የAPEC ጉባኤና የቺሌዉ ፕሬዝዳንት መግለጫ | ኤኮኖሚ | DW | 22.11.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የAPEC ጉባኤና የቺሌዉ ፕሬዝዳንት መግለጫ

የቺሌዉ ፕሬዝዳንት-ሥለነዚሕ ጉዳዮች ሲጠየቁ ተናደዱ።ዝር ዝሩንም አልተናገሩም። ገፃቸዉ ግን ጋዜጠኞች እንዳሉት ሁሉንም ብሎታል።

ጉባኤተኞች

ጉባኤተኞች

ቺሌ ርዕሠ-ከተማ ሳንቲያጎ ተሠይሞ የመነበረዉ የእስያ-ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ APEC) ጉባኤ ያሳለፋቸዉ ዉሳኔዎች የማሕበሩን አባል ሐገራት ትብብር ይበልጥ ያጠናከረ እንደነበር አስተናጋጁ አስታወቁ።የቺሌዉ ፕሬዝዳንት ሪካርዶ ላጎስ እንዳሉት የሁለት ቀኑ ጉባኤ እንደ ቻይናና ሩሲያ የመሳሰሉ ፣ከደቡብ አሜሪካ እጅግ የራቁ ሐገራትን ከቺሌና ከጎበረቤቶችዋ ጋር ያቀራረበ ነዉ።በጉባኤዉ ላይ የተካፈሉት የሃያ-አንዱ ሐገራት መሪዎች ፀረ-ሽብር ዘመቻቸዉን ለማጠናከር ወስነዋል። ነፃ የንግድ ልዉዉጥ ቀጠና ለመመስረት የቀረበዉን ሐሳብ ግን ጉባኤተኞቹ አላፀደቁትም።ጉባኤዉ የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽን የሚቃወሙ ሠልፈኞችና የፀጥታ አስከባሪዎች ግጭትም አጥልቶበት ነበር።


ቅዳሜና እሁድን ሳንቲያጎ ተሰብስበዉ የነበሩት የሃያ አንዱ ሐገራት መሪዎች እንደ ማሕበሩ ሥም በይፋ እንደሚታወቅ አላማ-ምግባሩም ሥለምጣኔ ሐብትና ንግድ ግንኙነታቸዉ መክረዉ-ዘክረዉ ይወስናሉ ነበር-እምነቱ።ከምጣኔ ሐብቱ ይልቅ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር መርሐ-ግብር ለማስቆም ይደረግ የነበረዉ ድርድር ሥለሚቀጥልበት፣ ከንግድ ሽርክናዉ ይብስ አሸባሪዎችን ለመዋጋት የመሥረቱት ትብብር ሥለሚጠናከርበት ነዉ-የወሰኑት።«አንድ ማሕበረሰብ መፃኤ ተስፋችን» በሚል መሪ መፈክር የታደሙት መሪዎች በሃያ አንዱ ሐገሮቻቸዉ መካከል ነፃ የንግድ ልዉዉጥ የሚመሠርትበት ድርድር እንዲጀመር ባለሙያዎች ባቀረቡት ሐሳብ እንኳን አልተስማሙም።

ጉባኤዉ መቅደም የነበረበትን አስከትሎ ፣መከተል የነበረበትን ማስቀደሙ ለጉባኤዉ አስተናጋጅ ሪካርዶ ላጎስ ተገቢ ነዉ።የቺሌዉ ፕሬዝዳንት እንግዶቻቸዉን ትናንት ለጋዜጠኞች እንደነገሩት ሐገራቸዉ ጉባኤዉን ማስተናገዷ፣ ጉባኤዉ የወሰነዉን መወሰኑም አለምን በሌላ አይነት ለመመልከት ረድቷል።ምክንያቱም ላጎስ እንደሚሉት ደቡብ ምሥራቅና ሰሜን እስያን ከደቡብ አሜሪካ የሚለየዉን ርቀት ጉባኤዉ አጥቦታልና።ምሳሌያቸዉ የሩቅ ምሥራቅዋ የምጣኔ ሐብት የሕዝብ፣ የፖለቲካ የጦር ሐይልም ሐያሏ ቻናና የሰሜን ምሥራቅ አዉሮጳ ብጤዋ ሩሲያ ናቸዉ።

ቻይናና ሩሲያ-በተለይ የእስያ ሐገራት-ባጠቃላይ፣- ከደቡብ አሜሪካ ሐገራት ያላቸዉን ሽርክና ለማጠናከር መስማማታቸዉ የቺሊዉ ፕሬዝዳንት እንደሚያምኑት ለሁለቱ አካባቢዎች የምጤኔ-ሐብት እድገት በጅጉ የሚጠቅም ነዉ።ፕሬዝዳንት ላጎስ፣ ጋዜጠኞች እንደታዘቡት፣ ሁለት ቀን ያስተናገዱት ጉባኤ የወሰነዉን በወሰኑ፣ እጅግ መደሰታቸዉን በቃል-ብቻ ሳይሆን በፊታቸዉም ይገልጡት ነበር።-ዘና-በፈገግ እያሉ።በጋዜጣዊዉ ጥያቄ-መልስ በስተማብቂያ አንድ ጋዜጠኛ የወረወራት ጥያቄ ግን እስከዚያ ድረስ ፈገግታ ያልተለየዉን የላጎስን ፊት ያቀጨመች፣ ቀለል-ዘና ብሎ የነበረ ሰዉነታቸዉን የሰበሰበች፣ ስሜታቸዉንም ያስቆጣች ነበረች።


ፕሬዝዳንት ሪካርዶ ላጎስ በተለይ ለዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ክብር ልዩ የእራት ግብዣ ደግሰዉ ነበር።ትናንት ማታ።በግብዣዉ ላይ ከሃያ አንዱ መሪዎች ሌላ ሰወስት መቶ ባለሥልጣናት፣ የትላልቅ ኩባንያ ባለቤቶችና ነጋዴዎችም ተጋብዘዉ ነበር።የቡሽ ፀጥታ አስከባሪዎች ወደ ግብዣዉ አዳራሽ የሚገባዉን ሰወስት መቶ እግዳ በሙሉ በኤሌክትሪክ መመርመሪያ እራሳቸዉ ካልፈተሹ እንዳማያስገቡ አስታወቁ።ፍተሻዉ ለክብር እንግዶቹ እንደ ክብር-ነክ የሚቆጠር ነዉ።ፈታሹቹ የአሜሪካ ፀጥታ አስከባሪዎች እንዲሆኑ አሜሪካኖች መጠየቃቸዉ ደግሞ ለቺሌ ፀጥታ አስከባሪዎች ለላጎስ መንግስትም አሳፋሪ ነበር።

ግብዣዉ ተሠረዘ።

ፕሬዝዳንት ቡሽ ከጉባኤዉ በሕዋላ ለበርካታ ሠአታት በቺሌ «ይፋ ጉብኝት» አደረጉ ተባለ እንጂ ላ-ሞንዳ ከተባለዉ የቺሌ ቤተ-መንግሥት አልወጡም።ያ አንዱ መሪዎች የተሰበሰቡበት አዳራሽ ዙሪያ ገባ ከአርብ ጀምሮ ፕሬዝዳንት ቡሽን በሚቃወሙ ሠልፈኞች ተከቦ ነዉ-የሰነበተዉ።ተቃዉሞ ሠልፈኞችና ፀጥታ አስከባሪዎች ተጋጭተዉ ሰዉ ተጎድቷል።አሳቻ ልብስ ለብሰዉ ከቺሌ ፀጥታ አስከባሪዎች መሐል ተቀይጦዉ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ይከታተሉ ከነበሩ የፕሬዝዳንት ቡሽ ጠባቂዎች መሐል አንዱ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ወደ ጉባኤዉ አደራሽ ሊገባ ሲል የቺሌ ፀጥታ አስከባሪዎች መከልከላቸዉ ሌላ ጠብ አብቅሎ ነበር።

የቺሌዉ ፕሬዝዳንት-ሥለነዚሕ ጉዳዮች ሲጠየቁ ተናደዱ።ዝር ዝሩንም አልተናገሩም። ገፃቸዉ ግን ጋዜጠኞች እንዳሉት ሁሉንም ብሎታል።

ተቃዉሞ ሠልፍ፣ ግጭት፣ ጭቅጭቅ የመርሐ-ግብር መሠረዝ ያልተለየዉ ጉባኤ «የሳንቲያጎ መግለጫ» ባለዉ ሠነዱ ሃያ አንዱ ሐገራት ነፃ የንግድ ልዉዉጥ ለመስረት ድርድር መጀመር አለመጀመራቸዉን ለከርሞ የሚደረገዉ ጉባኤ እንዲወስን ክፍት አድርጎታል።ይሁና ነፃ የንግድ ልዉዉጡ እንዲጀመር የሚረዱ የንግድ ሥምምነቶችን ለማጥናትና ለማጠናከር ጉቤተኞቹ ቃል-ገብተዋል።ቻይና የአለም ንግድ ማሕበር አባል በመሆንዋ ሃያ አንዱ መሪዎች መደሰታቸዉን ገልጠዉ፣ ሩሲያና ቬትናምም እንደቻይና የማሕበሩ አባል ለመሆን የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ ተስማምተዋል።ሃያ-አንድ የእስያና የአሜሪካ ሐገራትን የሚያስተናብረዉ የንግድ ማሕበር የተመሠረተዉ በ1981 ነዉ።