ዩፕ ሀይንከስ እና የወደፊቱ ዕቅዳቸው | ስፖርት | DW | 05.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ዩፕ ሀይንከስ እና የወደፊቱ ዕቅዳቸው

የ68 ዓመቱ የኤፍ ሴ ባየርን ሚውንኽኑ የእግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ ዩፕ ሀይንከስ በቀጣዩቹ የቡንድስሊጋ የግጥሚያ ወራት ዕረፍት እንደሚያደርጉ ትናንት በይፋ አስታወቁ።

ይሁንና፣ ባየርን ሚውንኽንን ለሦስትዮሽ ሻምፒዮና ያደረሱት ዩፕ ሀይንከስ፣ ብዙዎች እንደገመቱት፣ የአሠልጣኝነቱን ሙያ በዚሁ ማብቃታቸውን እና የጡረታ ጊዜአቸውን መጀመራቸውን ሳያስታወቁ ነበር ያለፉት።

ተሰናባቹ የኤፍ ሴ ባየርን ሚውንኽኑ የእግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ ዩፕ ሀይንከስ የዚሁ ቡድን አሠልጣኝ ሆነው ያገለገሉባቸውን ዓመታት መለስ ብለው ሲመለከቱ እጅግ ውጤታማ እንደነበሩ ይናገራሉ። የሚውንኽኑ ቡድናቸው ዘንድሮ የቡንድስሊጋውን ሻምፒዮና፣ የአውሮጳ ሻምፒዮና እና የፌዴሬሽኑ ዋንጫ ባለቤት በመሆን በጀርመን ሦስት ሻምፒዮናዎችን በማሸነፍ የመጀመሪያው ቡድን ሆኖዋል።

« በዘንድሮው የጀርመን የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ግጥሚያ ወቅት በጠቅላላ በአንድነት እና በሙሉ ልብ፣ በራስ መተማመን የታከለበት ግልጽ አቅድ የያዘ ግሩም ጨዋታ ነበር ያሳየነው። »

የ68 ዓመቱ ሀይንከስ ለጊዜው ከአሠልጣኝነቱ ሙያ እንደሚለያዩ በይፋ ቢያስታውቁም እና ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው የእግር ኳስ ክለብ እንደማይሰሩ ቢገልጹም፣ የወደፊቱን ዕቅዳቸውን በተመለከተ ግልጹን መልስ ሳይሰጡ ነበር ያለፉት።

« በመጀመሪያ ዕረፍት አደርጋለሁ። እአአ ከሀምሌ አንድ በኋላ በሀገርም ውስጥ ሆነ በውጭ ሀገር የአሠልጣኝነት ስራ አልሰራም። በባህሪዬ ድምዳሜ በመድረስ አንፃር ነኝ፣ እና ዛሬ ስለወደፊቱ ዕቅዴ ማሳወቅ የማልችልበት ሁኔታ ላይ መሆኔን እገልጻለሁ። አሁን 68 ዓመቴ ነው እና ከ ብሎም ከአሠልጣኝነቱ ሙያ በኋላም ሕይወት አለ። »

ሆኖም ሀይንከስ በተለይ ካለፉት ሣምንታት ስራ በኋላ የሽምግልና ስሜት እደተሰማቸው ነው የገለጹት።

« ስራው ጉልበት እና ብዙ አቅም የሚጠይቅብኝ መሆኑን ተገንዝቤአለሁ። »

እንደ ሀይንከስ ገለጻ፣ የአንድ ትልቅ የእግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ ከሆኑ ዕረፍት ሊያደርጉ አይችሉም። በዚሁ አነጋገራቸውም ሀይንከስ ፖርቱጋላዊውን ኾዜ ሞሪኞን በመተካት የስጳኛውያኑ የእግር ኳስ ክለብ « ሬአል ማድሪድ አሠልጣኝ ይሆናሉ በሚል ባለፉት ጊዚያት የተሰማውን መላ ምት አብቅዋል። ይህ ግን ከአሠልጣኝነቱ ሙያ ጨርሰው መለያየታቸውን የሚጠቁም አለመሆኑን ነው ያስታወቁት።

የባየርን ሚውንኽኑ የእግር ኳስ ክለብ አመራር ሀይንከስ ክለቡን የሦስት ሻምፒዮና ባለቤት ያደረጉበት እና ከተጫዋቾች ጋ የነበራቸውን ግንኙነት በአርአያነት ሊታይ የሚገባ ሲል አሞግሶዋል። የስጳኙ ኤፍ ሴ ባርሰሎና አሠልጣኝ የነበሩት ዮሴፕ ጉዋርዲዮላ በቀጣዩ የቡንድስሊጋ የሻምፒዮና ውድድር ላይ የኤፍ ሴ ባየርን ሚውንኽን የእግር ኳስ ክለብን ዩፕ ሀይንከስን በመተካት ያሠለጥናሉ። ዩፕ ሀይንከስ «ከዓለም ምርጥ የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው ባሉት» ክለብ ውስጥ የተጫወቱትን ሚና መቀጠል ቀላል እንደማይሆን ጉዋርዲዮላ ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic