የ2019 ዓ/ም የሳይንስ ዝግጅቶቻችን ቅኝት በከፊል | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 01.01.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የ2019 ዓ/ም የሳይንስ ዝግጅቶቻችን ቅኝት በከፊል

በተገባደደዉ  የጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም በሳይንስና ቴክኖሎጅ ፕሮግራም ከቃኜናቸዉ  ዝግጅቶች መካከል በዛሬዉ ዝግጅታችን የተወሰኑትን ቃኝተናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:36

ዐበይት የሳይንስ ግኝቶች


ባሳለፍነዉ የፈረንጆቹ 2019 ዓ/ም በኢትዮጵያ የተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሰው አልባ ተንቀሳቃሽ አውሮፕላኖች (ድሮኖችን) በነዳጅ  ማስተላለፍ፣ በማዕድን ፍለጋ እና በግብርና መረጃ አሰባሰብ ዙሪያ ለመጠቀም እያደረጓቸው ያሉትን እንቅስቃሴም ዳሰን ነበር።

ሰው አልባ ተንቀሳቃሽ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ብዙ ጊዜ  ወታደራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንደ መጠን እና አይነታቸው፤ አገልግሎታቸው እና የሚሳተፉበትም ዘርፍ እየበዛ መጥቷል። ድሮኖች ከወታደራዊ እና መዝናኛ አገልግሎቶች ባሻገር በኮንስትራክሽን፣ ማዕድን ፍለጋ፣ ኢንሹራንስ እና የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ (ሪል ስቴት) ዘርፎች የማይናቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ያሉ ተቋማትም የሌላውን ዓለም ፈለግ እየተከተሉ ያሉ ይመስላሉ።  ከነዚህም መካከል የጤና ጥበቃ ሚንስትር አንዱ ነዉ። 


የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መድኃኒቶችን፣ ደም እና የህክምና ቁሳቁሶችን በቀላሉ ወደማይደረስባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች በድሮን የማጓጓዝ ውጥኑን ወደ ተግባራዊ ሙከራ ያሸጋገረዉ  ትናንት በተሸኘዉ 2019 ዓም ነበር። ድሮኖቹ ለታለመላቸው አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ከጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት ጋር በትብብር እየሰራ ያለው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  ከማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋርም ተመሳሳይ ስምምነት ፈጽሟል። 


ስምምነቱ ድሮኖች በነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ጥበቃ እና ክትትል ላይ እንዲሰማሩና  ከዚህ በተጨማሪም ድሮኖችን በማዕድን ፍለጋ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ነዉ።
ከዚህ ቀደም  በአውሮፕላን አማካኝነት ከአየር ላይ በሚነሱ ፎቶዎች እና የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም መረጃዎችን  ይሰበስብ የነበረው የግብርና ሚኒስቴርም  ድሮኖችን ለመጠቀም  መወሰኑን  በተሸኘዉ 2019 ዓ/ም አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን ሳተላይት አመጠቀች
ኢትዮጵያ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን ሳተላይት በቻይና ሀገር ከሚገኝ የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ በታኅሣሥ ወር ለማምጠቅ ማቀዷን፤ ሳተላይቷም ከህዋ ላይ ሆና መሬትን ለመመልከት የምታገለግልና  ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸውን መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንደምትውል የተገለፀዉ በተገባደደዉ የጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም ነበር።
የኢትዮጵያ የተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በመስከረም ወር መጨረሻ በጋራ ባደርጉት ስብሰባ  የኢትዮጵያ መንግስት በዓመቱ ውስጥ ሊያከናውናቸው ያሰባቸውን ዐበይት ጉዳዮች በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በኩል ገልጿል። የፕሬዝዳትነት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ መንግስት ዓመታዊ እቅድን መስከረም 26 ቀን 2012 በተካሄደው የሁለቱ ምክር ቤቶች ስብሰባ በዝርዝር ባቀረቡበት ወቅት  ከጠቀሷቸው እና የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሳተላይቷን በዚህ ዓመት ለማምጠቅ የማቀዷ ነበር። 


“የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሳተላይት በያዝነው ዓመት በታኅሣሥ 2012 ዓ.ም. በቻይና ከሚገኝ የማምጠቂያ ማዕከል ወደ ጠፈር የሚላክ ሲሆን ይህ ሳተላይት ለግብርና፣ ለደን ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት የሚያስፈልጉትን የሳተላይት መረጃዎች ለመቀበል ይውላል” ብለው ነበር ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በምክር ቤት መክፈቻ ንግግራቸው። 
በኢትዮጵያውያን እና ቻይናውያን መሐንዲሶች እንደተሠራች የተነገረላት ይኽች ሳተላይት በእንግሊዝኛ ምኅጻር (ETRSS1) ተብላ የምትጠራ መሆኗን ባለሞያዎቹ ገልጸዋል።ይህች ሳተላይት 72 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሲሆን በተቆረጠላት ቀን በጎርጎሮያኑ ዘመን አቆጣጠር ታኅሳስ 20 ቀን 2019 በሰሜን ምሥራቅ ቻይና ሻንሺ በተባለ  አውራጃ  በሚገኝ  የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ህዋ መላኳ ተበስሯል።

የሰው ልጅ ጨረቃን የረገጠበት 50ኛ ዓመት

 የሰው ልጅ ጨረቃን የረገጠበት 50ኛ ዓመት ሌላዉ በ2019 በዝግጅት ክፍላችን የቃኘነዉ ጉዳይ ነበር። የጨረቃ ጉዞ እና የህዋ ታሪክ የበላይነት ፉክክር ሲነሳ የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እና ዩናይትድ ስቴትስ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በህዋ ጉዞ የበላይነትን ለመጨበጥ የነበረውን እሽቅድምድም የቀዝቃዛው ጦርነት ፍጥጫ አንዱ መገለጫም ነበር።
ቦታው በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ኬፕ ካናቭራል የሚገኘው የኬኒዲ የህዋ ማዕከል ነው። በማዕከሉ እና አካባቢው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አፍንጫውን ወደ ሰማይ ያቀናውን “አፖሎ 11” የተሰኘውን መንኮራኮር በጉጉት ይመለከታሉ። ልክ እንደ እነርሱ ሁሉ ሚሊዮኖች በቴሌቪዥን መስኮቶቻቸው ፊት ተኮልኮለው ሁነቱን በቀጥታ ተከታትለዋል። ሦስት ጠፈርተኞችን የያዘው መንኮራኮር ያለምንም እንከን ወደ ህዋ ሲወነጨፍ ጭብጨባው ደመቀ። 
አፖሎ 11 መንኮራኮር ከ102 ሰዓታት እና 45 ደቂቃዎች ጉዞ በኋላ ከጨረቃ ሲያርፍ ለሰው ልጅ እስከዚያን ጊዜ ህልም የነበረው ጨረቃ ላይ የመድረስ እቅድ እውን ሆነ። ከደቂቃዎች በኋላ ከሦስቱ ጠፈርተኞች አንዱ የሆነው ኔል አርምስትሮንግ ጨረቃን በመርገጥ የመጀመሪያው ሰው በመሆን ታሪክ ሰራ። ባልደረባው በዝ አልድሪንም ተከተለው። የዓለምን ታሪክ ከቀየሩ ጉልህ ክስተቶች አንዱ የሆነው የመጀመሪያው የተሳካ የጨረቃ ጉዞም  በተገባደደዉ  2019  50ኛ ዓመቱን ደፍኗል።በጥር ወር አጋማሽ 2019 ዓ/ም  በሳይንስ መጽሔቶች (ጆርናሎች)  የታተሙ ሁለት ጥናቶች 60 በመቶ የሚሆኑት የጫካ ቡና ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ይፋ አድርገዋል። ጥናቶቹ ትኩረት ካደረጉባቸው ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ከ70 ዓመት በኋላ የቡና ዝርያዎቹ ተፈጥሯዊ መጠን በ50 በመቶ እንደሚቀንስ ተተንብዩዋል።
«ኪው» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የእንግሊዙ ዕውቅ የዕጽዋት ምርምር ተቋም ባለፈው ጥር ወር ለንባብ ያበቃቸው እነዚህ ሁለት የምርምር ውጤቶች ለቡና አፍቃሪዎች መልካም ዜናን ይዘው አልመጡም። በእውቅ የምርምር መጽሔቶች (ጆርናሎች) ላይ የታተሙት እነዚህ ጥናቶች ኢኮኖሚያቸው በቡና ላይ ለተመሰረተ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራትም የማንቂያ ደውል ሆነዋል።
“ሳይንስ አድቫንስ” በተሰኘው ጆርናል የታተመው የመጀመሪያው ጥናት በመላው ዓለም ካሉ የጫካ ቡና ዝርያዎች ውስጥ መቶ ሃያ አራቱ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ይፋ አድርጓል።  
በኢትዮጵያም የሚመረተው እና 60 በመቶውን የዓለም አቀፍ የቡና ግብይት የሚሸፍነዉ የአረቢካ ቡናም  የመጥፋት ስጋት ከተደቀነባቸው ውስጥ በዋነኛነት እንደሚጠቀስ “ግሎባል ቼንጅ” በተባለው የምርምር መጽሔት ለንባብ ያበቃው ሌላኛው ጥናት አመልክቷል። ትኩረቱን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገው ይህ ጥናት በኪው ተቋም አጥኚዎች እና በኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች የተደረገ ነው። 


የአካባቢ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የቡና ደን መድረክ በሚባል ሀገር በቀል ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ተመራማሪነት እየሰሩ ያሉት ዶ/ር ታደሰ ወልደማርያም ጥናቱን ካካሄዱት ባለሞያዎች አንዱ ናቸው። እሳቸዉ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ያለው የጫካ ቡና የተፈጥሮ መጠን በአየር ጸባይ ለውጥ፣ በተለያዩ በሽታዎች እና በደን ጭፍጨፋ ምክንያት ከ70 ዓመት በኋላ በ50 በመቶ እንደሚቀንስ ጥናቱ ያሳያል። የቡናው የተፈጥሮ መጠን ሲቀንስ በዚያው የሚጠፉ የቡና ዝርያዎች እንደሚኖሩም ጥናቱ ይጠቁማል።በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የጫካ ቡና ዝርያዎች ለመታደግ ከአሁኑ መሰራት እንዳለበትም  ተመራማሪው አሳስበዋል።
 

ኖ ቴክኖሎጂ ላሊበላን እና የብራና መጽሐፍትን ይታደግ ይሆን? 
በመንግስታዊው የኢትዮጵያ ባዩ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያሉ ተመራማሪዎች ቅርሶችን ከውኃ ከጸሀይ ብርሃን መከላከል የሚያስችል ኬሚካል በቅርቡ ፈብርከዋል። ኬሚካሉን በድንጋይም ላይም ሆነ እንደ ወረቀት ባሉ ቁሶች ላይ በመቀባት ቅርሶቹን ከመበላሸት መጠበቅ እንደሚቻል ተመራማሪዎቹ ይገልጻሉ። 
ባለሙያዎቹ  የናኖ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ነው ምርምራቸውን ሲያካሄዱ የቆዩት። አቶ ከበደ ጋሞ በመንግስታዊው የኢትዮጵያ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የናኖ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። የኢትዮጵያ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች የናኖ ቴክኖሎጂን የምርምር ውጤት ውኃን እና ጸሀይ ወደ ውስጥ እንዳይሰርግ የሚከላከል ኬሚካል ነው ይሉታል። ኬሚካሉ በድንጋይም ሆነ በብረት፣ በወረቀትም ሆነ በጨርቅ ላይ ከተቀባ አንድን ቁስ በውሃ እና በጸሀይ ብርሃን ከመበላሸት እንደሚታደግ ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ። የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንደ ምሳሌ ያነሱት አቶ ከበደ ኬሚካሉ እንዴት ቅርሱን ከጉዳት ሊከላከል እንደሚችል ያስረዳሉ።   


«ስንቀባው አንደኛ ዝናብ እንዳይጎዳው ያደርገዋል። ያ ማለት ውሃ ጠል ባህሪ እንዳለው፣ ዝናብ እንዳያጎረጉደው፣ እንዳይሰረጉደው ያደርጋል ማለት ነው።  ሁለተኛ ደግሞ ባክቴሪያዎችም ሆነ ፈንገሶች እዚያ ላይ ተጣብቀው እንዳይጎዱት ቅርሱን ያ ጸረ ባክቴሪያ (anti bacterial) ባህሪ ስላለው ይገለዋል ማለት ነው። እዚያ ላይ እንዳይራባ ያደርጋል።  በጸሀይ ደግሞ እንዳይጎዳ ሙሉ ለሙሉ የጸሀይ ብርሃኑ ሰርጎ እንዳይገባ እንዲያንጸባርቅ ያደርገዋል ማለት ነው።”
ኬሚካሉ በተለያዩ ቁሶች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ቢሆንም በቅርሶች ላይ በቀጥታ መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት  በቤተ ሙከራ ደረጃ ተጨማሪ ሙከራዎች እንደሚያደርጉ ባለሙያዎቹ ገልፀዋል።

የኒውክለር ጨረር ቴክኖሎጂን የተጠቀመው የጤፍ ምርምር
በደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል የኒውክለር ጨረር ቴክኖሎጂን የተጠቀመው የጤፍ ምርምር ባለፈዉ 2019 ዓ/ም ከቃኜናቸዉ ዝግጅት አንዱ ነዉ።
በጤፍ ዝርያዎች ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው የደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል  ላለፉት 40 ዓመታት 26 የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎች ወጥተዋል። 
የደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል በቅርቡም አዲስ የምርምር ውጤት ይዞ መጥቷል። በቤተ ሙከራ ደረጃ ሶስት ዓመታት የወሰደው ይህ የማዕከሉ ምርምር የኒውከለር ጨረር ቴክኖሎጂን የሚጠቀም መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። የምርምር ማዕከሉን በዳይሬክተርነት የሚመሩት ዶ/ር ሰለሞን ጫንያለው ይህን ምርምር ከሚያከናውኑ ሰባት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አንዱ ናቸው። 
“የምርምሩ ዋና ዓላማ ይህንን የኒውክለር ቴክሎጂን በተለይ የጨረር ቴክሎጂን ተጠቅመን የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን ማስገኘት ነው። በተለይ ከምርት ጋር ተያይዞ ድርቅን የሚቋቋም፣ ቶሎ ፈጥኖ የሚደርስ እንዲሁም መጋሸብን የሚቋቋም ዝርያ ማውጣት ነው። እና ይህንንም የሚቋቋም ዝርያ ለማውጣት ታስቦ ነው። ከዚያ ውጪ አንዱ የፕሮጀክቱ ዓላማ ደግሞ የጤፍን የምግብ ይዞታ (nutrient content) የምንለውን ለማሻሻል ነው” ይላሉ ።

24112006 PZ TEFF.jpg (DW-TV)


ለ60 ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያውያን ዋነኛ ምግብ የሆነው ጤፍ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ከአንድ ሄክታር የሚገኘው  ምርት በአማካይ ከ15 ኩንታል አይበልጥም።አዲሱ ምርምር  ይህንን የምርት መጠን ወደ 32 ኩንታል ከፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል። ዶ/ር ሰለሞን እና ባልደረቦቻቸው በአዲሱ ምርምራቸው የጤፍን የፕሮቲን መጠን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ይዘት ለመጨመር ሞክረዋል። 

የኖቤል ሽልማት በ2019  በኬሚስትሪ ዘርፍ 3 ሳይንቲስቶችን ሸልሟል። 
በዓለም ደረጃ በተለያዩ የሞያ ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የሚበረከተው የኖቤል ሽልማት በባለሙያዎች ዘንድ ከፍተኛ ክብር አለው። በ5 ዘርፎች የተከፋፈለው የኖቤል ሽልማት በ2019  በኬሚስትሪ ዘርፍ 3 ሳይንቲስቶችን ሸልሟል። 
ተሸላሚዎቹን ለዕውቅና ካበቋቸው ስራዎች ውስጥ በየሰው ኪስ እና ቦርሳ ከማይጠፋው የተንቃሳቃሽ (ሞባይል) ስልክ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። በአሁኑ ወቅት  መደበኛ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት  የተንቀሳቃሽ ስልኮች  ኃይል የሚያገኙት በባትሪያቸው ነው። እነዚህ ባትሪዎች “ሊትየም አየን” ከተሰኘ ንጥረ ነገር የተሰሩ ሲሆን፤  በስፋት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ለማድረግም የተመራማሪዎችን የዓመታት ጥረት ጠይቋል።


በሳይንሱ ዘርፍ ያሉ ባለሞያዎችን ለኖቤል ሽልማት የሚመርጠዉ የስዊዲን የሳይንስ አካዳሚ ለዚህ የተመራማሪዎች ድካም እና ውጤት በተገባደደዉ ዓመት ዕዉቅና  ሰጥቷል። የኖቤል የሽልማት ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ጎራን ሃንሰን በኬምስትሪ ዘርፍ የተመረጡ የእዚህ ዓመት የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎችን  መስከረም 28 ቀን 2019 ዓ/ም ይፋ አድርጓል።
“የሊትየም አየን” ባትሪ አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ በተለያየ ጊዜ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ተመራማሪዎች ሳይዘነጉ ነው። “የስዊዲን ሮያል የሳይንስ አካዳሚ የሊትየም አየን ባትሪን ለማሳደግ ለሰሩት ለጆን ጉድኢነፍ፣ ለስታንሊ ዊቲንግሃም እና አኪራ ዮሺኖ የ2019 የኖቤል የኬምስትሪ ሽልማት በጋራ እንዲሰጥ ወስኗል” ብለዋል።
ለሽልማት የበቁት ሦስቱም ተመራማሪዎች  ያበረከቱት አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ቢሆንም፤ ካሸነፉት ሦስቱ ተመራማሪዎች ውስጥ የ97 ዓመቱ ጆን ጉድኢነፍ  እስካሁን ኖቤል ከተሸለሙ 923 ሎሬቶች ውስጥ በእድሜ ትልቁ በመሆን ታሪክ ሠርተዋል። 


ፀሐይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

 

Audios and videos on the topic