ዩኤስ አሜሪካ ሀቫና ኩባ ኤምባሲ ከፈተች | ዓለም | DW | 14.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ዩኤስ አሜሪካ ሀቫና ኩባ ኤምባሲ ከፈተች

የዩኤስ አሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ዛሬ ለታሪካዊ ጉብኝት ኪውባ መዲና ሀቫና ገብተዋል። ኬሪ ከ 54 ዓመታት በኋላ በሀቫና ባለው ሜልኮ የባህር ወሽመጥ ዳርቻ የሚገኘዉ የዩኤስ አሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ ዳግም በሚከፈትበት እና የሃገራቸው ሰንደቃላማ ከፍ ብሎ በሚዉለበለብበት ሥነ-ስርዓት ላይ ለመገኘት ነው ወደዚያ የተጓዙት።

ጆን ኬሪ ከጎርጎረሳዊዉ 1945 ዓ,ም ወዲህ የኮሚኒስት መርህን የምትከተለዉን ኪውባን የጎበኙ የመጀመርያዉ የዩኤስ አሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሆናቸዉ ነዉ። ኬሪ በሃቫና ቆይታቸው ከኪውባ አቻቸዉ ቡርኖ ሮድሪገዝ ጋር በሚያደርጉት ውይይት፤ ስለ ኪውባ የሰብዓዊ መብት ይዞት እና ዩኤስ አሜሪካ በካሪቢኳ ሃገር ላይ የጣለችዉ ማዕቀብ ስለሚነሳበት፣ እንዲሁም፣ ከኪዩባ ጋር ስለተቋረጠዉ የንግድ ግንኙነት ጉዳይ እንደሚያነሱ ተገልጾዋል።

በሌላ በኩል ኬሪ በኪውባ ከሚገኙ ተቃዋሚዎች ጋር እንደሚገናኙም ይጠበቃል።

ኪውባና ዩኤስ አሜሪካ ግንኙነታቸውን ከአምስት አሰርተ ዓመታት በላይ ካቋረጡ በኋላ ሐምሌ 13፣ 2007 ነበር ዳግም ዲፕሎማስያዊ ግንኙነትን የጀመሩት። ይህ የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና የኪውባው ፕሬዚዳንት ራዉል ካስትሮ ባለፈዉ ታሕሳስ ወር መቀራረብ ከጀመሩ በኋላ የተወሰደ ትልቁ ርምጃ መሆኑን ተያይዞ የደረሰን ዜና አመልክቶዋል።

የዩኤስ አሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና የኩባዉ ፕሬዚዳንት ራዉል ካስትሮ የሁለትዮሽ ዉይይት የሃገራቱን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገሩ መገለጩ ይታወሳል። የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ፓናማ ላይ በሚካሄደዉ የአሜሪካ ጉባኤ ላይ ፊት ለፊት ተገኛኝተው መነጋገራቸው ታሪካዊ ክስተት ነዉ ሲሉ የአሜሪካኑ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ተናግረዉ ነበር።

እንድያም ሆኖ ኦባማ ሁለቱ ሃገሮች እጅግ የሰፋ ልዩነት እንዳላቸዉ ሳይናገሩ አላለፉም። የኩባዉ ፕሬዚዳንት ራዉል ካስትሮ በበኩላቸዉ ሃገራቸዉ ስለሁሉም ነገ ለመወያየት ዝግጁ መሆንዋን ነገር ግን እጅግ ትዕግስት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዉ ነበር። ከጎርጎረሳዊዉ 1959 የኩባዉ ሶሻሊስት አብዮት በኋላ የዋሽንግተኑና የሃቫናዉ መንግሥት በጠላትነት ሲተያዩ መቆየታቸዉ ይታወቃል። ከባለፈዉ የጎርጎረሳዊ ዓመት 2014 ዓ,ም ጀምሮ ሁለቱ ሃገራት ለአንድ ዓመት ተኩል ከዘለቀ ምስጢራዊ ድርድር በኋላ አዲስ ግንኙነት መጀመራቸዉን ይፋ ማድረጋቸዉ ይታወሳል።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ