የ2019 የኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 16.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የ2019 የኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች

በአለም ደረጃ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የሚበረከተው የኖቤል ሽልማት በባለሙያዎች ዘንድ ከፍተኛ ክብር አለው። በ5 ዘርፎች የተከፋፈለው የኖቤል ሽልማት የዚህ ዓመት አሸናፊዎች ማንነት እስካለፈው ሰኞ ድረስ በተከታታይ ሲገለጽ ቆይቷል። ዘንድሮ በኬሚስትሪ ዘርፍ አሸናፊ የሆኑት 3 ሳይንቲስቶች ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 06:58

የ2019 የኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች

የኖቤል ሽልማት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን እንደ ዘንድሮው ቅርብ ሆኖ አያውቅም። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለኖቤል የሰላም ሽልማት መታጨታቸው ከተነገረበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሽልማቱ የሚሰጠው ትኩረት ጨምሮ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእዚህን ዓመት የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸው ከመገለጹ በፊት በህክምና፣ በፊዚክስ፣ በኬምስትሪ እና በስነ ጽሁፍ ዘርፎች ተሸላሚዎች የሆኑ ግለሰቦች ማንነት በተከታታይ ይፋ ተደርጓል። ተሸላሚዎቹን ለዕውቅና ካበቋቸው ስራዎች ውስጥ እንደ ኬሚስትሪው ዘርፍ የምርምር ውጤት ለቢሊዮኖች የቀረበ የለም።

ይህ የምርምር ውጤት በየሰው ኪስ እና ቦርሳ ከማይጠፋው የተንቃሳቃሽ (ሞባይል) ስልክ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ዘመናዊዎቹም ሆኑ በአፍሪካ የሚዘወተሩት መደበኛ አገልግሎት የሚሰጡት የተንቀሳቃሽ ስልኮች ጀርባቸው ሲከፈት በጉልህ የሚታየው የመንቀሳቀቀሻ ኃይል የሚያገኙበት ባትሪያቸው ነው። እነዚህ ባትሪዎችን ቀረብ ብሎ የተመለከተ ደግሞ “ሊትየም አየን” ከተሰኘ ንጥረ ነገር መሰራታቸውን በቀላሉ ማወቅ ይችላል። እኒህን አይነት ባትሪዎች በስፋት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ደግሞ የበየሀገሩ ያሉ ተመራማሪዎችን የዓመታት ጥረት ጠይቋል።

በሳይንሱ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን ለኖቤል ሽልማት የመምረጥ ሚና የተሰጠው የስዊዲን የሳይንስ አካዳሚ ለዚህ የተመራማሪዎች ድካም እና ውጤት ዘንድሮ ዕውቅና ሰጥቷል። የኖቤል የሽልማት ኮሚቴ ዋና ጸሀፊ ጎራን ሃንሰን በኬምስትሪ ዘርፍ የተመረጡ የእዚህ ዓመት የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎችን ባለፈው ረቡዕ መስከረም 28 ይፋ ሲያደርጉም “የሊትየም አየን” ባትሪ አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ በተለያየ ጊዜ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ተመራማሪዎች ሳይዘነጉ ነው። “የስዊዲን ሮያል የሳይንስ የሳይንስ አካዳሚ የሊትየም አየን ባትሪን ለማሳደግ ለሰሩት ለጆን ጉድኢነፍ፣ ለስታንሊ ዊቲንግሃም እና አኪራ ዮሺኖ የ2019 የኖቤል የኬምስትሪ ሽልማት በጋራ እንዲሰጥ ወስኗል” ብለዋል።

 ለሽልማት የበቁት ሶስቱም ተመራማሪዎች ከሊትየም የሚሰራ ባትሪ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ያበረከቱት አስተዋጽኦ ላቅ ያለ እንደሆነ ይነገርላቸዋል። ከእነርሱ ውስጥ የሊትየም አየን ባትሪዎች እውን እንዲሆኑ መሰረት ጥለዋል የሚባሉት ስታንሊ ዊትንግሃም ናቸው። በኒው ዮርክ ስቴት ዩኒቨርስቲ የኬምስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዊትንግሃም አገልግሎት ላይ ሊውል የሚችል የሊትየም ባትሪ የሰሩት በ1970ዎቹ ውስጥ ነው። ያኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተ የነዳጅ ዘይት እጥረት እና ተከትሎት በመጣው የዋጋ ማሻቀብ ምክንያት ዓለም አማራጭ የኃይል አቅርቦት በጥብቅ የሚፈልግበት ጊዜ ነበር።

ዊትንግሃም ታዲያ ከብረት ዘሮች አንዱ የሆነው እና ከመቅለሉ የተነሳ በውሃ ላይ ጭምር ሊንሳፈፍ የሚችለውን ሊተየም የተባለው ውህድ ኃይልን ሰብስቦ በውስጡ ሊያምቅ እንደሚችል ይደርሱበታል። ከዚያም በከፊል ሊትየም ያለበት፣ ኃይልን ማስተላለፍ የሚችል ባትሪ ይሰራሉ። ሆኖም ባትሪው የኃይል መዋዥቅ ችግር ነበረበት እና በሰፊው አገልግሎት ላይ መዋል ሳይችል ይቀራል።

በጀርመን የተወለዱት እና በስተኋላ የአሜሪካ ዜግነትን የወሰዱት የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያው ጆን ጉድኢነፍ በዊትንግሃም በተሰራው ባትሪ ላይ ተመርኩዘው የራሳቸውን ምርምር ማካሄድ ቀጠሉ። በባትሪ ውስጥ ያለውን የብረት ውህድ በሌላ በመተካት የባትሪውን የኃይል አቅም በእጥፍ በማሳደግ ወደ አራት ቮልት አስገቡት። የእርሳቸው የምርምር ውጤት ይበልጥ ኃይል ያላቸውን እና ለረጅም ጊዜ ማገልገል የሚችሉ ባትሪዎችን ለመስራት መንገዱን ጠርጓል።

ጉድኢነፍ የምርምር ውጤታቸውን ባሳተሙበት ወቅት በጃፓን ያሉት ተመራማሪ አኪራ ዮሺኖ በሊትየም አየን ባትሪዎች ላይ ምርምር መጀመራቸው ነበር። በጉድኢነፍ ስራ ላይ ተንተርሰው ባደረጉት ምርምር ማንኛውም ሰው በተንቀሳቃሽ ስልኩ በኪሱ ይዞት የሚዞረው ባትሪ እንዲፈበረክ አስችለዋል። ተመራማሪው ከብረት ይልቅ የካርበን ቁሶችን በመጠቀም የሊትየም አየን ውህዶች በባትሪ ውስጥ እንዲከማቹ አድርገዋል።

የሶስቱ ባለሙያዎች የቅብብሎሽ የምርምር ስራ ባለከፍተኛ ኃይል፣ ክብደቱ ቀለል ያለ እና በየጊዜው ሊሞላ (ቻርጅ ሊደረግ) የሚችል ባትሪ ለመፍጠር አስችሏል። ሶስቱ ተመራማሪዎች የኖቤል የኬሚስትሪ ሽልማት ማሸነፋቸው በተነገረበት ዕለት የሽልማቱ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኦሎፍ ራምስቶርም ይህንኑ በአጽንኦት አንሰተዋል። ከፊት ለፊታቸው በተዘረጋው ግድግዳ ላይ ያለውን ፔሬዲክ ቴብል እያሳዩ ለጋዜጠኞች ተከታዮን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“በደንብ የሚሰራ እና ውጤታማ የሆኑ ባትሪዎችን ዲዛይን ማድረግ እና መስራት በእውነቱ በጣም ከባድ ነገር ነው። ምሳሌ ለመስጠት ያህል አሁን የምንገለገልባቸው እንደ ‘ሊድ አሲድ ባትሪ’ እና ‘አልካላይን ባትሪ’ አይነቶቹ ተሰርተው የተጠናቀቁት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ስለዚህ አዲስ ጥሩ ባትሪ መስራት ከባድ ስራ ነው። እንዲያም ቢሆን ሶስቱ ሉሬቶቻችን በእርግጥ የሰሩት ያንን ነው። ይህንን ፈተና በመቀበላቸው የእነርሱ ግኝቶች ክስተታዊ እና አስደናቂ ለሆነው የሊትየም አየን ባትሪ መሰራት ምክንያት ሆኗል። ይህ ነገር ታዲያ ምንድነው ያላችሁ እንደው? እንደምትመለከቱት እና ስሙ ራሱ እንደሚገልጸው ነገርየው ሊትየም ነው። በፔሬድክ ቴብሉ ላይ እንደምትመለከቱት፤ በቀይ ሳጥን ውስጥ ያለው እና አቶሚክ ቁጥር 3 የተጻፈበት ሊትየም ነው። በጣም ትንሽ ንጥረ ነገር ነው። ካለን የብረት አይነቶች ውስጥ በጣም ቀላሉ የሚባለው ነው።”

በስዊዲኑ ስቶክሆልም ዩኒቨርስቲ የቁሶች እና የአካባቢ ኬምስትሪ ትምህርት ክፍል ምክትል ኃላፊ የሆኑት ቻይናዊቷ ዞ ዣይዶንግ የሶስቱ የኖቤል ተሸላሚዎቹ የምርምር ስራዎች ከጊዜ በኋላ ምን ውጤት እንዳስገኙ ያስረዳሉ። “የእያንዳንዳቸው አበርክቶት አሁን በእጃችን ነው ያለው። ይህ ማለት የዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ላፕ ቶፕ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እድገት ለሊተየም አየን ባትሪዎች ተነጥሎ የሚታይ አይደለም ማለት ነው። በሊትየም ባትሪዎች ላይ በመመስረት በርካታ አነስተኛ እና በቀላሉ ማንቀሳቀስ የምንችላቸው የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ማምረት ተችሏል። እኔ እንደማስበው ይህ ለሳይንስ ትልቅ መሻሻል ነው” ሲሉ የተመራማሪዎቹን ስራ ዘክረዋል። 

Tesla Roadster Elektroauto (AP)

የሊትየም አየን ባትሪ ከአነስተኛ ቁሳቁሶች እስከ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች ማንቀሳቀሻ ማዋሉ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የኃይል ምንጮች እንደ ደጋፊ እና መጠባበቂያ መዋሉ ጠቀሜታውን እንደሚያደርገው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ አባሉ ኦሎፍ ራምስቶርም ይጠቅሳሉ። ጸሃይ እና ንፋስን ተጠቅመው ኃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶች የኃይል አቅርቦት መዋዥቅ ሲያጋጥማቸው በምትኩ የሊትየም አየን ባትሪዎችን በብዛት መጠቀማቸውን በምሳሌነት ያነሳሉ። “ይህ ባትሪ በማህበረሰባችን ውስጥ አስደናቂ ውጤት አምጥቷል። የሶስቱ ሎሬቶቻችን ግኝቶች ይህ እውን እንዲሆን ማስቻሉም ግልጽ ነው። ስለዚህ ይህ ለሰው ልጅ በጎ የሆነ ጠቀሜታ የሆነ ነው” ይላሉ።    

በኬምስትሪ ዘርፍ ባለፈው ረቡዕ የኖቤል ሽልማት ካሸነፉት ሶስቱ ተመራማሪዎች ውስጥ ጆን ጉድኢነፍ በሌላ ክብረወሰንም አስመዘግበዋል። አሁን 97 ዓመታቸውን የደፈኑት ጉድኢነፍ እስካሁን የኖቤል ከተበረከተላቸው 923 ሎሬቶች ውስጥ በእድሜ ትልቁ በመሆን ታሪክ ሰርተዋል።  

ተስፋለም ወልደየስ 

ሸዋዬ ለገሠ      

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች