ዩክሬንና የአውሮፓ ህብረት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 10.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ዩክሬንና የአውሮፓ ህብረት

የዩክሬን መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ጋር ከዚህ ቀደም የተስማማበትን ልዩ የንግድና የፖለቲካ ውል ለጊዜው አልፈርምም ማለቱን የሚቃወሙ ኃይላት የጠሩት የአደባባይ ሠልፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል ። ሃገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ግንኙነቷ እንዲጠብቅ የሚፈልጉ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎቻቸውና የአውሮፓ መንግስታት የመንግስትን እርምጃ እያወገዙ ነው ።

መንግሥት በበኩሉ ውሉ ከመፈረሙ በፊት ከሩስያ ጋር የምማከርበት ፋታ ስጡኝ እያለ ነው ። ሩስያ ደግሞ የአውሮፓ መንግሥታት በዩክሬን ውሳኔ ጣልቃ መግባት የለባቸውም ስትል ታሳስባለች ። የአውሮፓ ህብረትና ሩስያ ዩክሬንን ወደ ራሳቸው ለመሳብ በየበኩላቸው የሚያካሂዱት ትግልና ከሁለት ወገን የተወጠረችውን የዩክሬን ወቅታዊ ሁኔታ የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ። ለቅንብሩ ኂሩት መለሰ
ካለፉት 2 ሳምንታት ወዲህ የዓለምን ትኩረት የሳበችው ምሥራቅ አውሮፓዊቷ አገር ዩክሬን የ46 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ ናት ። በዓለም ባንክ መመዘኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ ትመደባለች ። ከህዝቧ 77.8 በመቶው ዩክሬናውያን ፣ 17 በመቶው ሩስያውያን የተቀሩት ደግሞ ቤላሩሳውያንና ሮሜንያውያን ናቸው ። በቆዳ ስፋትዋ ከአውሮፓ ትልቁን ስፍራ ትይዛለች ። 603,628 ስኩዌር ኪሎሜትር የቆዳ ስፋት አላት። በስተምሥራቅና በስተሰሜን ምሥራቅ የሩስያ ፌደሬሽን ፣በሰተሰሜን ምዕራብ ቤላሩስ ፣በስተምዕራብ ፖላንድ ስሎቫክያና ሃንጋሪ፣ በስተደቡብ ምዕራብ ፣ ሮሜንያና ሞልዶቫ ፣በስተደቡብና በስተደቡብ ምሥራቅ ደግሞ ጥቁር ባህርና የአዞቭ ባህር ያዋስኗታል ። የዩክሬን ሶሻሊስት ሪፐብሊክ እጎአ 1922 የቀድሞዋን ሶቭየት ህብረት ከመሠረቱት ሪፐብሊኮች አንዷ ናት ። በ1941 በናዚ ጀርመን ተወራ በሩስያ ጦር ድጋፍ በ1944 ነፃ ብትወጣም ። በጦርነቱ አሸናፊ ሶቭየት ህብረት ስር ከመሆን አላመለጠችም ።

Ukraine Protest Regierung EU Spezialeinheit

ተቃውሞ በዩክሬን

ሶቭየት ህብረት እጎአ በ1991 ስትፈረካከስ ግን ራስዋን የቻለች አገር ሆነች ። ዩክሬን ከዚያን ጊዜ አንስቶ የነፃ ኤኮኖሚ መርህ ታራምዳለች ። ለም መሬት ያላት ዩክሬን የእህል ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ 3 ተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሃገር ናት ። ዩክሬን በእርሻ ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ ምርቶቿም ታዋቂ ሃገር ናት ። ልዩ ልዩ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችና ከባድ የጭነት መኪናዎች ግዙፉ የመንገደኞችና የእቃ ማመላለሻ አውሮፕላን አንቶኖቭም ይመረትባታል ። ከአውሮፓ ከሩስያ ቀጥሎ በወታደራዊ ኃይል ሁለተኛን ደረጃን የምትይዝም ሃገር ናት ። የአብዛኛዎቹ ምርቶቿ ገበያ አውሮፓ ነው ። ሃገሪቱ የሚያስፈልጋት የኃይል አቅርቦት በተለይ የነዳጅ ዘይት ና የተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታዋ በአብዛኛው የሚገኘው ከሩስያ በመሆኑ የሞስኮ ጥገኛ ናት ። 25 በመቶ የተፈጥሮ ጋዝ ከሃገር ውስጥ ስታገኝ ፣35 በመቶውን ከሩስያ የተቀረውን 40 በመቶው በሩስያ በኩል ከመካከለኛው እስያ ሃገራት ታስገባለች ። በሌላ በኩል ሩስያ ለምዕራብ አውሮፓ ከምታቀርበው የተፈጥሮ ጋዝ 85 በመቶው የሚያልፈው በዩክሬን በኩል ነው ። በኢንዱስትሪና በእርሻ ምርቷ የምትታወቀው ዩክሬን መሰረተ ልማትዋ የሚፈለገውን ያህል ያልዳበረ በሙስናና በቢሮክራሲ ስሟ የሚነሳም ሃገር ናት ።

ከ4 ዓመት በፊት ነበር የአውሮፓ ህብረት ፣ዩክሬንን ጨምሮ ከምስራቅ አውሮፓዎቹ አገራት ከአርሜንያ ። ከአዘርባጃን ከጆርጅያ ከሞልዶቫና ከቤላሩስ ጋር የጋራ ስምምነት የመዋዋል ሃሳብ ያቀረበው ። እነዚህ ሃገራት ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች ካደረጉ ህብረቱ በለውጡ ከሃገራቱ ጋር ነፃ ንግድ ለማካሄድና ና የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገባላቸው ። የታቀዱት አጋርነቶች ልዩ የትብብር ስምምነቶች የህብረቱን አባልነት ሳይጨምር ዜጎች ያለ ቪዛ ወይም መግቢያ ፈቃድ እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል ፣ ቀረጥ ወይም ግብርን መቀነስን እንዲሁም የአውሮፓውያን ስነ ምግባሮች ተግባራዊ ማድረግን ይመለከታሉ ። በይፋ ባይገለፅም የህብረቱ ሌላው ዓላማ ሩስያ በምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት ላይ ያላትን ጫና ለመገደብ ያሰበ ና ሕብረቱም ወደ ምሥራቅ ምን ያህል እንደሚስፋፋ የሚያስቀምጥ ነበር ። በእቅዱ መሠረት በጎርጎሮሳውያኑ ህዳር 29 ያኑኮቪች 900 ገፅ

Ukraine Vertrauensabstimmung Klitschko 03.12.2013

ክሊትችኮ

ያለውን ውል በወቅቱ የአውሮፓ ህብረት ሊቀመንበር በሊትዌንያ ዋና ከተማ ቪሊንዩስ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ሊፈራረሙ ቀጠሮ ተይዞ ነበር ። ይሁንና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች በጎርጎሮሳውያኑ ህዳር 21 ከዚህ ቀደም ቃል የገቡለትን የስምምነቱን ፊርማ ላልተወሰነ ጊዜ ማስተላለፋቸውን አስታወቁ ። የያኑኮቪች ውሳኔ ዩክሬን ከአውሮፓ ህብረት ጋር እንድትቀራረብ የሚፈልጉትን ወገኖች አስቆጥቶ ለተቃውሞ አደባባይ አስወጣ ። ተጠናክሮ በቀጠለው ተቃውሞ አዲስ መንግሥት እንዲመሰርት የሚቀርበው ጥያቄ ቀጥሏል ። ዩክሬን ወደፊት የአውሮፓ ህብረት አባል የምትሆንበት መንገድ እንዲመቻች የሚፈልጉት እነዚሁ ወገኖች ወደ ውህደቱ የሚደረገው ጉዞ ያለ ፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች መንግሥት እንዲሆን ጥያቄአቸውን ማቅረብ የጀመሩት ገና ከጅምሩ አንስቶ ነው ።
«ካቢኔው ከሥልጣን መውረድ አለበት በምጣኔ ሃብቱም ቢሆን አዲስ ህይወት መጀመር አለብን ። »
«መንግሥት ከሥልጣን ይወርዳል ብለን እንጠብቃለን ። እናሸንፋለን ምክንያቱም ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ መጨረሻው እዚህ እንቆያለን ። እናሸንፋለን ብዬ አስባለሁ ። የአውሮፓ አካል መሆን እንፈልጋለን አውሮፓም ይረዳናል ።»
«መንገዱን በሙሉ መዝጋት ይኖርብናል ። አንድም ባለሥልጣን ወደ ሚኒስትሮች ካቢኔ ቢሮ እንዳይገባ ለማድረግ ከበስተኃላችን ያለውን መንገድ መዝጋት አለብን ። »
«ወንጀለኛውን ፕሬዝዳንት እቃወማለሁ ። በቴሌቪዥን 3200ህሪቭንያስ የዩክሬን ገንዘብ 388 ዶላር እንደምናገኝ ይናገራሉ ። ልነግርህ እችላለሁ ማንም ይህን ያህል ደሞዝ አያገኝም ። በየክፍለ ሃገሩ ህዝቡ የሚላስ የሚቀመስ የለውም ። »
በዋና ከተማይቱ ክየቭ ከሚገኘው ማድያን ከተባለው የነፃነት አደባባይ አንስቶ በሌሎችም ከተሞች ተቃውሞው በዚህ መልኩ ቀጥሎ በሳምንቱ መጨረሻ ተቃዋሚዎች የሌኒን ሐውልት እስከማፍረስ ደርሰዋል ። የዓለም የከባድ ሚዛን ቦክስ ሻምፕዮንና ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቪታሊ ክሊችኮ እንደሚለው ህዝቡ በአደባባይ ተቃውሞውን ለመግለፅ የወጣው በዩክሬን ሁኔታዎች ከድጡ ወደ ማጡ እየሆኑ በመሄዳቸው ነው ።

EU Gipfel Litauen Janukowitsch Barroso Van Rompuy 28.11.2013

ባሮሶ ቫን ሮምፖይና ያኑኮቮች


« ህዝቡ በየጎዳናው የወጣው ቅር ስለተሰኘ ነው ። መንግሥት ይቀያየራል ፤ ሚኒስትሮችም ይለዋወጣሉ ። ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ግን አልተለወጠም ። ይልቁንም እየተባባሰ ነው የሄደው ። ሙሰኝነት ስርዓት አልበኛነት ተባብሷል ።ስርዓቱን መለወጥ አለብን ። »
ተቃዋሚዎች ይህን ሲሉ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ያኑኮቪች ግን ውሳኔዬ ሃገሬን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም ሲሉ ለማግባባት እየሞከሩ ነው ።
« ወደ ተወሳሰቡ ውሳኔዎች ላይ መድረስ ግድ ይለኛል ። ለዚህም ነው አንዳንዴ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱኝ የሚያደርጉ ውሳኔዎችን ለመውሰድ የምደፍረው ። ለዚህም ነው ዛሬ ህዝባችን በጥንቃቄ እንዲያደምጠኝ የምጠይቀው ። ዩክሬንና ህዝቦችዋን የሚጎዳ አንድም እርምጃ ፈጽሞ አልወስድም ። »
ከአውሮፓ ህብረት ጋር የትብብር ውል ይፈርማሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት ያኑኮቪች ውሳኔያቸውን ያስቀየሯቸው የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መሆናቸው ነው የሚነገረው ።ዩክሬን በምዕራባውያኑ እጅ ውስጥ እንዳትወድቅ ከፍተኛ ትግል የሚያደርጉት ፑቲን በጎሮጎሮሳውያኑ ህዳር 9 2013 ዓም ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች ጋር ሞስኮ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ወታደራዊ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ተገናኝተው ያካሄዱት ንግግር ያኑኮቪች ውሉ ከመፈረም እንዲያዘገዩ አድርጓቸዋል ነው የሚባለው ። ሰሞኑን ቻይናን የጎበኙት ያኑኮቪች ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ እግረ መንገዳቸውን በሩስያዋ የሶቺ ከተማ ከፑቲን ጋር መክረዋል ። ያኑኮቪች እስካሁን ከሁሉም ወገን የተሻለ ስምምነት እየጠበቁ ነበር ። ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ስምምነት አሁን ለመፍረሱ በይፋ የሚሰጠው ምክንያት የቀድሞዋ የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዩልያዋ ቲሞሼንኮ ከእስር አለመለቀቅ ነው ። የአውሮፓ ህብረት የቲሞሼንኮን መለቀቅ እንደ ቅድመ ግዴታ አስቀምጧል ። ያኑኮቪች ደግሞ የቀድሞዋን ተቀናቃኛቸውን ለመፍታት አልፈለጉም ። ባለፈው ሳምንት የተሰበሰበው የሃገሪቱ ፓርላማም ቲሞሼንኮ እንዲለቀቁ የሚጠይቀውን ረቂቅ ህግ አላፀደቀም ። ከዚህ በላይ ግን ዩክሬን ከህብረቱ ና ከሩስያ በኩል ቃል የተገባላት የገንዘብ ማማለያዎች ወሳኝ ድርሻ ነበራቸው ። እዳ ለተቆለለበት ለዩክሬን ፑቲን በድጎማ መልክ በቢሊዮኖች ዮሮ የሚቆጠር ገንዘብ ለመስጠት እዳዋንም ለመሰረዝ እና እቃዎቿንም ከቀረጥ ነፃ እንድታስገባ ቃል ገብተውላታል ። የአውሮፓ ህብረት ደግሞ ወደ 610 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 827 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ነው ያቀደው ። ከዚሁ ጋር የዓለም የገንዘብ ድርጅት በምህፃሩ IMF የ1 ቢሊዮን ዩሮ ያልተረጋጠ የብድር ተስፋ ሰጥቷት ነበር ። የዩክሬን መሪዎች ከዚህኛው ይልቅ የሩስያው ቃል ስቧቸዋል ።

Julia Timoschenko im Gefängnis in Charkow

ቲሞቼንኮ እስር ቤት ውስጥ

ተንታኞች እደሚሉት ለሩስያ ዩክሬንን መያዝ ጂኦ ፖለቲካዊ ተፅእኖ ማድረግ መቻል ብቻ ሳይሆን ከብዙ ዓመታት በፊት የሩስያ ግዛት እምብርት የነበረችውን ሃገር መቆጣጠር ማለት ነው ። የአውሮፓ ህብረትና ሩስያ በሚቋምጡላት በዩክሬን ሰበብ ብራስልስና ሞስኮ ከ23 ዓመታት በፊት የነበረውን ዓይነት የቀዝቃዛው ጦርነት ስሜት ውስጥ የገቡ ይመስላል ። ለሰሞኑ ተቃውሞ መንግስት የወሰደውን እርምጃ ህብረቱና አባላቱ እየተቃወሙት ነው ። ከዚሁ ጋርም መንግሥት ውሳኔውን እንደገና ያጤነዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው እያሳወቁ ነው ። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆሴ ማኑዌል ባሮሶ ።
«የዩክሬን ባለሥልጣናት ዲሞክራሲያዊ ነጻነቶችንና ሰልፍ የማድረግ መብቶችን እንዲያከብሩ በግልፅ ተናግረናል ። ከዚሁ ጋርም ተቃዋሚ ሰልፈኞች ከኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበናል ። ርግጥ ነው ይህ የሆነው ብዙዎቹ ዩክሬናውያን ወደፊት ከአውሮፓ ጋር መዋሃድ የሚፈልጉ በመሆናቸው ነው ። በቪሊኑሱ ጉባኤ ቅር በመሰኘታቸው ነው ። ሆኖም ውይይቱ ይቀጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ።
«
ባለፈው ሳምንት ክየቭ የሄዱት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርለም የአውሮፓ ህብረት አሁንም ዩክሬንን እጆቼን ዘርግቶ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል ። ቬስተርቬለ እንዳሉት ዩክሬን ስምምነቱን ብትቀበል ተጠቃሚ ናት
ድምፅ
ቬስተርቬለ በኪቭ ጉብኝታቸው ተቃዋሚዎች በተሰበሰቡበት አደባባይ ተገኝተው ነበር ። መንግሥታት በዩክሬን ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ሩስያ ማሳሰቢያ እየሰጠች ነው ። ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ዩክሬን ጥገኛዋ መሆኗን ለማስረገጥ ሩስያ ልዩ ልዩ እርምጃዎች ወስዳባታለች ። 3 ጊዜያት የተፈጥሮ ጋዝ በማቋረጥ ኃይሏን አሳይታታለች ። አልፎ አልፎ የሩስያ ምርቶች እንዳይገቡም ማገዷ አልቀረም ። ዩክሬን ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ምርት አንድ ሶስተኛው ወደ ሩስያ የሚላክ ሲሆንወደ አውሮፓ ህብረት የምትልከው ደግሞ 25 በመቶ ብቻ ነው ። በነዚህ ምክንያቶች ዩክሬን ወደ ሩስያ ያደላች ይመስላል ። ከአውሮፓ ህብረት ጋር የምትፈራረመው ውል ለአንድ ዓመት እንዲዘግይ አድርጋለች ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው ዩክሬን የታሰበውን ውል ወደፊት መፈረሟ አጠራጣሪ ቢመስልም ህብረቱን ግን ምን ጊዜም በሩን ክፍት አድርጎ እንደሚጠብቃት ነው ያሳወቀው ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic