ዩናይትድ ስቴትስና የዓለም ፀጥታ | ዓለም | DW | 20.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ዩናይትድ ስቴትስና የዓለም ፀጥታ

የብራስልስ፤ቦን፤ ሙኒኩ ስብሰባ ጉባኤ የነባሮቹን ወዳጅ ሐገራት ግንኙነት ወትሮዉ እንደነበረዉ እንደሚቀጥል፤ የምዕራባዉያንና የሩሲያ ጠብ እንደሚረግብ ተስፋ ሰጥተዋል።ቀጣይነቱ ግን በርግጥ ያጠያይቃል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:20

የዩኤስ አሜሪካ መርህ እና የዓለም ፀጥታ

የዩናይትድ ስቴትስ አዲስ መስተዳድር አዳዲስ ሹማምንት እንደ አዲሱ መሪያቸዉ ሳይሆን እንደ ብዙ ቀዳሚ መሪ-አቻዎቻቸዉ ለማድረግ ተናገሩ።ቃል ገቡም።በአዲሱ የአሜሪካ መሪ አዲስ መርሕ፤ እንግዳ ንግግር የተደናገጡት የምዕራብ አዉሮጳ፤ የአረብ እና እስያ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ፤ የጦር-ዲፕሎሲ ኃላፊዎች «ተንፈስ» አሉ።በአዲሱ የአሜሪካ መሪ  መርሕ፤  መልዕክት ተደስተዉ የነበሩት የሩሲያ ሹማምንት ተስፋ ተጠናከረ።የአዲሱ የሜሪካ መሪ ትችት ዘለፋ ቻይኖችን አስኮረፎ ነበር።የአዳዲሶቹ የአሜሪካ ሚንስትሮች ነባር ቃል ግን አፅናናቸዉ።ሰዉዬዉ ግን እንደገና ዓለም አስደነገጡ።ሳምንቱም አበቃ።የሳምንቱን ንግግር ቃል ምንነት፤ ከቀዳሚዉ ከመለየቱ እንዴትነት ጋር፤ የእፎይታ፤ተስፋ፤መፅናናቱን ምክንያት፤ ከቀጣይነቱ አጠያያቂነት ጋር አሰባጥረን እንቃኛለን። 

                          

ሰዉዬዉ በምርጫ ድል ማግሥት የፕሬዝደትነቱን ሥልጣን ከያዙ ወር ደፈኑ።ቅዳሜ ግን  የምርጫ ዘመቻ ላይ ነበሩ።ፍሎሪዳ።መራጭ፤ ተከታይ፤ አድናቂዎቻቸዉ ያጨበጭባሉ፤ይጨፍራሉ፤ ይዘምራሉ።መሪያቸዉን ያሞግሳሉ።«ሐገራችንን አስተማማኝ ማድረግ አለብን» አሉ የዓለም ብቸኛ ልዕለ ሐያል ሐገር ፕሬዝደንት።

                           

«ይሕ ነዉ ዋናዉ ቁም ነገር።ሐገራችን ለጥቃት እንዳትጋለጥ መጠበቅ አለብን።የሚሆነዉን ተመልከቱ»

«ጀርመን የሆነዉን ተመልከቱ» ቀጠሉ የዓለም ምርጦ ጦር ጠቅላይ አዣዥ ዶናልድ ትራምፕ።«---ትናንት ማታ ስዊድን የሆነዉን ተመልከቱ---» አከሉ የዓለም ቁጥር አንድ የኑክሌር ቦምብ አከማች ሐገር መሪ ዶናልድ ትራምፕ።«የጀርመን የሚሆነዉን ተመልከቱ።ትናንት ማታ ስዊድን ዉስጥ የሆነዉን ተመልከቱ።ስዊድን፤ ማን ያምናል።ስዊድን።ብዙ ቁጥር ያለዉ (ስደተኛ) ተቀብለዉ ይሆናል ብለዉ ፍፁም ያላሰቡት (ሆነ) »

ምን ሆነ? ዓለም ጠየቀ።አርብ ማታ «ምን ሆነ?» ስዊድኖች ደነገጡ።ግን ከዓለም ታላቅ፤ ልዕለ ኃያል፤ ሐብታም ሐገር ሐብታም መሪ በላይ ሲዊድኖች ሥለ-ሲዊድን እንዴት ሊያዉቁ ይችላሉ? ትራምፕ ጋዜጠኛ እንዳይጠይቃቸዉ ሰዉዬ ጋዜጠኛ ይሳደባሉ።ሊያዉስ የት ተገኝተዉ።ቢሆንም ሲዊድኖች ጠቅላይ ሚንስራቸዉን ጠየቁ።ጠቅላሚንስትር ስቴፋን ሎፍቭን በዋሽግተን የሐገራቸዉን አምባሳደር ከመጠየቅ ሌላ ምርጫ አልነበራቸዉም።

የትራምፕ ንግግር ምክንያት አርብ ማታ በቴሌቪዥን ያዩት ዘጋቢ ፊልም ነዉ ተባለ።ጋዜጠኛ ይሳደባሉi፤ ጋዜጠኛ የዘገበዉን ያያሉ።ባንድ ወቅት አንድ የቴሌቪዥን ዝግጅት ይመሩ ነበር።ሥለ የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልም እና እዉነታን ግን አይለዩም።ዓለምን ይመራሉ።አድናቂ፤ አወዳሾቻቸዉን ያስጨፍራሉ፤ ያዘምራሉ።ያስደነግጣሉም።

                                

ዶናልድ ትራም። ጉደኛ መሪ።አሜሪካ ድንቅ ሐገር።የካፒታሊስት ኮሚኒስት ኃያላን በአዉቶሚክ  ቦምብ  ለመደባደብ በሚዛዛቱበት በ1960ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ብሪታንያዊዉ ፈላስፋ በርትራንድ ረስል ጀምረዉት የዓለም የፀረ-ኑክሌር ኃይላት ደጋግመዉ የሚናገሩት አባባል ነበራቸዉ።«የዓለም ሕዝብ መኖር አለመኖር የሚወሰነዉ በሊንደን ጆንሰን፤ በኒኪታ ኽሪሽቾቭ፤ ወይም በማኦ ዜዶንግ መልካም ፈቃድ ነዉ።» የሚል ዓይነት።እርግጥ ነዉ የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እንዳሉት ዓለምን በሚያወድም የኑክሌር ቦምብ ለመጠፋፋት ይዛዛቱ የነበሩት መንግሥታት ከቬትናም እስከ አንጎላ፤ ከላኦስ እስከ ቺሊ በተዘዋዋሪ ተቀናቃኞችን ያዋጉ፤ሕዝብ ያጫርሱ እንጂ ፊት ለፊት ተጋጭተዉ አያዉቁም።

                            

«ከዩ ኤስ ጋር ምን አይነት ግንኙነት ነዉ የምንፈልገዉ?ገቢራዊ ግንኙነት፤መከባበር፤ ለዓለም መረጋጋት ልዩ ኃላፊነት ያለብን መሆኑን መገንዘብ።ሐገሮቻችን ቀጥታ ተጋጭተዉ አያዉቁም።ይሕ እዉነት ነዉ።ከግጭት ፍጥጫ ይልቅ የወዳጅነት ግንኙነት ታሪክ ነዉ ያለን።»

ላቭሮቭ

እንዳሉት ሞስኮዎች ዛሬም እንደጥንቱ የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅ ከዋሽግተኖች እኩል ልዩ ኃላፊነት አለብን ብለዉ ያስቡ ይሆናል።በ1990ዎቹ ሶቬት ሕብረት ከተፈረካከሰች ወዲሕ «ዓለም አድም ከኛ ዓአለያም ከጠላቶቻችን እያሉ የሚያስፈራሩ፤ ከሰርቢያ እስከ አፍቃኒስታን፤ከሶማሊያ እስከ ኢራቅ፤ ከሊቢያ እስከ ሶሪያ ባሻቸዉ ወቅት ያሻቸዉን የሚያደርጉት ዋሽግተኖች እና ወዳጆችዋ ለመሆናቸዉ አብነት መጥቀስ ጅልነት ነዉ።ዓለም ለሰላሙ ይሁን ለጥፋቱ፤ ለቀለቡ ይሁን ለረሐቡ፤ ለስደቱ ይሁን ለሐብቱ፤ ለሹመቱ ይሁን ለሽረቱ፤ ለሙዚቃዉ-ይሁን ለፊልሙ፤ ለጌጡ ይሁን ለፋሽኑ አንጋጥጦ የሚያዉ፤ የዚያች ሐገር መሪ፤ፖለቲከኛ፤ቱጃሮች የሚሉ የሚያደርጉት ለማወቅ የሚጓጓዉም አለምክንያት አይደለም።

የአዲሱ መሪ አዲስ  መልዕክት ብዙዉን ዓለም  ግራ-አጋብቶ፤ ሲዊድኖችን አስደንግጦ፤ ብልሆችን ዳግም ያነጋገረበት ያለፈዉ ሳምንት ለአዉሮጳ-አሜሪካ፤ ለእስያ፤ ለአረብ እስራኤል ኃያል፤ ሐብታም መንግስታት ፖለቲከኛ፤ ዲፕሎማት የጦር አዛዞች አባታይ ሳምንት ነበር።እርግጥ ነዉ የአሜሪካና የእስራኤል መሪዎች ጉባኤ፤ የአስታና-ኻዛክስታን የሶሪያ ድርድር፤ ሌሎችም ስብሰባ-ጉባኤዎች ነበሩ።

ዋንኞቹ ግን ሰወስት ናቸዉ። የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሐገራት የመከላከያ ሚንስትሮች ስብሰባ።የቡድን 20 አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ እና የዓለም የፀጥታ ጉባኤ።የካፒታሊስቱ ሥርዓት ተቃዋሚዎች፤ ጋዜጠኞች፤  የጀርመን እና የቤልጂግ የፀጥታ ሐይሎች፤ሰላዮች፤ አጃቢዎች፤አስተናጋጆችም እንደ መሪ ሚንስትሮቻቸዉ ሁሉ ሲባትሉ ነዉ የሰነበቱት።ስብሰባ ጉባኤዎቹ ሰወስት ናቸዉ እንዳልነዉ ሁሉ አንድም ናቸዉ። አንድም ሰወስትም።ብዙዎቹ ጋዜጠኞች፤ ተሰብሳቢ ጉባኤተኞች  የዓለም ሕዝብ ጭምር ትኩረት፤ ጥያቄ ና ጉጉትም አንድም ብዙም ነዉ።አዳዲሶቹ የሜሪካ ሹማምንት «ምን ይሉ ይሆን?» ጥያቄዉን የብዙዎች የሆነበት ምክንያት እንደየሰዉ፤ እንደ ሐገር፤ ፓርቲዉ ይለያይ ይሆናል ዋናዉ ግን ሰዉዬዉ ከዚሕ ቀደም ያሉት ነዉ።

                              

«ኔቶ በራሱ ችግር የለዉም።አባላቱ ግን  28 ሐገራት አሉ።ብዙዎቹ እኛን ይጠቀሙብናል።አይከፍሉንም።እኛ ከጥቃት እንጠብቃቸዋለን።ግን ለኛ አይከፍሉንም።የመጨረሻዋን ሲሰሙ ሁሉም ከኔጋር ይስማማሉ።ኔቶን እደግፋለሁ፤ ኔቶ አሮጌ ነዉ ብያለሁ።አንዱ ባልደረባሕ ሲጠይቀኝ የሰጠሁት መልስ ነዉ።ኔቶ አርጅቷል ብያለዉ ምክንያቱም ሽብርን መዋጋት አልቻለም።ይሕን ታዉቃለሕ።ትክክል መሆኔ ተረጋግጧል።በጣም ብዙ ሰዎች አመስግነዉኛልም።»

ብለዉ ነበር።መከለያከያ ሚንስትራቸዉ ጄምስ ማቲስ ባለፈዉ ሳምንት ብራስልስ ላይ ለተሰበሰቡት የኔቶ አባል ሐገራት መከላከያ ሚንስትሮች ግን ተቃራኒዉን አሉ።

                                 

27ቱ መከላከያ ሚንስትሮች በአሜሪካዊዉ አቻቸዉ ቃል «እፎይ» አሉ።እፎይታዉን

ለማጣጠም ግን ጊዜ አልነበረም።ሌላ ስብሰባ።የቡድን 20 አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ከነአጃቢ፤ ረዳቶቻቸዉ ቦን ላይ ታደሙ።እዚሕም ከዚያ ጥያቄ የጎላ ጥያቄ አልነበረም።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ምን ይሉ ይሆን? እንዳለቃቸዉ «አሜሪካ ትቅደም?» አልወጣቸዉም።

ይልቅዬ በተቃራኒዉ አሜሪካ ከሁለተኛዉ ያዓለም ጦርነት ጊዜ ጀምሮ እንደምትታወቅበት ከወዳጅ-ሸሪኮችዋ ጋር ተባብራ መሥራትዋን ትቀጥላለች አሉ።የአስራ-ዘጠኙን አቻዎቻቸዉን ደስታ የስብሰባዉ አስተናጋጅ የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዚግማር ጋብርኤል ባጭሩ ጠቀለሉት።

                    

«ከፊታችን የተደቀነዉን ከባድ ሥራ የትኛዉም መንግሥት ብቻዉን ሊወጣዉ እንደማይችል በሁሉም ዘንድ ጠንካራ መንግባባት በመኖሩ በጣም ተደስቻለሁ።ይኸ ምንም አያጠራጥርም።የወንጀለኞች ዝዉዉር፤ የአየር ንብረት ለዉጥ፤ ሽብርተኝነት፤ስደተኞች እነዚሕን ሁሉ በየብሔራዊ ድንበሮቻችን ብቻ መታገል አንችልም።እነዚሕን ችግሮች መቋቋም የምንችለዉ በየድንበሩ ኬላና መቆጣጠሪያ ማማ ሳይሆን ተባብረንና በግልፅ ሥንሰራ ነዉ።»

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ትቅደም ከማለታቸዉ እኩል እንደቀዳሚዎቻቸዉ ሞስኮን ገለል፤ ራቅ ማድረግ እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ አስታዉቀዋል።ይሕ መርሐቸዉ ዩናይትድ ስቴትስን ተማምነዉ ሞስኮዎችን ሲያስፈራሩ፤ ሲቆጡ፤ በማዕቀብ ሲቀጡ የከረሙትን የአሜሪካ የቅርብ ወዳጆችን አስግቶ ነበር።

 

የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን የሐገራቸዉን የቅርብ ወዳጆች አስደሰቱ እንጂ በረሲያ ሰበብ የገባቸዉን ሥጋት አላስወገዱም።የቀድሞዉ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ሥራ-አስኪያጅ እንደ ጥሩ ነጋዴ ጥቅም ካለ ትብብር አለ ነዉ ያሉት።የቲለርሰን መልዕክት የሩሲያዎችን ተስፋ አጠናክሯል።የአሜሪካ ወዳጆችን ሥጋት ባያስወግድም አላስከፋም።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫ ዘመቻቸዉ እስከ ቲዊተር መልዕክታቸዉ ቻይናን ያልተቹ ያልዘለፉበት ጊዜ የለም።ኩባንዮቻቸዉ ጠቀም ያለ ዶላር የሚዝቁት ግን ከቻይኖች በሚገዙ እና ለቻይኖች በሚሸጡት ሸቀጥ ነዉ።በዚሕም ሰበብ የትራምፕን ትችት ዘለፋ ቤጂንጎች ከቁብ አልቆጠሩትም ነበር።

«አንዲት ቻይና» የሚለዉን መርሕ ትራምፕ ሲቃወሙ ግን «ቀይ መስመር ረገጥሕ» አይነት አሉ ቻይኖች።ቻይና ከ1970 ጀምሮ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላት ግንኙነት ዋሽግተኖች ለታይዋን  የሚሰጡት የመንግሥትነት እዉቅና ደበቅ አድርገዉ በይፋ አንዲት ቻይና የሚለዉን የቤጂንግን መርሕ እንደሚያከብሩ ቃል በመግባታቸዉ  ነበር።

በትራምፕ ንግግር ያኮረፉት የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዪ የዩናይትድ ስቴትሱን አቻቸዉን ላለማግኘት ሲሉ በቦኑ ስብሰባ ላይ እንደማይካፈሉ አስታዉቀዉ ነበር።ትራምፕ ለቻይናዉ መሪ  ለቺ ጂፒንግ ሥልክ ደዉለዉ ካባበሏቸዉ በኋላ ግ ቺ ዋንግን ወደ ቦን ላኩዋቸዉ።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አሜሪካ የቻይናን ነባር መርሕ እንደምታከብር ነገሯቸዉ።እና ቻይኖች ተፅናኑ።

ግን ጊዜ የለም።አርብ የቦኑ ስብሰባ አበቃ።ሌላ ቀጠለ።የዓለም የፀጥታ ጉባኤ።ሙኒክ። 16 ርዕሳነ ብሔራት፤ አስራ አምስት መራሕያነ-መንግሥታት፤ 47 ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች፤ 30 መከላከያ ሚንስትሮች፤ 59 የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተጠሪዎች፤ 65 የኩባንያ ባለቤቶች በጥቅሉ 500 ሰዎች Bayerischer Hof ሆቴል ታድመዋል።

የአሜሪካ መከላካያ ሚንስትር

ብራስልስ፤ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ቦን ላይ ያሉ-ያደረጉትን ሁሉም ሰምተዋል።ገለል፤ ቀለል፤ ዝና ብለዋል።ግን ምክትል ፕሬዝደንቱን ለመስማት ጓጉተዋል።ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ እንደ አለቃቸዉ ሳይሆን እንደ ሚንስትሮቻቸዉ ወይም እንደ ቀዳሚዎቻቸዉ ተናገሩ።ኔቶ ያስፈልገናል።

                             

«የኛ እና የዚሕ ትብብር (የኔቶ) ጥንካሬ ከጦር መሳሪያ ጥንክሬያችን ብቻ የሚመጣ አይደለም።ከጋራ መርሐችን  አንዱ ነዉ። ከልብ ከምንጠብቀዉ መርሕ የሚነጭ ነዉ።»

የጀርመንዋ ዉጪ መራሒተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ለዶናልድ ትራም ስደተኞች የሚቀበሉ-ሞኝ፤ የዩሮ ምንዛሪን እያስቀነሱ ሐገራቸዉን የሚያበለፅጉ ራስ ወዳድ ናቸዉ።ለምክትል ፕሬዝደንት ለፔንስ ግን ሜርክል ጥብቅ የአሜሪካ ወዳጅ፤ በሳል መሪ፤ ጠንካራ አስተባባሪ ናቸዉ።ሜርክል ራሳቸዉ ፀጥታ በጦር ኃይል ብቻ አይጠበቅም አሉ።በልማት ጭምር እንጂ።

                                

«በአንድ መስመር ብቻ እንደማንታጠር ተስፋ አደርጋለሁ።የመከላከያ ሐይል በማሳደግ ብቻ ፀጥታና ደሕንነትን ማስከበር አይቻልም።ፀጥታና ደሕንነት ለማስከበር የልማትና ብልፅግናን ማሳደግና በዚሕ ረገድ የጋራ ሐላፊነታችንን መወጣትም ይገባናል።»

የጋራ ሐላፊነት።የብራስልስ፤ቦን፤ ሙኒኩ ስብሰባ ጉባኤ የነባሮቹን ወዳጅ ሐገራት ግንኙነት ወትሮዉ እንደነበረዉ እንደሚቀጥል፤ የምዕራባዉያንና የሩሲያ ጠብ እንደሚረግብ ተስፋ ሰጥተዋል። ቀጣይነቱ ግን በርግጥ ያጠያይቃል።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም ፍሎሪዳ ሆነዉ ዓለምን በሐሰት ማስፈራራታቸዉ ግን አጠያያቂዉን ተስፋ ጨርሶ እንዳያጨናጉለዉ ያሰጋል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

Audios and videos on the topic