ዩውሮን ለማረጋጋት የአውሮፓው ኅብረት ግፊት፣ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 13.05.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ዩውሮን ለማረጋጋት የአውሮፓው ኅብረት ግፊት፣

በዕዳ ይበልጥ ለተዘፈቁት የዩውሮ ተጠቃሚ አባል አገሮች ድጎማ፣ 750 ቢሊዮን ዩውሮ ቢመደብም፣ አሁንም ቀውስ ከአነአካቴው የሚወገድ ባለመምሰሉ፣ ዩውሮን ለማረጋጋት፣

default

ኅብረቱ ግፊቱን ማጠናከር ሊኖርበት ነው ተባለ። የአውሮፓው ኅብረት የኤኮኖሚ ጉዳዮች ዋና ኀላፊ Olli Rehn ፣ የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሆሴ ማኑኤል ባሮሶ በተገኙበት ያቀረቡት እቅድ፤ የዩውሮ አባል አገሮች ላቅ ያለ ዲስፕሊን እንዲኖራቸው ካስፈለገም ቅጣት እንዲቀበሉ የሚያደርግ ነው። ከብራሰልስ፣ የዶቸ ቨለ ባልደረባ ሱዛነ ሄን የላከችውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናክሮታል።

የአውሮፓው ኅብረት የኤኮኖሚ ጉዳዮች ዋና ኀላፊ ኦሊ ሬን፣ ተጨማሪ ቁጥጥር፣ ተጨማሪ የቅጣት እርምጃ ብሎም ላቅ ያለ ትብብር እንዲደረግ ነው የሚመኙት። ኮሚሽኑ፣ አሁን፣ በ3 ዐበይት ጉዳዮች ላይ ሆኗል ያተኮረው። የዩውሮን መረጋጋት ይበልጥ ማጠናከር፣ አውሮፓ ውስጥ በገበያ ያለውን የመወዳደር አቅም ማስተካከል፣ እንዲሁም፣ በግምጃ ቤታቸው ላይ የመራቆት አደጋ ለሚያጋጥማቸው አገሮች ቋሚ የሆነ አስተማማኝ መረብ መዘርጋት የሚሉት ናቸው።

የኦሊ ሬን ፍላጎት፣ አባል መንግሥታት፣ ወደፊት ፣ በጀታቸውን ለብሔራዊ ም/ቤቶቻቸው አቅርበው እንዲጸድቅ ከማድረጋቸው በፊት፣ ረቂቁን፣ በቅድሚያ ብራሰልስ ውስጥ እንዲያስመረምሩ ነው።

«መሠረታዊ ለሆነና ለተጠናከረ የኤኮኖሚ አመራር፣ አብነቱ፣ ወቅታዊ የፖለቲካ መርኅን ማስተባበር ነው። በጊዜ፣ ብሔራዊ በጀት፣ ከአውሮፓውያን ጥያቄም ሆነ ማሳሰቢያ ጋር ተጣጥሞ መቅረብ ይኖርበታል።»

ይህ ሐሳብ፣ የአውሮፓው ኅብረት ሐሳብ የሆነው ሆኖ፣ በብዙ የኣባል ሀገራት መዲናዎች ተቃውሞ እንደሚገጥመውም ሆነ ችላ እንደሚባል ነው የሚታሰበው። በሌላ በኩል፣ አንድ ሀገር፣ ዘወትር፣ የዩውሮን ማረጋጊያ የኤኮኖሚ መርኅ እየጣሰ እስከተገኘ ድርስ ከባድ ማዕቀብ እንዳይጣልበት ያሠጋዋል። የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሆሴ ማኑኤል ባሮሶ እንዳሉት፣ ለምሳሌ ያህል፣ ኅብረቱ የመደበው ድጎማ፣ የበጀት ጉድለት ለሚያሳዩት አገሮች እንደመቀጣጫ ሊቀነስባቸው ይችላል።

«በግልጽ እንድንናገር ይፈቀድልን! ያለማዕቀብ በቂ ተዓማኒነት ስለማይኖር፣ በቃላችን እንጸናለን። የማረጋጊያውና የኤኮኖሚ ዕድገት ነኩ ስምምነት መከበር ስላለበት፣ አባል ሃገራቱን ሊያስፈራራ የሚችል እንዲህ ዓይነት ደንብ መኖሩ ጠቃሚ ነው»።

የአውሮፓው ኅብረት፣ በግሪክ የፋይናንስ ቀውስ ተደናግጦ ሲመክር የሰነበተ ቢሆንም፣ ወደፊትም ተመሳሳይ ቀውሶች እንዳያጋጥሙ የጋራ መደጎሚያ እስከመመደብ መድረሱ የሚታወስ ነው። በሌላ በኩል፣ በሌሎች አባል አገሮች የሚታየው የበጀት ጉድለት ተጨማሪ ችግር እንደማይፈጥር አላሠጋም ማለት አይቻልም። እስፓኝ፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ቀንሳለች። ፖርቱጋልም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ተነሳስታለች። ኢጣልያ በበኩሏ፣ ለመን ግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ ላለማድረግና አዳዲስ ሠራተኞች ላለመቅጠር በማሰላሰል ላይ ናት። የአውሮፓው ኅብረት ፣ በተለይ የበጀት ጉድለት ያጋጠማቸውም ሆኑ ዕዳ የተቆለለባቸው አባል አገሮች፤ በሰፊው ቁጠባ እንዲያስተዋውቁ የሚጠብቅ ቢሆንም፣ ተቀዳሚ ግዴታዎችን አሟልታለች ያላትን የቦልቲክ ባህር አዋሳኝ አገር ፣ ኢስቶኒያን 17ኛ የዩውሮ አባል መንግሥታት ማህበርተኛ ትሆን ዘንድ ተቀብሏታል።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ