ዩክሬን ፤የምሥራቅ ምዕራቦች መሻኮቻ ሀገር | ዓለም | DW | 01.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ዩክሬን ፤የምሥራቅ ምዕራቦች መሻኮቻ ሀገር

ባለፉት አስምስት ወራት ብቻ ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዉ ሞቷል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ተሰዷል።በስንዴ ምርቱ ከዓለም የታወቀዉ ግዛት፤በነፋሻ አየሩ የሚወደደዉ ያ ግዛት እየጠፋ ነዉ።

የሩሲያና የዩክሬን መሪዎች እንደ ወዳጅ እየተጨባበጡ፤ለመደራደር፤ ለማደራደር ቃል እየገቡ እንደ ጦረኛ ወታደሮቻቸዉን ያዋጋሉ። የሞስኮ መሪዎች ጦርቸዉን እያዋጉ የዘመተ ወታደር የለንም ይላሉ። የዋሽግተን፤ ብራስልስ ተሻራኪዎች ሩሲያ ጦር ማዝመቷን እያወገዙ፤ እሩሲያ ድንበር ጥግ ጦር ያሰፍራሉ። እንደ ጦርኛ ጦር እያሰፈሩ እንደ ሠላም ወዳድ ዩክሬንን የሚያብጠዉ ዉጊያ በድርድር መፈታት አለበት ይላሉ።ሩሲያን በማዕቀብ እየቀጡ፤የሩሲያን አፀፋ ያወግዛሉ።ተቃናቃኞቹ የዓለም ሐያላን በርግጥ ፊትለፊት አይዋጉም።ሰላምም አላወረዱም።የሚዘዉሩትን ዓለም ሕዝብን ግን በሠላምና በጦርነት መሐል ያላጋሉ።ምሥራቃዊ ዩክሬንን ያስነድዳሉ።ላፍታ እንዴት ለምን እንበል አብራችሁኝ ቆዩ።

የናትሴ ጀርመን ጦር ፖላንድን መዉረሩን ለመበቀል ብሪታንያና ፈረንሳይ በጀርመን ላይ ጦርነት ካወጁ እነሆ ዛሬ ሰባ-አምስተኛ ዓመቱን ደፈነ። መስከረም 1 1939 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።) «የዓለምና ሁለተኛዉ የተባለዉን» ያን ዘግናኝ ጦርነት በድል አድራጊነት ካተጠናቀቁት እዉቅ የዓለም መሪዎች አንዱ የሶቬት ሕብረቱ ጆሴፍ ስታሊን አንድ አባባል ነበራቸዉ።

« ጠብ ያንዣበበት ሐገር ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር « አሉ፤ አሉ ሐይለኛዉ ጦረኛ ባንድ ወቅት «ዓለም አቀፍ የሠላም ጉባኤ ካልተጠራ ሞቼ እገኛለሁ እያለ ከተሟገተ፤ የዚያች ሐገር መከላከያ ሚላንስትር ለዉጊያ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠርጥር።»

60 ሚሊዮኖችን ያረገፈዉ ጦርነት የተጀመረበት ሰባ-አምስትኛ ዓመት ሊዘከር ዕለታት ሲቀሩት ባለፈዉ አርብ የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ለተማሪዎች ባደረጉት ንግግር የዩክሬን መንግሥት ጦር ምሥራቃዊ ዩክሬን በሚገኙ አማፂያን ላይ የከፈተዉን ጥቃት በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ጦር በሶቬት ሕብረት ላይ ከፈፀመዉ ወረራ ጋር አመሳስለዉታል።የኪየቭና ኪየቭን የሚደግፉት የምዕራብ ፖለቲከኞች ባንፃሩ የፑቲንዋ ሩሲያ ሥለ ዩክሬን የምትከተለዉን ምርሕ ከስታሊኗ ሶቬት ሕብረት መርሕ እርምጃ ጋር ያመሳስሉታል።

በዩክሬን ፖለቲካዊ ቀዉስ ሰበብ ከተካረረ ጠብ የገቡትን የሞስኮ፤የኪየቭ፤የዋሽግተን፤ብራስልስ ፖለቲከኞች የድርጊት ብሒል ተቃርኖን ያስተዋለ ገለልትኛ ታዛቢ ግን የስታሊንን የቆየ ብሒል አለማስታወስ አይችልም።ባለፈዉ ግንቦት ከኪየቭ መዓከላዊ መንግሥት ተገንጥላ የራስዋን አስተዳደር መመስረቷን ያወጀችዉ የዶኔትስክ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር አልክሳንደር ቭላድሚሮቪች ዛሐርሼንኮ የሩሲያ ወታደሮች እሳቸዉ ከሚመሯቸዉ አማፂያን ጎን ቆመዉ ከዩክሬን መንግሥት ጦር ጋር እንደሚዋጉ ባለፈዉ ሐሙስ አስታወቁ።

የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ግን የሩሲያ ወታደሮች ከዩክሬን መንግሥት ጦር ጋር ይዋጋሉ የሚለዉ የምዕራባዉያን ወቀሳም፤ በሞስኮ የሚደገፉት አማፂይንን መግለጫም ተቃረኑ።አርብ።

«ሁሉንም ዓይነት መላ ምት ሥንሰማ የመጀመሪያ ጊዚያችን አይደለም።አንድም ጊዜ ግን የቀረበለን ተጨባጭ ማረጋገጪያ የለም።የሩሲያ ወታደሮችን እንቅስቃሴ የሚያሳይ የሳተላይት ፎቶ ግራፍ አለ የሚል ዘገባ ነበር።በተጨባጭ ግን በኮፒዉተር የተሠራ ጨዋታዎች መሆናቸዉንና ምሥል ከዚያ የተወሰደ መሆኑ ተረጋግጧል።»

የዩክሬኑ ፕሬዝንዳት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ባለፈዉ ማክሰኞ ሚንስክ-ቤሎ ሩስ ዉስጥ ከሩሲያዉ አቻቸዉ ቭላድሚር ፑቲን ጋር በተነጋገሩ ማግሥት ምሥራቃዊ ዩክሬንን የሚያወድመዉን ጦርነት በድርድር ለማስወገድ መስማማታቸዉን አስታዉቀዉ ነበር።

«የሠላም ሂደት እንዲጀመር በሚጥሩት በዩክሬንና በሩሲያ ጦር ሐይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች መካከል የምክክር መርሐ-ግብር ለማዘጋጀት ተስማምተናል።ወደ ጋራ የተኩስ አቁም ሥምምነት የሚደረገዉን ሽግግር ለማፋጠን በሰወስትዮሹ አገኛኝ ቡድን አማካይነት ምክክር እናደርጋለን።ይሕንን የሚቆጣጠረዉ የአዉሮጳ የፀጥታና የትብብር ድርጅት ተልኮ ነዉ።አነሱ (የቡድኑ አባላት) የጋራ የሆነዉ የተኩስ አቁም የመቆጣጣሪና የማጣሪያ መርሐ-ግብራቸዉን እንደሚያቀርቡ ተስፋ አለን።»

ሚንስክ ላይ ሥለሠላም ድርድር ለመናገር-በስታሊን «ሥልት» ዉጪ ጉዳይ ሚንስራቸዉን ያልጠበቁት ፖሮሼኮ ብራስልስ ላይ ተቃራኒዉን ለማለትም መከላከያ ሚንስትራቸዉን አልጠበቁም።በዉጪ ሐይል «ተወረናል» አሉ።በአሸባሪዎች «ተሸብረናል።» ቅዳሜ።

«ለሠላም የተጠናከረ ዓለም አቀፍ ጥረት ቢደረግም እና ከፍተኛ ጉጉት ቢኖረንም ዩክሩን ባሁኑ ሰዓት የዉጪ ወረራና የሽብር ሠለባ ሆናለች።ከነሐሴ ሃያ-ሰባት ጀምሮ ደግሞ በሺ የሚቆጠሩ የዉጪ ወታደሮችና በመቶ የሚቆጠሩ ታንኮች ዩክሬን ግዛት ዉስጥ ሰፍረዋል።ይሕ ለዩክሬን ብቻ ሳይሆን ለመላዉ አዉሮጳ ሠላምና መረጋጋት ሲበዛ አደገኛ ነዉ።»

በምዕራባዉን መንግሥታት የሚደገፉት የዩክሬን ፖለቲከኞች በሕዝብ የተመረጡትን ግን ከሩሲያ የተወዳጁትን የቀድሞዉን የሐገሪቱን ፕሬዝዳት ከሥልጣን አስወግደዉ የኪየቭ ቤተ-መንግሥትን መቆጣጠራቸዉ የጠብ-ዉዝግቡ ሁሉ መነሻ መሆኑን ለማስተንተን፤ የሚፈልግ የምዕራብ ፖለቲከኛ የለም።ካለም አልተሰማም።ክሬሚያ ከዩክሬን ተገንጥላ-ከሩሲያ ጋር የመቀየጧም ሆነ ምሥራቃዊ ዩክሬን የሸመቁ አማፂያን ጠመንጃ የማንሳታቸዉ ሰበብ ምክንያት የያኔዎቹ ተቃዋሚዎች ባለፈዉ ሕዳር ኪየቭ አደባባይ ሲወጡ የተቀጣጠለዉ የሞስኮ፤ዋሽግተን-ብራስልስ የጥቅም ግጭት መሆኑ ግልፅ ነዉ።

ፕሬዝዳንት ፖሮሼንኮ የመላዉ አዉሮጳን ሠላምና መረጋጋት የሚያሰጋ ያሉትን ግጭት ዉዝግብን ሲሆን ከመቀጣጠሉ በፊት፤ ይሕ ቢቀር ከተቀጣጠለ በኋላ ጥቅምን አቻችሎ ለማጥፋት መሞከር የብልሆች ጀግንነት በሆነ ነበር።ግን ለሐያላኑ ግልፁ ሐቅ-ሕቅታ፤ ለሠላም መሆን የነበረበት አለመሆኑ ወይም አለማድረጋቸዉ መኩሪያ የሆነ-ነዉ የመሠለባቸዉ።

ባለፈዉ ማክሰኞ በሚንስኩ ጉባኤ የተካፈሉት የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ወይዘሮ ካትሪን አሽተን ጉባኤዉ ጦርነቱ የሚቆምበትን ብልሐት መቀየሱን አስታዉቀዉ ነበር።

«ለዉይይት በሁለት ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ችለናል።ዉጊያዉ የሚቆምበትን መንግድ ለመፈለግ በጣም ወሳኝ በሆነዉ በሠላምና በፀጥታ ጉዳይና የአዋሳኝ ድንበር አካባቢዎችን ደሕንነት በማረጋገጡ (ላይ)»

የአሽተን የቅርብ አለቃ የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆሴ ማኑኤል ባሮሶም ባለፈዉ ቅዳሜ ሠላማዊ መፍትሔ እንጂ የጦር ፍጥጫ፤ ግጭት፤ ዉጊያ ለማንም አይጠቅመም ነዉ ያሉት።

«እኛ አዉሮጳ ሕብረት ዉስጥ ያለነዉ ከሩሲያ ጋር መጋጨቱን አንፈልገዉም።ሩሲያም ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር የመጋጨቱ ፍላጎት ሊኖራት አይገባም ብዬ አምናለሁ።»

የአዉሮጳ ሕብረት ባለሥልጣናት ቃል ተሰፋ፤ የኪየቭን ቤተ-መንግሥት ለምዕራባዉያን ያደሩት ፖለቲከኞች በተቆጣጠሩበት ወቅት ተስምቶ ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬና ዛሬ የሆነና የሚሆነዉ ባልሆነ ነበር።ይሕ ቢቀር የአዳዲሶቹ የኪየቭ መሪዎች ርምጃ ሩሲያን፣ አዉሮጳ ዉስጥ የነበራትን ተሠሚነትና የምታሳርፈዉን ተፅዕኖ ከፍፃሜዉ የሚያደርስ ነዉ ከሚል ሥጋት ባልዶላት ነበር።ሁለቱም አልሆነም። እንዲያዉም በምዕራባዉያኑ ድጋፍ የተጃገኑት የዩክሬን መሪዎች የሐያል ጎረቤታቸዉን ሥጋት ለማቃለል ከመጣር ይልቅ ቤተ-መንግሥት በገቡ ማግሥት የሩሲያ ዝርያ ላላቸዉ የሐገሪቱ ዜጎች ላቅ ያለ አካባቢያዊ አስተዳደርና በቋንቋቸዉ የመጠቀም መብት የሚፈቅደዉን ነባር ሕግ ሽረዉ በሌላ ለመተካት መሞከራቸዉ የሞስኮዎችን ሥጋት ወደ ቁጣ አናረዉ።

ሩሲያ በሜድትራንያን እና በጥቁር ባሕር ላይ ያላትን ተፅዕኖ ለመጠበቅ የሞስኮ መሪዎች ታሪክን አስታከዉ ክሬሚያን ከግዛታቸዉ ጋር ሲቀይጡ፤ ለሐይል እርምጃ፤ለማዕቀብ አጸፋ ከመሯጥ ይልቅ ዛሬ ከነባሮሶ የምንሰማዉ የሠላማዊ መፍትሔ ሐሳብ ቢሞከር የዛሬዉ ሥጋት ቢያንስ በቀነሰ ነበር።ተቃራኒዉ ነዉ የሆነዉ።ሩሲያ ክሪሚያን ለመያዝ አንድ ሁለት ሥትል ዩናዩትድ ስቴትስ፤ ፈረሳይ፤ ታላቋ ብሪታንያ፤ ካናዳ፤ ኋላ ጀርመን፤ስዊድን፤የዴንማርክና ቼክ ሪፕብሊክ ሳትቀር ተዋጊ ጄቶቻቸዉን፤ የጦር መርከቦቻቸዉን እና ወታደሮቻቸዉን ለማስፈር ነበር የተጣደፉት።

ምዕራባዉያኑ ሐገራት ሲሻቸዉ በተናጥል፣ ሲፈልጋቸዉ በሠሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ( ኔቶ) ሥም ፖላንድ፤ሊትዌንያ፤ ኢስቶኒያ፤ሮሜንያና ቡልጋሪያ ዉስጥ ባሰፈሩት ጦር፤ተዋጊ ጄት፤መርከብና ሚሳዬል የሩሲያን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በቅርብ ርቀት እየተከታተሉ ነዉ።ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ዩናይትድ ስቴትስ፤ የሩሲያ ምሥራቃዊ ዩክሬን ዉስጥ የምታሠራጨዉን ፕሮፓጋንዳ ለማምከን፤የዩክሬን ጦር የመገናኛ ዘዴን ለማጠናከር እና የሩሲያን ሠርጎ ገብ ወታደሮች እንቅስቃሴ ለመጠቆም የሚረዱ ሥልጠናዎችንና መሳሪያዎችን ለዩክሬን መስጠት የጀመረችዉ ከሚያዚያ ማብቂያ ጀምሮ ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በቀደም እንዳሉት ግን ሩሲያ በአሜሪካኖችና በተባባሪዎቻቸዉ የሚረዳዉን የዩክሬንን መንግሥት የሚወጉትን አማፂያንን በመደገፏ ዉግዘትና ቅጣቱ ሲያንስ ነዉ።

«ተገንጣዮቹ በሩሲያ የሠለጠኑ፤ በሩሲያ የታጠቁ፤ በሩሲያ ገንዘብ የሚደገፉ ናቸዉ።ሩሲያ ሆን ብላ እና በተደጋጋሚ የዩክሬንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ጥሳለች።የሩሲያ ወታደሮች ዩክሬን ዉስጥ መግባታቸዉን የሚያሳየዉ አዲሱ ምሥል ደግሞ ዓለም ሁሉንም በግልፅ እንዲያዉቀዉ ያደርጋል።»

ዓለም አዉቆ-የሚያደርገዉ ወይም ለማድረግ የሚችለዉ ካለ-የሚያዉቀዉ ሁሉንም ነዉ።ያም ሆኖ የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከምዕራባዉያን መንግሥታት ለሚሠነዘርባቸዉ ወቀሳ ትችት አፀፋ በመሠለ መግለጫቸዉ ልክ እንደ እስከ ትናንቱ ሁሉ ትናንትም፤ «ድርድር» ብለዋል።

«ቴክክኒካዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን ምሥራቃዊ ዩክሬን የሚኖረዉን ሕዝብ ፍላጎት ለመጠበቅ የማሕበረሰቡን ፖለቲካዊ ድርጅትና የአስተዳደር ጉዳይን ጭምር የሚዳስስ ፍሬያማና ትርጉም ያለዉ ድርድር ባስቸኳይ መጀመር አለበት።»

ተሰናባቹ የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆሴ ማኑኤል ባሮሶ እንዳሉት ምዕራባዉያንም ሩሲያም ቀጥታ ግጭት ጦርነቱን አይፈልጉት ይሆናል።ዓለም ግን ካጠቃላዩ የዓለም ሕዝብ 2,5 ከመቶ የሚበልጥ (ከሥልሳ ሚሊዮን በላይ) ሕዝብ ያለቀበትን ጦርነት አጀማመርን በሚዘክርበት ባሁኑ ወቅት ከሌላ የጦርነት ሥጋት እንደዶሉት ነዉ።

የምሥራቅ ዩክሬንን ሕዝብ እያስገደሉ፤ እያሰደዱት ነዉ።ባለፉት አስምስት ወራት ብቻ ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዉ ሞቷል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ተሰዷል።በስንዴ ምርቱ ከዓለም የታወቀዉ ግዛት፤በነፋሻ አየሩ የሚወደደዉ ግዛት እየጠፋ ነዉ።

«ቤቴ ወድሟል።በሆነ መንገድ መገንባት አለብኝ።ገንዘብ የማገኘዉ አነዚሕ ዉድቅዳቂ ብረቶችን በመሸጥ ነዉ።ሌላ ምን አደርጋለሁ።ሁሉም ነገር ወድሟል።ሥራም የለም።»

ይላሉ ከሞት ስደት ከተረፉት አንዱ። የአሽተን ዲፕሎማሲ፤የባሮሶ የድርድር ሐሳብ ከዘገየ፤ የፑቲንም የድርድር መልዕክት በርግጥ አርፍዷል።ለሠላም ካሰቡ ግን የዉይይት ድርድሩ መፍትሔ ዘገየ እንጂ-ጨርሶ አልቀረም።ረፈደ እንጂ አልመሸም።ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች