ዩናይትድ ስቴትስና ሶማሊያ | ዓለም | DW | 11.12.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ዩናይትድ ስቴትስና ሶማሊያ

በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር 1993ዓ,ም ዓለምን ያስደነገጡ ምስሎች አይዘነጉም፤ የታጠቁ ሶማሌያዉያን የተገደሉ የዩናይትድ ስቴትስን ወታደሮች አስከሬን በመቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ ሲጎትቱ ታዩ። «የመቃዲሾ ዉጊያ» ተብሎ የሚጠራዉ ይህ ክስተት ለአሜሪካን ከፍተኛ ጥፋት ሆኗል፤ በወታደራዊ ተልዕኮዋም ዋነኛዉ አሳዛኝ አጋጣሚ።

default

በጎርጎሮሳዊዉ 1992ዓ,ም ታህሳስ 9ቀን፤ ልክ የዛሬ 20ዓመት ማለት ነዉ። ይህ ጥቁር ምዕራፍም ዋሽንግተን የአፍሪቃ ፖሊሲዋን ደግማ እንድትቃኘዉ ማድረጉ ይገለፃል።
ሶማሊያ የአምባገነኑ ዚያድ ባሬ መንግስት ከተገረሰሰበት ከዛሬ 21ዓመት ወዲህ በእርስ በርስ ጦርነት ብሎም በርሃብ እልቂት ስትዳክር ትገኛለች። በጎርጎሮሳዊዉ 1992ዓ,ም ታህሳስ 3 ቀን፤ የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔt አረጋግቶ ሰብዓዊ ርዳታ ማቅረብ እንዲቻል ዓለም ዓቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ በሙሉ ድምፅ ወሰነ። «የተባበረዉ ግብረ ኃይል» የተሰኘዉን ስብስብ አዛዥነትም ዩናይትድ ስቴትስ ተረከበች። 

የሶማሊያ ጉዳይ አዋቂ የሆኑትና ከዛሬ 20ዓመታት በፊት ኬንያ ዉስጥ የተማሩት ራሺድ አብዲ በጎረቤት ሶማሊያ በወቅቱ የተከናወነዉን በሚገባ ያስታዉሳሉ። ሁኔታዉ በመጀመሪያ በህዝቡ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር ባይናቸዉ፤
«የሰብዓዊ ርዳታ ማቅረቢያ በሮች ለማግኘት ተችሎ የረድኤት ድርጅቶች መግባት ጀምረዉ፤ ምግብ እጅግ ለተቸገሩት ወገኖች መድረስ ችሎ ነበር፤ ሆኖም ድንገት ጣልቃገብነቱ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሆነ፤ የአሜሪካን ወታደር ሲገደል ደግሞ ጉዳዩ ተባብሶ ወደጥፋት አዘነበለ።»
በወቅቱ የሶማሊያ ሚሊሺያ ወታደሮች ሁለት የዩናይትድ ስቴትስን ሄሊኮፕተሮችን መትተዉ ጣሉ፤ 18 የአሜሪካን ወታደሮችም ህይወት ጠፋ። የሟች ወታደሮቹም አስከሬን በመቃዲሾ ጎዳናዎች ተጎተተ። ዋሽንተን ወታደሮቿን ወዲያዉ አስወጣች። የሎንዶኑ ቻተም ሃዉስ ተንታኝ ቶማስ ካርጊሊ፤
«ዩናይትድ ስቴትስ በዚያን ወቅት ሶማሊያ ዉስጥ ያላት ተሞክሮ እጅግ አንገሽጋሽ ነዉ፤ እናም ለበርካታ ዓመታት እስከመስከረም አንዱ ጥቃት ድረስ እንዲያ ያለ የዉጭ ጣልቃገብነት ፍላጎቷን የቀነሰ ሆኖነዉ የታየዉ፤ በአፍሪቃም ቢሆን በሰብዓዊ ርዳታዎች ላይ ብቻ አተኩራ ነዉ የቆየችዉ።»
ይህ ሁኔታ ደግሞ በጎርጎሮሳዊዉ 2007ዓ,ም ተቀየረ፤ መቀመጫዉ ጀርመን ሽቱትጋርት የሆነዉ የአሜሪካን አፍሪቃ ወታደራዊ ዕዝ፤ አፍሪኮም ተቋቋመ። ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚከታተለዉ ይህን አካል ከምንም በላይ ወታደራዊ ስልጠና ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል። ካለፈዉ የአዉሮጳዉያን ዓመት 2011 ጀምሮ ለምሳሌ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በማዕከላዊ አፍሪቃ በጦር ወንጀለኛነት የሚጠየቀዉን ጆሴፍ ኮኒን በማደኑ ተግባር ዑጋንዳን እያገዙ ነዉ። ሶማሊያም ቢሆን ከአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ AMISOM ጀርባ በመሆን አሜሪካ ዳግም እንቅስቃሴ ጀምራለች። ከአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶናልድ ታይተልባዉም፤
«ለአፍሪቃ ኅብረት አማካሪዎችን መድበናል፤ እንዲሁም ለአፍሪቃ ኅብረት ተልዕኮ እና ኃይሎች የቴክኒክ ረዳቶችን እናቀርባለን፤ በተጨማሪም ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ድጋፋችንን እየሰጠን ነዉ፤ በዚያ ላይ የምንሰጣቸዉ ርዳታዎች አይነት በሶማሊያ ማኅበረሰብ በራሱ የሚወሰኑ ይሆናሉ።»

Somalia USA Amerikanischer Luftangriff auf Al-Qaida-Ziel in Somalia

ሶማሊያ ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ በዘንድሮዉ የሰሜኑ ንፍቀክበብ የመፀዉ ወራት  ከእርስበርስ ጦርነት ተንፈስ ብላ በአግባቡ የሚንቀሳቀስ ማዕከላዊ መንግስት የመሠረተችዉ። ሀሰን ቼኪ ሞሐመድ አዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሆነዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ይህች ሀገር ተረጋግታ የእስላማዊዉ ፅንፈኛ አሸባብ ሚሊሻዎች ተፅዕኖ ጠፍቶ የማየት ፅኑ ፍላጎት አላት። በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፈዉ AMOSOM ወታደሮች ከቡድኑ ጋ በሚያደርጉት ዉጊያ አዎንታዊ ርምጃ ተራምደዋል። አሜሪካ ድጋፏን በግልፅ ብትሰጥ ግን አሉታዊ መዘዝ ሊኖረዉ አይችልም ብሎ መገመት ያዳግታል ይላሉ ራሺድ አብዲ፤
«አሜሪካኖች ሶማሊያ ዉስጥ ቀጥተኛና ግልፅ ወታደራዊ ጣልቃገብነታቸዉን አሸባብ ፀረአሜሪካን ቅስቀሳ ለማድረግ ሊጠቀምበት እንደሚችል ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። በዚህ ምክንያትም ነዉ አሜሪካኖች በዚህ ጉዳይ ዉስጥ በቀጥታ ራሳቸዉን ከማስገባት ይልቅ ሶማሊያ ዉስጥ ተቀባይነት ያላቸዉን የአፍሪቃ ሀገሮች መደገፍ የመረጡት።»

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic