ዩክሬይን፤የ«ኦኤስሲኢ» ታዛቢዎች በርሊን ከተማ ገቡ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 03.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ዩክሬይን፤የ«ኦኤስሲኢ» ታዛቢዎች በርሊን ከተማ ገቡ

በመፍቀሬ-ሩሲያ አማፅያን ታግተው የቆዩ የአውሮጳ የፀጥታ እና የትብብር ድርጅት በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ «ኦኤስሲኢ» ታዛቢዎች ትናንት ምሽት ጀርመን መዲና በርሊን ገቡ። እንደ አማፅያኑ፤ ታጋቾቹ ነጻ የተለቀቁት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ነዉ።

ለስምንት ቀናት በመፍቀሬ ሩሲያ አማፅያን ታግተዉ የሰነበቱት የአውሮጳ የደኅንነት እና የትብብር ድርጅት በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ «ኦኤስሲኢ» ታዛቢዎች በአንድ የጀርመን መንግሥት አዉሮፕላን ትናንት ምሽት በርሊን ገቡ። ቡድኑ አዉሮፕላን ጣብያ ሲደርስ የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ኡርዙላ ፎንደር ላይን፤ ከቼክ ሪፐብሊክ እና ከዴንማርክ አቻቸዉ ጋር በመሆን በአዉሮፕላን ጣብያ ተቀብለዋቸዋል። የጀርመንዋ መከላከያ ሚኒስትር የቡድኑን አባላት ያለምንም ጉዳትና፤ ደኅንነታቸዉ በተጠበቀ ሁኔታ ላይ ስላገኙዋቸዉ የእፎይ ታገፅታ እንደታየባቸዉ ተመልክቶአል። እዚህ ዉጤት ላይ ለመድረስ ስለተደረገዉ የትብብር ስራም አመስግነዋል። በስላቭያንስክ ከተማ ከታገቱት እና ትናንት ነጻ ከተለቀቁት የአውሮጳ የደኅንነት እና የትብብር ድርጅት ታዛቢዎች መካከል አራት ጀርመናዉያን፤ አንድ የፖላንድ ዜጋ፤ አንድ ከቼክ ሪፐብሊክ እንዲሁም አንድ የዴንማርክ ዜጋ ይገኙበታል። ከእዚህ ቡድን ጋር አብረዉ የተጓዙት አምስት የዩክሬይን ዜጎች ትናንት ከእገታዉ ነጻ እንደተለቀቁ በጀርመን ወታደር እጀባ ኪይቭ መግባታቸዉ ተዘግቦአል። ምስራቅ ዩክሬይን ውስጥ ከታገቱት የአውሮጳ የደኅንነት እና የትብብር ድርጅት ታዛቢዎች መካከል ታማሚዉ ሥዊድናዊ ከተወሰኑ ቀናት በፊት ነጻመለቀቃቸዉን ዘገባዉ ያሳያል።

ታግተው የቆዩት የ«ኦኤስሲኢ» ታዛቢዎች በርሊን ሲገቡ

ታግተው የቆዩት የ«ኦኤስሲኢ» ታዛቢዎች በርሊን ሲገቡ

ቡድኑ በታጋቾቹ የተያዘው ስላቭያንስክ ከተማ ዉስጥ ሲሆን ከታዛቢ አባላቱ መካከል አራቱ ጀርመናውያን፣ አንድ ቺቺንያዊ፣ አንድ ፖላንዳዊ፣ አንድ ስዊዲናዊ እና አንድ ዴንማርካዊ ይገኙበታል። ከእዚህም ሌላ አራት የዩክሬይን ወታደሮች አብረው ታግተው ነበር። የስውዲናዊው ታጋች የጤና ሁኔታ ጥሩ ስላልነበር ከባለፈው እሁድ ጀምሮ አጋቾቹ ለቀዋቸው ነበር። ጀርመን እና የአውሮጳ ህብረት ባለፉት ቀናት በተደጋጋሚ ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፒቲን ታዛቢ ቡድኑ እንዲለቀቁ ጥሪ አድርገው ነበር። የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታየን ማየር፤ የታጋጆቹን መለቀቅ አስመልክቶ በሰጡት የቴሌቪዥን መግለጫ፤ ታግተው የነበሩት 12 ሰዎች የጤና ሁኔታ በጥሩ መሆኑን በመግለፅ፤ ለሰዎቹ መፈታት ትልቅ ሚና የተጫወቱትን በሙሉ አመስግነዋል።

የአውሮጳ የደኅንነት እና የትብብር ድርጅት በእንግሊዘኛ ምህፃሩ « ኦኤስሲኤ» ትናንት ከቀትር በፊት ይፋ እንዳደረገዉ በምስራቅ ዩክሬይን ታግተዉ የነበሩት የ«ኦኤስሲኤ» ቡድን ታዛቢዎች ነፃ ተለቀዋል። የቡድኑ ነፃ መለቀቅ ከምንም ነገር ጋር ግንኙነት እንደሌለዉ መፍቀሬ ሩስያ አማፅያን አስታዉቀዋል። የአውሮጳ የደኅንነት እና የትብብር ድርጅት ቃል አቀባይ ታዛቢ ቡድኑ ነፃ እንደተለቀቁ ባሰሙት ንግግር « የወታደራዊ ጉዳይ ታዛቢ ቡድን ነፃ ተለቋል፤ አንድ ልዩ መልክተኛ ነፃ የተለቀዉን ቡድን እስኪቀበል በመጠባበቅ ላይ ነን። ከአንድ ሳምንት በፊት በምስራቅ ዩክሬይን ሰባት የአውሮጳ የደኅንነት እና የትብብር ድርጅት ታዛቢዎችና ሌሎች አምስት ግለሰቦች ለሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን «ኔቶ» ይሰላሉ በሚል መታገታቸዉ ይታወሳል።

የ«ኦኤስሲኢ» ተሽከርካሪ

የ«ኦኤስሲኢ» ተሽከርካሪ

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የዩክሬይን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር አርሴን አዋኮቭ፤ የዩክሬይን የጦር ኃይል በሀገሪቱ የምስራቅ ከተሞች የሚገኙ መፍቀሬ-ሩሲያውያን ላይ ዘመቻውን ማጠናከራቸዉን አስታዉቀዋል። «የሞስኮ ወዳጅ በሆኑት አማፂያን ላይ በካርማቶስክ ከተማ ዘመቻው ቀጥሏል» ብለዋል አማኮቭ ። በእዚህችው ከተማም ተኩስ መከፈቱ ተስተውሏል። እንደ ሚኒስትሩ ከሆነ የመንግሥት ወታደሮች የስለላ ድርጅቱን ህንፃ መልሰው በቁጥጥራቸው ስር አውለዋል። በአቅራቢያው በምትገኝ የስሎቭያንስክ ከተማም ግጭቱ ተጠናክሯል። በአንፃሩ እስካሁን ሰላም በሰፈነባት ኦዴሳ ከተማም ሁኔታው ከሯል። እንደ ፖሊስ ገለፃ አርብ ዕለት ብቻ ቢያንስ 42 ሰዎች በአንድ ህንፃ ላይ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ሞተዋል። ከእሳት ቃጠሎው ጋር በተያያዘ ፖሊስ 130 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

ሚሊዮኖች በሚኖሩባት የዩክሬኗ ኦዴሳ ከተማ ወደ 2000 የሚጠጉ መፍቀሬ-ሩስያውያንና የፀጥታ ኃይላት መጋጨታቸው ተዘግቧል። መፍቀሬ-ሩስያውያኑ ዛሬ ከተማው ውስጥ የሚገኘውን የጦር ዕዝ በመውረር መቆጣጠራቸውንም የዩክሬይን የሀገር ውስጥ ዘገባዎች ጠቁመዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ