ዩጋንዳና የኤቦላ ተሞክሮዋ | ጤና እና አካባቢ | DW | 21.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ዩጋንዳና የኤቦላ ተሞክሮዋ

የኤቦላ በሽታ ዩጋንዳ ውስጥ አራት ጊዜ ተከስቶ ነበር። በኤቦላ ተኀዋሲ የተያዘው ሰው ቁጥር ግን በእጅ ጣት የሚቆጠር ነበር። ይህችው የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገር ምን ብታደርግ ነበር ያኔ የበሽታውን ስርጭት ባለበት ማስቆም የቻለችው? በምዕራብ አፍሪቃ ለምን ይህን ማድረግ አልተቻለም?

የኤቦላ ተኀዋሲ በአራቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት፣ ጊኒ፣ ሲየራ ልዮን፣ ላይቤርያ እና ናይጀሪያ ውስጥ ያስከተለውን ዓይነት ጥፋት ካሁን ቀደም አድርሶ አያውቅም። ጠበብት የኤቦላ ተኀዋሲን እአአ በ1976 ዓም በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ውስጥ ካገኙ ወዲህ፣ በሽታው በኮንጎ፣ በሱዳን ፣ በጋቡን እና በዩጋንዳ 20 ጊዜ ተከስቶዋል። ዩጋንዳ ውስጥ እአአ በ2000 ዓም 425 ሰዎች፣ ከአራት ዓመታት በኋላ እአአ በ2004 ዓም ደግሞ 149 ሰዎች በኤቦላ ተኀዋሲ ታመዋል። ከዚያ በቀጠሉት ዓመታት ኤቦላ እንደገና ዩጋንዳ ውስጥ ሁለት ጊዜ ቢከሰትም፣ በተኀዋሲው የተያዘው ሰው ቁጥር ከ30 አይበለጠም ነበር። ኤቦላ ዩጋንዳ ውስጥ በመጀመሪያ በተከሰተባቸው ዓመታት ለብዙ ወራት ሳይታወቅ በመቆየቱ በሽታውን የሚያሰተላልፈው ተኀዋሲ ብዙ ሰዎችን መያዙን በዩጋንዳ ከዩኤስ አሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከያ መስሪያ ቤት ጋር የትብብር ፕሮዤ የሚያካሂደው የተኀዋሲ ምርምር ማዕከል ባልደረባ ትሬቨር ሹማከር አስታውሰዋል።

« የሆነው ምን መሰለህ፣ የኤቦላ በሽታ ተከስቶ መሰራጨት ጀመረ፤ ይህ የታወቀው ግን ከሁለት እና ሶስት ወራት በኋላ ነበር። በመሆኑም በነዚህ ወራት ብዙ የህብረተሰቡ አባል በተኀዋሲው ተይዞዋል። »

ይህ እንደታወቀ ከህሙማኑ የተወሰደው ደም ለምርመራ ወደ ዩኤስ አሜሪካ መላክ ነበረበት፣ ከዚያም የመጀመሪያዎቹ ዓለም አቀፍ የህክምና ርዳታ ሰጪ ቡድኖች ወደ ሀገሪቱ እስኪመጡ ድረስ ህሙማኑ ርዳታ ሊያገኙ የሚችሉባቸው ብዙ ሳምንታት ነበሩ ያለፉት። ከ2010ዓም ወዲህ ግን በዩጋንዳ ቋሚ የምርምር ማዕከል የተከፈተበት ድርጊት ሹማከርን እና አቻዎቻቸውን የተኀዋሲውን ስርጭት በሽታው ገና ሲከሰት በሚደረግ የደም ምርመራ ለመለየት እንደረዳቸው ሹማከር ገልጸዋል። ሹማከር አክለው እንዳስረዱትም፣ የደሙ ምረመራ ውጤት አንድ ሰው በተኀዋሲው መያዙን ካረጋገጠ አንድ ቡድን ወዲያው ወደታየበት አካባቢ ተልኮ ተኀዋሲው ከተገኘበት ሰው ጋር የተገናኙ ሰዎችን በመመርመር እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት ለማስቆም ተችሎዋል።

ኤቦላን በተመለከተ ሰፊ ተሞክሮ ያካበተችው ዩጋንዳ ሕዝቧን ስለበሽታው ተገቢውን መረጃ በመስጠቷ ሕዝቡ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ተባበራል። በምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት እንደታየው ዓይነት በበሽታው የተያዙትን የመለየት እና የማም ችግር አላጋጠማቸውም።

« ኤቦላን በተመለከተ፣ ዩጋንዳ በሌሎች ምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት አንፃር በጣም ግልጽ ናት፤ የዩጋንዳ ዜጎች በበሽታው የተያዙ ሰዎች ወይም ተይዘው ይሆናል ብሎ የጠረጠሩዋቸው ሰዎች ካሉ ሳይደባብቁ ለሚመለከተው አካል ይናገራሉ። ምክንያቱም በሽታው እንዲሰራጭ አይፈልጉምና። » ይሁናና፣ ኤቦላ የተከሰተባቸው ሀገራት ሕዝቦች የበሽታውን ስርጭት በመታገሉ ረገድ አቅም አልባ በሆነው የየሀገራቸው የጤና አውታር ላይ ያላቸው እምነት ዝቅተኛ ነው።

Westafrika Sierra Leone Ebola Virus ausgebrochen Bluttest

የሲየራ ልዮን ዜጎች ደም ሲሰጡ

ለምሳሌ በሲየራ ልዮን ከአንድ ሀኪም ቤት ጋር በመተባበር ርዳታ የሚሰጠው የጀርመናውያኑ ሀኪሞች ቡድን ባልደረባ ካትያ ሜንት እንደገለጹት ፣ ከፍተኛ የሀኪሞችና የጤና መኮንኖች እ ጥረት ይታያል። ከዚህ በተጨማሪም የጤናውን አውታር በተመለከተ ዩጋንዳ ባለፉት ዓመታት የገነባችው ዓይነቱ መሠረተ ልማት ተጓድሎ ይገኛል። የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ መንግሥት ያወጣቸው የአስቸኳይ ጊዜ ሕጎችም በቂ ግንዛቤ ባላስጨበጠው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘታቸውን ሜንት በማስረዳት ስለበሽታው ለሕዝቡ አስፈላጊውን መረጃ በማቅረቡ ረገድ ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ፋዴላ ቻይብም እንዳስታወቁት፣ በነዚሁ ሀገራት ለበሽታው ተፋጥኖ መስፋፋት የሕዝቦች ዝውውር አንዱ ምክንያት በመሆኑ ዝውውሩን ለመገደብ የሚያስችል ርምጃ መውሰድ የግድ ይላል።

« ሕዝብ ሀገሩ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደሌሎች ሀገራትም በብዛት ይዘዋወራል። እና የተኀዋሲውን ስርጭር ለመቀነስ ከተፈለገ በሽታው አብዝቶ በተስፋፋባቸው ሀገራት ውስጥ የሚደረገውን የሕዝብ ዝውውር መገደብ አስፈላጊ ይሆናል። »

ሂልከ ፊሸር/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic