የ70ዎቹ ፓርቲዎች የረሐብ አድማ ውጥንና የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 04.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የ70ዎቹ ፓርቲዎች የረሐብ አድማ ውጥንና የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት

ወደ 70 ገደማ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቤቱታችንን ካልሰማ "የረሐብ አድማ እናደርጋለን" ማለታቸው በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ዘንድ መወያያ ሆኗል። የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች አዲስ ስምምነት ሌላው ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:34

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

አዲሱ የምርጫና እና የፓለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ "የሕልውናችን አደጋ ሆኗል" የሚሉ ፓርቲዎች "የረሐብ አድማ ልናደርግ ነው" እያሉ ነው። ፓርቲዎቹ እንዳሉት ወደ ረሐብ አድማ ከመሔድ የሚያግዳቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዓመቱ የመጀመሪያ ስብሰባ በጉዳያቸው ላይ ከመከረ ብቻ ነው። ጉዳዩ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ነቀፌታ በርትቶበታል።

ፍሬው አበበ «አባል እና ደጋፊ ያለው ፓርቲ ሲከፋው ሰልፍ ጠርቶ እንኳንስ ገዢውን ምድሩን ያንቀጠቅጣል። የኛዎቹ አባል አልባ ፓርቲዎች የሚጠሩት ቢያጡ በረሀብ አድማ ጮማቸውን እያቀለጡ ያለቅሳሉ» ሲል ነቅፈዋቸዋል።

ገረመው አያሌው «ወትሮም "ፓርቲ" ያቋቋሙት ለርሀብ ማስታገሻ ነው ወዳጄ- አለማፈራቸው? "የምርጫ ሕግ ካልተሻሻለ የርሀብ አድማ እናደርጋለን አሉ?» ሲሉ ለፍሬው አበበ በሰጡት መልስ ጠይቀዋል።

«በዚህ ጉዳይ ባልፅፍ ደስ ባለኝ» ሲሉ የጀመሩት ተክሌ በቀለ «እኔ በግሌ 1000 ሰው ተሁኖም ፖርቲ መመስረት መቻል አለበት ባይ ነኝ። የሀብት ክፍፍል ጥያቄን ሲያስከትል ግን አከፋፋዩ መንግስት በምርጫ ቦርድ በኩል የራሱን መመዘኛዎች ማውጣቱ ተገቢ ነው።ተቃዋሚዎቻችን የርሃብ አድማ ሊያረጉ ነው ሲባል ስሰማ ግን ለውድቀታቸው ማንን ተጠያቂ ሊያደርጉ እንደፈለጉ እየገረመኝ ነው» ብለዋል።

ግዛቸው አበበ ደግሞ «የዐብይ አሕመድ ቡድን በሚሰጠውን መመሪያም ሆነ መሰሪ ምክርን በመጠቀም የፓርቲዎችን ቁጥር መወሰን ተገቢ አይደለም። የዐብይ ቡድን ማድረግ የሚችለው በገንዘብ የሚደጉማቸውንና የማይደጉማቸውን፣ ጽሕፈት ቤት የሚሰጣቸውንና የሚነፍጋቸውን ፓርቲዎች የሚለይበት መመሪያና ደንብ ማውጣት ብቻ ነው። የአገሪቱ አቅም ፓርቲ ነኝ የሚለውን ሁሉ መሸከም ስለማይችል። ነገር ግን `አሜሪካ ውስጥ ሁለት ፓርቲዎች ብቻ ነው ያሉት` በሚል ተረት የኢትዮጵያን ፓርቲዎች ቁጥር ለመወሰን ተጽዕኖ ማድረጉ አምባገነናዊ አካሄድ ነው። ምርጫ ቦርድ ይህን በዐብይ አሕመድ ጉትጎታ የመጣን ውሰና መተው አለበት።  100 ሚሊዮን [ሕዝብ] ባለበት አገር እንዴት 10 ሺሕ በዛ ይባላል? የሚለው ምክንያትም ውኃ አያነሳም» ሲሉ ከተክሌ በቀለ ጋር በፌስቡክ ባደረጉት ውይይት ላይ ፅፈዋል።

ለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውጥን ምንድነው?

በማኅበራዊ ድረ-ገፆች መወያያ ሆነው የሰነበቱት 70 ገደማ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን ማቅረብ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። ዋንኛ ቅራኒያቸው የሚመነጨው በቅርቡ ከጸደቀው አዲሱ የምርጫና እና የፓለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ነው። ፓርቲዎቹ ከዚህ ቀደም በሌሎች ርዕሰ-ጉዳዮች ለመወያየት ተሰብስበው "የሕልውናችን ሥጋት" በሚሉት በዚሁ የምርጫና እና የፓለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ሲወዛገቡ ታይተዋል።

ፓርቲዎቹ በአዲሱ አዋጅ "እንደገና ተመዝገቡ ተብለናል" የሚል ቅሬታ አላቸው። የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀ-መንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ «20 እና 25 ዓመታት ሲንገላቱ እና ሲታገሉ የቆዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አዲስ እንደገና ፓርቲያቸውን አፍርሰው በዚህ ህግ መመስረት አለባቸው» ሲሉ ተናግረዋል። «ፓርቲዎቹ ሕልውናቸውን አጥተዋል» የሚሉት አቶ ቶሎሳ አዋጁ «አሳሪ ነው» ሲሉ ቅሬታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው አዋጁ «የእያንዳንዳችንን ሕልውና አፍርሶታል» ባይ ናቸው።

ፓርቲዎቹ ባለፈው ረቡዕ በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያው ስብሰባ ጉዳያቸውን እንዲመለከት ጠይቀዋል። አለበለዚያ ከጥቅምት 5 እስከ 6 የረሐብ አድማ እናደርጋለን ሲሉ አስጠቅቀዋል።

ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ እስካሁን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠ ምላሽ የለም። ፌስቡክ እና ትዊተርን የመሳሰሉ የማኅበራዊ ድረ-ገፆች ተጠቃሚዎች ግን በጉዳዩ መነጋገራቸውን ቀጥለዋል።

ሐና ጫላ በትዊተር «ኢትዮጵያዬ ከኮሜድያኖችሽ የተሻለ የሚያስቁኝ እኮ ፖለቲከኞችሽ ናቸው። የረሀብ አድማ?» ሲሉ በጉዳዩ መገረማቸውን ገልጸዋል። ታጋይ ህጻናት «አሻንጉሊት ካልገዛሽልኝ ምሳዬን አልበላም" ይላሉ ከሚል ማነፃጸሪያ የጀመሩት ካሳሁን መሰለ ደግሞ «መድረክ አዘጋጅተው መወያየት እና መከራከር ያቃታቸው ታጋይ ፓርቲዎች አዋጁ ካልተሻረ የረሀብ አድማ እንመታለን» ማለታቸውን ጠቅሰው ነቅፈዋል።

ኤርሚያስ ሙሉጌታ ደግሞ «በፖለቲካ ፓርቲዎች የታወጀውን የረሀብ አድማ ተከትሎ የምግብ ዋጋ ይወርዳል ተብሎ ይጠበቃል። ግን አድማ ባይደረግስ ምግብ እኮ የለንም» ሲሉ ተሳልቀዋል። ደያሞ ዳሌ ደግሞ በትዊተር «ስንት ሕዝብ እየተራበ በአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ሕይወቱን የሚያቆይባትን አገር ለመምራት፤ በምርጫ እንወዳደራለን የሚሉ ፓርቲዎች የሕዝብ ድጋፍ የፓርቲነት መስፈርት መሆኑን በመቃወም የረሀብ አድማ ሲመቱ ከማየት የበለጠ ቀልድ የለም» ብለዋል።

ኑረዲን ሰዒድ «የረሀብ አድማውን እድሜ ልክ ቢያደርጉት ለኛ የኑሮ ውድነቱ ይቀንስልን ነበር። ምክንያቱም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመብዛታቸው የተነሳ ለኑሮ ውድነቱ አስተዋጿቸው ከፍተኛ ነው» ሲሉ ፌስቡክ ላይ ፅፈዋል። ሽመልስ ቶሎሳ ደግሞ «ኸረ እባካችሁ እፈሩ። 10 ሺሕ ደጋፊ ማስፈረም ካልቻላችሁ ማንን ልትወክሉ ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ እንደበፊቱ በተለጣፊ አይሸወድም ነቄ ሆኗል» ብለዋል። ደርቤ ቢሰጥ በበኩላቸው «የፓርቲ ጋጋታ ለሀገራችን አይጠቅማትም፤ ሰብሰብ ብላችሁ አቋም ይኑራችሁ። በፓርቲ ስም ገንዘብ ለመሰብሰብና ህዝብን ለማጋጨት ማነሳሳት ይቅርባችሁ» ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የኦሮሞ ፓርቲዎች ስምምነት

በሳምንቱ ዋና ዋናዎቹ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች «በጋራ ለመስራት» ከስምምነት መድረሳቸውን አሳውቀዋል። ፓርቲዎቹ ሰባት ናቸው። ስምምነት በተፈረመበት ዕለት በኦሮሞ ፖለቲካ ከፍተኛ ሚና ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና የለውጥ አራማጆች ተገኝተዋል።  «እጅግ ደስ የሚል ዜና ነው፣ ኢትዮጵያችን የምትፈልገው በጋራ አንድ ሆኖ ለሕዝቡ መሥራት ነው፣ ባሁኑ ጊዜ የሚያስፈልገው ሌሎችም ፓርቲዎች ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ወስደው መሥራትና መተባበር አለባቸው» ያሉት ጀማል አብደላ የፓርቲዎቹን ስምምነት እንደ በጎ እርምጃ ተቀብለውታል።  ታደሰ ጌታቸው «ይህ ነዉ አንድነት፤ ኦሮሚያም ኢትዮጵያም ተስፋ አላት፣ ፈርጣማ አንድነት ነዉ፤ በዲሞክራሲ ባህል እንዲህ አብሮ መሥራት እንጂ በጠላትነት መፈራረጅ ማብቃቱ ያስደስታል። መባላት ሲቀር ማደግ ይመጣል» በማለት እንደ ጀማል አብደላ ሁሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።

ጂቲ አሬዶ «ይሄ ትልቅ ብስለት ነው፤ ሕዝቡም የሚፈልገው ይሄንን ነው፤ በውይይት በጠረጴዛ ዙሪያ መጨረሱም ምን ያህል ወደ ፊት እንደሄዳችሁ የሚያስይ ነው። ሕዝቡም እፎይታን ያገኛል። ጫካ ያሉትምን ለቤታቸው ያብቃቸው» ሲሉ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ኤርሚ ለ «የኦሮሚያ  ፓለቲከኞች የተለያየ ሀሳብ ቢኖራቸውም ልዩነታቸውን ወደ  ጎን ትተው በሚስማሙበት መልኩ በአንድነት ለሚወክሉት ህዝብ መቆማቸው  ከምንም አንፃር ስታየው ትልቅ ውሳኔ ነው። ለክልሉ ሰላም መሰረት ነው፤ ለውጭ ኃይሎች ደግሞ የማይናጋ፤ የማይነቃነቅ ግድግዳ ነው፤ አሁን የጃዋር፣ የኦነግ፣ የአብይ ደጋፊ ብሎ ምንም አይነት ሰላምን የሚያደፈርስ እንቅስቃሴ አይኖርም።  ለኦሮሚያ ትልቅ ስራ ነው» ሲሉ አተያያቸውን ጽፈዋል።

የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲህ አይነት ስምምነት ሲፈፅሙ የመጀመሪያቸው አይደለም። ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስምምነት ከፈረሙት መካከል የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድና፣ ምክትል ሊቀ-መንበርና የመከላከያ ምኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ -መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ-መንበር አቶ ሌንጮ ለታ እና በኦሮሞ ፖለቲካ ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው አቶ ጃዋር መሐመድ ተገኝተዋል።

በርካቶች በፌስቡክ እና በትዊተር አሁን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተፈራረሙት ስምምነት ከከዚህ ቀደሙ በምን ይለያል ሲሉ ጠይቀዋል።«ከዚያስ? ወደየት?» የሚል ጥያቄም ያቀረቡም አሉ። ስለ ስምምነቱ በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም የኦሮሞ የፖለቲካ መሪዎችን በአንድ ላይ ያሰባስባል ያሉትን ጋዲሰ ሆጋንሳ ኦሮሞ ለመመስረት መስማማታቸውን በጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። አቶ ለማ መገርሳ የሚመሩት እና አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙም ተገልጿል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች