«እማማ፣ ኮፐንሄገን፣ የሚባል ምርት ገና አልቀረበም፤ ከጉባዔ ስመለስ ግን ኮፐንሄገን የሚባልምርት ይቀርባል፣ ያኔ መርቱ፣ ጥሩ ፣ ወይምመጥፎ ስለመሆኑ ትነግሪኝአለሽ»በማለት ነበረ ወደ ጉባዔው ያመሩት። የኮፐንሄገኑ ምርት፣ ለዓለም ፖለቲከኞች ክሥረት ሲሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አያሌ ማኅበረሰባትን የሚያስተሣሥር በቂ ምክንያት አሳይቷል።

በኮፐንሄገን፤ የአየር ንብረት ጥያቄ ብቻ አይደልም የተነሣው። የልማት ጥያቄ፣ የሚበላ እህል፣ የሚጠጣ ውሃ የማግኘት መብት፣ በአጭሩ የኅልውና ጥያቄ ነበረ የቀረበው።

ሲቭሉ ማኅበረሰብ፣ በዓለም ፖለቲከኞች ላይ እንዳሁኑ ግፊቱን አጠንክሮ አያውቅም ነበረ። በተቃውሞ ሰልፍ ፣ በአደባባይ የፖለቲካ ስብሰባ፣ ችሎታ ባላቸው የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ነክ ሊቃውንት ጥብቅና የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ኮፐንሄገን ላይ ተረባርበው ነበር። የዓለም ፖለቲካ ፣ የሆነው ሆኖ፣ ከአንግዲህ፣ ከበላይ ባለሥልጣናት በኩል ሊመራ እንደማይገባና እንደማይቻል ለወደፊቱ ፍንጭ ሳይሰጡም አልቀሩም ። ከታች ያለው ጥንካራ እንቅሥቃሴ፣ እውቁ ባለቀኔ ደራሲ Berthold Brecht እ ጎ አ ሰኔ 17 ቀን 1953 ዓ ም፣ የተፈጸመውን ድርጊት አስመልክቶ የተናገረው ጥቅስ፣ ለዘመኑ ፖለቲከኞችም የሚሆን ነው። «መንግሥት፣ አዲስ ህዝብ ቢመርጥ ይቀለው የለም ወይ!?» ሲል ነበረና ያኔ Berthold Brecht የተናገረው።

በባለጸጎችና በድሆች፣ በሰሜንና በደቡብ፣ በመኖርና በመሞት መካከል ያለው ልዩነት እጅግ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው። ይህ በአየር ንብረት አጠባበቅ ድርድር ላይ ብቻ ሳይሆን ፣ በአጠቃላይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ፣ ልዩነቱ ጎልቶ በመታየት ላይ ነው። ይህ ኅብረተሰብን የሚያቆስል ልዩነት፤ ስግብግብነትን፣ ፍርኅትን አለመተማመንንና የመሳሰሉትን እያንፀባረቀ ነው።

ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ ቁስሉ ከውስጥ መሻር መጀመር አለበት። የፈጠራ ችሎት፣ ትብብር፣ ተምኔታዊ ዓላማ--የመንግሥት ባልሆኑ ድርጅቶች ዘንድ ነጥረው ታይተዋል። በሳይንሱ ዓለምም እንዲሁ። በኤኮኖሚው ዓለም ረገድም ቢሆን፣ በከፊል የታየ እንደመሆኑ መጠን ፣ ዓለም አቀፉ ቁስል አገግሞ፣ አዲስ ለአየር ንብረት የሚቆረቆር ብቻ ሳይሆን፣ ለሁሉም ፍትኀዊ መጻዔ-ዕድልን የሚያስተካክል መንገድ መቀየሱ አይቀርም።

ተክሌ የኋላ፣

ተዛማጅ ዘገባዎች