ያለፈው ዓመት የጤና ችግሮች እና የመከላከል ርምጃዎች | ጤና እና አካባቢ | DW | 01.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ያለፈው ዓመት የጤና ችግሮች እና የመከላከል ርምጃዎች

ባለፈው በ2011ዓ,ም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቁጥሩ በርከት ያለ የጤና ችግር በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ነበር። ከበሽታዎቹ ኮሌራ፣  ቺኩንጉኒያ፣ የደንጊ ትኩሳት፣ ቢጫወባ፣  ኩፍኝ፣  እና የልጅነት ልምሻ ወይም ፖሊዮ ይጠቀሳሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:58

በዓመቱ ከስድስት በላይ ወረርኝ ተከስቷል

በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲከሰት አጣዳፊ ተቅማጥ እና ተውከት በሚል ለዝቦ ይጠራ የነበረው ኮሌራ ባለፈው 2011 ዓ,ም ነው በዓለም ደረጃ በሚታወቀው ስሙ ተጠርቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ዋና ከተማዋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱ የተነገረው። ከሀገሪቱ የጤና ጥበቃ አካላት የወጡት መረጃዎች ወረርሽኙን በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ቢያመለክቱም አሁንም በሦስት ክልሎች ላይ በሽታው አልፎ አልፎ እንደሚታይ ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር  የሆኑት ዶክተር በየነ ሞገስ እንደሚሉት ከኮሌራ ወረርሽኙ የተረፉት የቤኒሻንጉል እና ጋልምቤላ ክልሎች ብቻ ናቸው።

«ኮሌራ ከቤንሻንጉል እና ከጋምቤላ ክልሎች ውች በሁሉ ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች በድሬደዋ እና በአዲስ አበባ ማለቴ ነው ተከስቶ ነበር። በእነዚህ ክልሎችም የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ቀድሞ ወረርሽኝን በማረጋገጥ ፈጣን ምላሽ ተሰጥቷል።»

እንደመረጃው በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ በሻሸመኔ ወረዳ 15 እንዲሁም በፈዲስ ወረዳ 20 ሰዎች፣  በሐረሪ ክልል በስድስት ወረዳዎች 15 ሰዎች እና በደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ ደግሞ 14 ሰዎች በኮሌራ ተይዘው አስፈላጊውን ህክምና አግኝተዋል።

BG Ebola-Ausbruch im Kongo (Reuters/O. Acland)

የግል ንፅሕናን መጠበቅ ዋነኛው ነው

አዲስ አበባን ጨምሮ ለወራት በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ከ700 ገደማ ሰዎች በተዛመተው የኮሌራ በሽታ መያዛቸው የተመዘገ ሲሆን ከ20 የሚበልጡት በበሽታው ሰበብ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ባለፈው ሳምንት ደግሞ ሻሸመኔ ላይ ኮሌራ አንድ ሰው ገድሏል። ውሎ አድሮ አሁን በሀገሪቱ የኮሌራ ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል ቢባልም አሁንም ኅብረተሰቡ እንዳይዘናጋ ይመከራል።

ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው ዓመት የተከሰተው ወረርሽኝ በትንኝ ንክሻ ሰበብ ከሰው ወደሰው እንደሚተላለፍ የተገለፀው ችኩንጉኒያ የተሰኘው በሽታ ነው።

በተለይ ድሬደዋ ከተማ እስካለፈው ነሐሴ ወር ማለቂያ ቀናት ድረስ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በዚህ በሽታ መያዛቸው ተነግሯል። በበሽታው ሰበብ የሰው ሕይወት ስለማለፉ ግን የተሰማ ነገር የለም። የጤና ጥበቃ መረጃ እንደሚያሳየው ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ 86 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች በሽታውን ሊያስተላልፉ የሚችሉት ትንኞች እጭ ተገኝቶባቸዋል። በሽታው ከዚህ በፊት በ2006ዓ,ም ሶማሌ ክልል ውስጥ ተከስቶ በተደረገ ክትትል በቁጥጥር ሥር ሊውል መቻሉን ያመለከቱት ዶክተር በየነ አሁን የተከሰተበትን ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ለትንኞቹ መራቢያ ምቹ ከሆኑ ነገሮች ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ያመለክታሉ።

Karte Äthiopien englisch

ቺኩንጉንያ ተሐዋሲ ከፍተኛ ትኩሳት እና የመገጣጠሚያ ሕመምን እንደሚያመጣ፤ በተጨማሪም ሰውነት ላይ ሽፍታ እንደሚያወጣም ዶክተር በየነ ገልፀውልናል። የጤና ጥበቃ መረጃ እንደሚያመለክተው የችኩንጉኒያ ወረርሽኝን በቀላሉ መቆጣጠር ያልተቻለው በከተማዋ  የዝናብ ውኃ የማጠራቀም ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ እና የሚጥለው የተቆራረጠ ዝናብ ለትንኟ መራቢያነት አመቺ በመሆኑ ነው ። ኅብረተሰቡ መጪውዎቹ ወራትም ለዚህች ትንኝ ብቻ ሳይሆን ለወባ ትንኝ መራባት ምክንያት እንዳይሆን ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበትም ይመከራል።

ከቺኩንጉኒያ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ዶክተር በየነ ያመለከቱት ሌላው ባለፈው ዓመት የተከሰተ ወረርሽኝ ደግሞ የደንጊ ትኩሳት የሚባለው ነው።

 «የደንጊ ትኩሳትም እንደዚሁ በሱማሌ ክልል እና በድሬደዋ ተከስቶ ነበር። እሱም ከቺኩንጉኒያ ጋር በሚያሳያቸው ምልክቶች በአብዛኛው የመመሳሰል ነገር አለው።  የሚተላለፍበትም መንገድ ተመሳሳይ ትንኝ ነች የምታስተላልፈው።»

ከዚህም ሌላ በደቡብ ክልል ወላይታ ሶዶ ላይ የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር እና ታማሚዎች አፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙ መደረጉንም አንስተዋል። ቢጫ ወባ ከሌሎቹ የሚለየው መከላከያ ክትባት ስላለው በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች ክትባቱን እንዲያገኙ መደረጉንም አመልክተዋል። እንደኮሌራ ሁሉ በአብዛኞቹ ክልሎች ተከስቶ የነበረው ደግሞ የኩፍኝ ወረርሽኝ ነበር። ዶክተር በየነ እንደሚሉት ኅብረተሰቡን ከማስተማር አንስቶ አስፈላጊው የበሽታ መከላከል ተግባር ተከናውኗል።

በ2011ዓ,ም   የልጅነት ልምሻ ማለትም ፖሊዮም  ኢትዮጵያ ውስጥ  ከተከሰቱት ወረርሽኞች አንዱ ነበር።  የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ተከስቶ ወዲያው የፖሊዮ ክትባት በየቦታው በመዳረሱ ከሁለት ዓመታት በኋላ በሽታውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ተችሎ ኢትዮጵያ ከልጅነት ልምሻ ነፃ የሆነ ዓመት ማሳለፏ በዓለም የጤና ድርጅት ሳይቀር ተመዝግቧል። በ2011ዓ,ም እንደገና በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ቦህ ወረዳ አንጋሎ ቀበሌ በግንቦት ወር 2011ዓ.ም መከሰቱ ነው የተሰማው። በዚህ ዓመት በወረርሽኝ መልክ የተከሰቱት በሽታዎች በርክተው እንደሁ የጠየቅናቸው ዶክተር በየነ፤ ከወትሮው የበለጡ በሽታዎች ተከስተው ሳይሆን በሽታዎቹን የመለየት እና መረጃም የማዳረሱ አሠራር በመጠናከሩ እንደሆነ ነው የገለፁልን። ካለፈው ዓመትስ ወደአዲሱ ዓመት 2012 የተሻገሩ ይኖሩ ይሆን?

ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic