ዩጋንዳና ግብረ ሰዶማዊነትን የሚቃወው ህጓ | አፍሪቃ | DW | 25.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዩጋንዳና ግብረ ሰዶማዊነትን የሚቃወው ህጓ

በዩጋንዳ ትናንት ጀምሮ ግብረ ሰዶማዊነት የሚቃወም ህግ ተደንግጓል ። የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የዩጋንዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግብረ ሰዶማዊነትን በመቃወም ባለፈው ታህሳስ ያሳለፈውን ህግ ትናንት በፊርማቸው አፅደድቀዋል ። ህጉ የፀደቀው በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ግብረሰዶማዊነትን በሚቃወሙ ወገኖች መካከል

ለዓመታት ከተካሄደ ትግል በኋላ ነው ። በአዲሱ ህግ የሰዶማዊነት ተግባር በእድሜ ልክ እሥራት ያስቀጣል ። አዲሱ ህግ ከመፅደቁ በፊት ብዙ ጊዜ ወስዷል ። እጎአ በ2009 ነበር ግብረ ሰዶማዊነትን የሚቃወም ረቂቅ ህግ ለዩጋንዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ። የያኔው ረቂቅ ህግ በተደጋጋሚ የግብረ ሰዶም ተግባር ሲፈፅም በተገኘ ሰው ላይ እስከ ሞት ቅጣት የሚደርስ ብይን እንዲተላለፍ የሚደነግግ ነበር ። ይህም በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ ። በመጨረሻም መቀመጫውን ካምፓላ ያደረገው የሃገሪቱ ፓርላማ ባለፈው ታህሳስ ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ እስራት ዝቅ ያደረገውን ህግ አሳለፈ ። ዩጋንዳ በብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ ሥር ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ በወንጀለኛ መቅጫ ደንብ ግብረ ሰዶማዊነትን የሚያስቀጣ አንቀፅ ሰፍሮ ይገኛል ። የአሁኑ ህግ ግን ከዚያም በላይ የጠነከረ ነው ። የግብረ ሰዶማውያንን ጥቅሞች የሚያስጠብቁ ወይም ግብረ ሰዶማዊ ባህርይ ያላቸውን ሰዎች የማያጋልጡም በእስራት ሊቀጡ ይችላሉ ። የስደተኞች ህግ ፕሮጀክት የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ ለሆኑት ለሲራንዳ ጀራልድ ብላክስ ይህ አስደንጋጭ መልዕክት ነው ።

«ይህ ረቂቅ እጆችን በሙሉ የሚያስር ነው ። ህጉ ሁላችንንም ችግር ውስጥ ይከታል ። ከግብረ ሰዶማውያን የሚሠሩ ወይም የሚኖሩ ቤት አከራይም ይሁኑ አለያም ሃኪሞች ብቻ እነዚህን ሰዎች የሚያውቁ ለፖሊስ የማመልከት ግዴታ አለባቸው ። ያን ካላደረግን ልንታሰር እንችላለን ። »

Uganda Homosexualität Aufnahme ohne Gesicht

ሙሴቬኒ ህጉን ወዲያውኑ አላፀደቁም ከዚያ በፊት ሳይንሳዊ ምክር እንደሚፈልጉ አሳወቁ ። አጋጣሚውን በመጠቀም የዩጋንዳ የህግ ባለሞያዎችና የመበት ተሟጋቾች ረቂቅ ህጉ አድሎአዊና ኢህገመንግሥታዊ ነው ሲሉ ስጋታቸው ለፕሬዝዳንቱ ገለፁ ። ዓለም ዓቀፍ ሃኪሞች ችግሩን በማሳወቅ ለፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ ሲፅፉ ከ60 በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች ተወካዮችም ህጉ የሚያስከትላቸውን መዘዞች በመዘርዘር አሳወቁ ።እነዚህ ወገኖች ከሁሉ በላይ ግብረ ሰዶማውያን ህክምና ከተነፈጋቸው HIV ኤድስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ ተፅእኖ ያሳድራል የሚል ስጋት አላቸው ። በዚህ ኦመት መጀመሪያ ላይ የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ጉዳድላክ ጆናታን ሰዶማዊነትን የሚቃወም ህግ በፊርማቸው ካፀደቁ ወዲህ ሙሴቬኒ በዚህ የተደፋፈሩ አስመስሏቸዋል ። የጠበቀ የክርስትና እምነት ያላቸው ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ራሳቸው ከሳይንቲስቶች ከሃኪሞችና ከፖለቲከኞች የመለመሏቸው 11 ሰዎች የሚገኙበት ኮሚሽን የግብረ ሰዶማዊውያንን ተፈጥሮ አጥንቶ የሚያቀርበውን ውጤት በመጠባበቅ ላይ ናቸው ። በመሃሉ ግን የካቲት 3 ቀን 2006 ሃላፊነት ያለበት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውጤቱን በማቅረብ ሳይንሳዊ የተባለ አቋም ወስዷል ። በዚህ ውጤት መሠረት ግብረሰዶማዊነት ተጨባጭ በሆነ ዘረ መል የሚከሰት በሽታ እንዳልሆነ ገልጿል ። አሁንም ቢሆን ተጨማሪ ምርምር ያስፈልጋል ። ኮሚሽኑ ግን እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨባጭ የሆነ ምክር አልሰጠም ። ይሄ ዜና የደረሰው የሙሴቬኒ ፓርቲ አብይ ጉባኤ ላይ ነበር ። በዚያኑ እለትም የ69 ዓመቱ ሙሴቬኒ ለ2016 ምርጫ ራሳቸውን በእጩ ተወዳዳሪነት አቅርበዋል ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የደረሰበትን ውሳኔ ፕሬዝዳንቱ ተቀብለው ሆኖም ግብረሰዶማዊነት በተፈጥሮ የሚወረስ ሳይሆን ከመጥፎ ማህበራዊ መስተጋብር የሚመጣ ነው የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰዋል ። ታዛቢዎች የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ ሥልጣን ለመቆየት የተጠቀሙበት ስልት ነው ሲሉ ተችተዋል ። ከጀርመን የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት አንድሪያ ኬምፕፍ

«ይህን ናይጀሪያን በመሳሰሉ ሌሎች አገራትም የምንታዘበው ነው ። ከልምድ እንደምገነዘበው ይህ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ነው ። እጎአ በ2009 ህጉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ በ2011 ምርጫው ተካሄደ ።»

ሙሴቬኒ በግብረ ሰዶማውያን ላይ የወሰዱት እርምጃ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በኩል ጠንካራ ትችት አስከትሏል ። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እርምጃው ዩጋንዳ ለሚገኙ ግብረ ሰዶማውያን አደጋ መሆኑን ለኡጋንዳውያንም ወደ ኃላ እንደመጓዝ የሚታይ እንደሆነ ተናግረዋል ። የጀርመን መንግሥት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ክሪስቶፍ ሽትራሰር ደግሞ ውሳኔው እንዳስደነገጣቸው አስታውቀዋል ። ከ54 ቱ የአፍሪቃ ሃገራት በ38 ቱ ግብረሰዶማዊነትን በህግ ያስቀጣል ። ከመካከላቸው በሞሪቴንያ በሱዳንና ሶማሊያ በሞት የሚያስቀጣ ድርጊት ነው ።

ፊሊፕ ዛንድነር

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic