ዩጋንዳ እና አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የምግብ ይዞታዋ | አፍሪቃ | DW | 23.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዩጋንዳ እና አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የምግብ ይዞታዋ

ጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም በብዙ የአፍሪቃ አካባቢ በከባድ ድርቅ ነው የተጀመረው። ከፊል ኬንያ፣ ሶማልያ፣  ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ አብዝተው ተጎድተዋል። በአንጻራቸው ይህ ችግር ጎረቤት ዩጋንዳን አልነካም። የዳቦ ቅርጫት እየተባለች የምትጠራው ዩጋንዳ ተስማሚ በሆነው የአየር ፀባይዋ እና ለምለም መሬቷ  የምግብ አቅርቦት አስተማማኝ  ሆኖ ቆይቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:41
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:41 ደቂቃ

ዩጋንዳ እና የምግብ አቅርቦቷ

ይሁን እንጂ፣  ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ወደ ሀገሯ በሚሄዱት እጅግ ብዙ ስደተኞች  ቁጥር እና በአየር ንብረት ለውጥ ሰበብ ቀላል የማይባሉ ተግዳሮቶች ገጥመዋታል። ችግሩ በተለይ ደረቅ እና ድሆች  በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙትን ማህበረሰቦች እየጎዳ ይገኛል። እና ዩጋንዳ አሁንም የዳቦ ቅርጫት ልትባል ትችል ይሆን ? የብዙዎች ጥያቄ ነው።

በሰሜን ምዕራባዊ ዩጋንዳ ወደምትገኘው አርዋ በሚወስደው አካባቢ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጥሏል። ያካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ በኤል ኒንዮ የአየር ንብረት ክስተት ባስከተለው ለውጥ የተነሳ  ባለፈው ዓመት የተጠበቀው ዝናብ ሳይጥል ነበር የቀረው። በዚያም ሆነ በዚህ ግን  ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ አሁን መጣሉ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር ለሚዋሰነው ለዚህ የዩጋንዳ አካባቢ አዲስ ሁኔታ አይደለም።  

አንዳንድ የአየር ንብረት አጥኚዎች እንደሚሉትም፣  ይኸው የዩጋንዳ አካባቢ ጥሩ ሰብል ሊሰበስብ ይችላል።  በሀይቆቹ እና በነጭ ዓባይ አስተማማኝ የውሀ አቅርቦት ያላት ዩጋንዳ ባለፈው ዓመት በምሥራቅ አፍሪቃ በተከሰተው ድርቅ  እንደ ጎረቤቶችዋ ሀገራት ባትጎዳም፣ ችግሩ ጨርሶ አልታየባትም ሊባል እንደማይችል መንግሥታዊ ያልሆነው የጀርመን የምግብ ድርጅት፣ ቬልት ሁንገርሂልፈ ባልደረባ አንድሪያ በርግ ገልጸዋል። «ዩጋንዳ እርግጥ ባለፉት አስር ዓመታት በብዙ የሀገሯ ከፊሎች መሻሻል አሳይታለች። ይሁንና፣ ስር በሰደደ ያልተመጣጠነ አመጋገብ እና በቂ ምግብ ባለማግኘት ችግር የሚሰቃዩት ህፃናት ቁጥር እጅግ አስደንጋጭ ደረጃ ላይ መድረሱን እናያለን።»

የጀርመን የምግብ ድርጅት፣ ቬልት ሁንገርሂልፈ  ዓለም አቀፍ የረሀብ ሁኔታን የሚመለከተውን ዓመታዊ ዘገባ ከሚያዘጋጁት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።  የዚሁ ድርጅት ባልደረባ አንድሪያ በርግ ንደሚሉት፣ በዩጋንዳ የሚታየው የምግብ እጥረት ችግር ሁሉን የሀገሪቱን አካባቢዎች የሚነካ አይደለም። «በካራሞጃ እና በስደተኞች መጠላ,ያ ጣቢያዎች የተጎጂዎች ቁጥር ከፍ ያለ ሲሆን፣ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ቁጥሩ አነስተኛ ነው። ይሁንና፣ በዩጋንድ  በአጠቃላይ አሳሳቢ የምግብ አቅርቦት እና ያልተመጣጠነ አመጋገብ ሁኔታ አለ ብለን መናገር እንችላለን።»

ሰሜናዊው የዩጋንዳ አካባቢ ከሀገሪቱ እጅግ ድሀ የሚባለው ነው። በደረቃማው ሰሜን ምሥራቃዊ የካራሞጃ አካባቢ የሚኖረው ህዝብ በብዛት አርብቶ አደር ነው፣ ሰሜን ምዕራባዊው አካባቢ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን የሄዱ ስደተኞች የሰፈሩበት ሲሆን፣ እጅግ ኋላ ቀርም ነው። በመንግሥቱ አንጻር  ለብዙ ዓመታት የተንቀሳቀሰው ጆሴፍ ኮኒ የመሩት ሎርድ ሬዚስተንስ  አሚ የተባለው ቡድን ባካባቢው ባካሄደው የሽብር ተግባር የተነሳ አካባቢው በአሁኑ ጊዜ  መሰረተ ልማቱ አልተስፋፋም፣ ይህ ነው የሚባል የግብርና ዘርፍም የለውም።  ለዚህም አንዳንዶች የዩጋንዳን መንግሥት ሲወቅሱ  ይሰማል፣ አንድሪያ በርግ ግን ወቀሳው ትክክለኛ አይደለም ይላሉ።  « እኔ እንደማስበው፣ ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ዩጋንዳ ያካባቢውን ህዝብ መርዳት ሳትፈልግ ቀርታ ሳይሆን፣ በወቅቱ መመልከት ያለባት ብዙ ጉዳዮች በመኖራቸው ነው። ይህ ከአቅሟ በላይ ሆኗል። »

የደቡብ ሱዳን ውዝግብ ባለፈው ዓመት እንዳዲስ በተጋጋለበት ጊዜ ዩጋንዳ ትልቅ ፈተና ነበር የገጠማት። ያኔ 1,3 ሚልዮን ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች ነበሩ ውዝግቡን በመሸሽ ወደ ዩጋንዳ የሄዱት። በብዙ ሀገራት አንጻር ዩጋንዳ ለእያንዳንዱ ስደተኛ ቤተሰብ የሚያርሰው መሬት በመስጠት ራስ አገዝ የሚሆንበትን ፖሊሲዋ አስተዋውቃለች። በአሩዋ ሰሜናዊ ቀበሌ የሚገኘው የዩጋንዳ መንግሥት ስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ሰራተኛ ሰለሞን ኦሳካን እንዳስታወቁት ግን፣ ካለፉት ጥቂት ጊዜያት ወዲህ በስደተኞች ቁጥር ብዛት የተነሳ ይህን ፖሊሲዋን ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ችግር አጋጥሟታል።«ቀደም ባሉ ጊዚያት  የቀንድ ከብቶቻቸውን ይዘው ለመጡት ስደተኞች የግጦሽ መሬት ይሰጣቸው ነበር።  አሁን ግን የምንሰጠው መሬት የለንም። ምክንያቱም የስደተኞቹ ቁጥር እጅግ ብዙ ነው።»

ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓም ዩጋንዳ በየቀኑ ከ2,000 የሚበልጡ አዳዲስ ስደተኞች ትቀበል ነበር። በዚያን ጊዜ ዩጋንዳ ለስደተኞች ትሰጠው የነበረውን መሬት ቀነሰች። ይሁንና፣ ስደተኞች በዚህ የተነሳ አርሰው እህል እንዳያመርቱ ሲያደርጋቸው፣ ዩጋንዳ በመሬት አሰጣጥ ላይ የወሰደችውን ውሳኔ መቀየሯን ኦሳካን ገልጸዋል።
«በቢዲቢዲ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በፊት ስደተኞች መኖሪያ ቤታቸውን የሚሰሩበት 30 ሜትር በ30 ሜትር  እንሰጥ ነበር፣ አሁን ግን መ,,,ጠኑን በማስፋት የሚያርሱት 50 ሜትር በ50 ሜትር መስጠት ጀምረናል።»

የሚታረሰው መሬት መስፋት እና በዚህ ዓመት በቂ ዝናብ መጣሉ ብዙ ስደተኞችን ራሳቸውን መመገብ ያስችላቸዋል የሚል ተስፋ አሳድሯል። ከዚህ በተጨማሪ ፣ የዩጋንዳ መንግሥት እና የተመድ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስደተኞቹ እና ስደተኞች አስተናጋጆች ማህበረሰቦችን መደገፍ የሚያስችል በቂ ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥረት ጀምረዋል። የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ 62 ሚልዮን ዩሮ ተጓድሏል። ስደተኞችን የሚያስተናግዱ በካራሞጃ አካባቢ ያሉትን ማህበረሰቦች የምግብ ዋስትናን   የማረጋገጡ ጉዳይ አብዝቶ እንዳሳሰባቸው ነው የቬልት ሁንገርሂልፈ ባልደረባ አንድሪያ በርግ ያመለከቱት።

«ይህን የማረጋገጡ ጉዳይ በቀጣዩ የዝናብ መጠን ላይ ጥገኛ ይሆናል። ይሁንና፣ አካባቢዎች ለድርቅ ተጋላጭ የሚሆኑበት አጋጣሚ ተደጋግሞ መታየቱ የማይቀር ነው።  ይህም በአርብቶ አደሮች ኑሮ ላይ ጫና ሊያሳርፍ ይችላል። ስለዚህ አማራጭ ልናቀርብላቸው ይገባል። ድርቅን እና ተለዋዋጭ የአየር ንብረት የሚያስከተላቸውን መዘዞች መቋቋም የሚያስችሏቸው አማራጮችን በማቅረብ ከነርሱ ጋር አብረን መስራት ይኖርብናል። »

ዜላ ኦኔኮ/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች