ዩጋንዳና፣መሰብሰብን የሚገታው ሕጓ፣ | አፍሪቃ | DW | 09.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዩጋንዳና፣መሰብሰብን የሚገታው ሕጓ፣

የዩጋንዳ የተቃውሞው ወገን የአገሪቱ ፓርላማ ፤ የህዝብን የመሰብሰብ መብት የሚያርቅ አዲስ ህግ ፣ ከትናንት በስቲያ ማጽደቁን አስመልክቶ ፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረ-ሰብ ጣልቃ ይገባ ዘንድ ተማጽኖ ለማቅረብ መዘጋጀቱ ተነገረ። በአዲሱ ህግ መሠረት፤ ማንኛውንም

ፖለቲካን የሚመለከት ሰብሰባ ከ 3 በላይ ሰዎች የሚያካትት ከሆነ የፖሊስ ፈቀድ ያስፈልጋል ይላል። ህጉ በተጨማሪ፤ አንዳንድ አካባቢዎች የፖለቲካ ስብሰባ ለማካሄድ ምቹ አይደሉም ብሎ የሀገር አስተዳደር ሚንስትሩ እንዲከለክልም ተጨማሪ ሥልጣን የሚሰጥ ነው።

የተቃውሞው ወገን እንደሚያምነው፤ ህጉ፤ የተቃውሞ ወገኖችን የፖለቲካ እንቅሥቃሴና ተግባራት ለማኮላሸትና በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በሚገባ የሚፎካከረው እንዳይኖር ለመግታት ታስቦበት የወጣ ነው።

በዚህ ሰሞን ካምፓላ ውስጥ ፖሊስ ከተቃውሞ ወገን ደጋፊዎች ጋር ሲሯሯጥና ሲጋጭ ማየት የተለመደ ሆኗል። አብዛኛውን ጊዜ ፖሊስ፣ በሚሰበሰቡ ሰዎች ላይ የገማ ፣ የሚያሳክክ፤ የተቀለመ ውሃና ጋዝ ሲረጭ ፣ አንዳንዴም ፣ ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፈኞች ያቀዱትን ዓላማ እንዳያሳኩ ጥይት እስከመተኮስ ፣ አስደንጋጭ እርምጃ ሲወስድ ታይቷል።

የዩጋንዳ የተቃውሞ ወገን ፤ ብሔራዊ የተቃውሞ ንቅናቄ በሚል ስያሜ የሚታወቀውን በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ የሚደግፈው ፖሊስ፣ የመሰብሰብ ፈቃድ ይሰጣል ብሎ እንደማይጠብቅ ነው የሚገልጸው። በዩጋንዳ ፓርላማ የተቃውሞው ወገን መሪ ናንዳላ ማፋቢ ---ህጉን በመቃወም እስከመጨረሻው እንደሚታገሉ ነው ያስታወቁት።

«የጸደቀው ደንብ በማንኛውም ዴሞክራቲክ አገር የማይፈቀድ ነው። ይህ ህግ፣ ሰብአዊ መብትን የሚጎዳ በመሆኑ፤ በፓርላማ የምንገናኝና በዴሞክራሲ የምናምን ወገኖች፣ህጉን በዩጋንዳ ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ለማስሻር እንሟገታለን።»

ህጉ የጸደቀው፤ የተቃውሞው ወገን አባላት የሆኑ የህዝብ እንደራሴዎች፤ በፓርላማው ምክትል አፈ ጉባዔ ጄኮብ ኦላንያህ ላይ ፣ ኦላንያህ ያሣፍራሉ! እያሉ ይጮኹ በነበሩበት ወቅት ነው። ኦላንያህም ፤ 4 የፓርላማ አባላት ለጊዜው እንዲታገዱ አድርገዋል። የተቃውሞው ወገን አሁን ኦላንያህ ሥልጣናቸውን ያላአግባቡ ተጠቅመውበታል በማለት የሚከስ ሲሆን ፤ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ጣልቃ ይገባ ዘንድ ተማጽኖ እንደሚያቀርብ ነው ያስታወቀው። በፍርድ ቤት በሚሟገቱበት ወቅትም፤ ኦላንያህ፤ ካገር -አገር የመዘዋወር መብት እንዲነፈጋቸው ይደረግ ዘንድ ነው የሚያሳስበው።

« 4 አባሎቻችንን ያላንዳች ህጋዊ ድጋፍ ነው ያባረሯቸው፤ ይህ ማለት ሥልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመውበታል ማለት ነው። በዚህ እንፋረዳቸዋልን። ለ 3 ቀናት የተባረሩት አባሎቻችን ሲመለሱ አንዳች ይቅርታ አይጠይቁም።»

የዩጋንዳ የተቃውሞው ወገን፣ በካምፓላ ማዕከል የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዱን የተለመደ ተግባር አድርጎት ቆይቷል። ፖሊስ በበኩሉ የንግዱን ማኅበረሰብ ተግባር የሚያውክ ነው በሚል ሰበብ ነው፣ ባለ -በሌለ ኃይሉ ፤ ሰልፉን ለማሰናክል የሚጥረው። የዩጋንዳ ፖሊስ አዛዥ ፣ ጀኔራል ካሌ ካይሁራ እንዲያውም ፣ ቁጥራቸው፣ ከ 3 የሚበልጥ ሰዎች፣ ለመሰብሰብ ከፈለጉ፣ ፖሊስን ማስፈቀድ አለባቸው የሚለው አዲስ ህግ ፤ ብዙ ዘግይቶ የፀደቀ ነው ባይ ናቸው።

«ሃገሪቱ፣ በተናጠል የህዝብን ፀጥታ የሚያስከብር ደንብ አያያዝ ማጽደቋ ጠቃሚ ነው፤ የግል የንግድ እንቅሥቃሴዎች እንዳይገቱ ለማድረግ እንጂ፤ የተቃውሞውን ወገን ለመጨቆን ተብሎ የተደበቀ አጀንዳ የለም»።

በካምፓላ ጎዳናዎች፤ ህዝቡን ይበልጥ የሚያሳስበው፤ በፖለቲካ ስብሰባዎች መሳተፍ ካልቻለ እንዴት በዴሞክራሲው ግንባታም ሆነ በፖለቲካው ሂደት ተሳትፎ ሊኖረው ይችላል? የሚለው ነው። አንዳን ድ የፓርላማ አባላት አዲሱን ህግ እንዲሁ ዝም ብለው ነው የደገፉት፤ ግን የፖሊሱ ኃይል በሙያዊ መርኅ፤ ያላንዳች አድልዎ ይሠራል- አይሠራም ፣ ርግጠኞች አይደሉም። ከአላፊ አግዳሚዎችም ይህን ያሉ አልታጡም።

«እንደሚመስለኝ ህጉ ደህና ነው። የትም ቦታ ህዝባዊ ስብሰባዎች፣ በፀጥታ አስከባሪዎች ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። ነገር ግን ያለኝ ሥጋት፤ እዚህ ላይ፤ ህጉ ፣ መሠረታዊ ነጻነትንና መብትን ለማረቅ አላግባብ እንዳይውል ነው። ከዚህ በተረፈ፤ አተገባበሩ የፖሊሱን ሠራዊት እርምጃ የሚያጋልጥ ነው የሚሆነው።»

«በመጀመሪያ ደረጃ የማያስፈልግ ነበር። በእርግጥ ተፈላጊ ጉዳይ ቢኖር፣ አዳዲስ ህግጋትን በየጊዜው ማውጣቱ ሳይሆን፤ በተደራጀና በሠለጠነ መንገድ፣ ያለውን እንዴት አድርጎ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ነው?እንደ ሀገር ፣ ለስማችን ጥሩ አይደለም። የሰዎችን አስተሳሰብና ተግባር ለመቆጣጠር ከመጣር ይልቅ ፣ ይበልጥ ግልጽነት ወዳለበት አሠራር ነው ማምራት የሚኖርብን።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic