የ2017 የአፍሪቃ ዓበይት ጉዳዮች ቅኝት | አፍሪቃ | DW | 23.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የ2017 የአፍሪቃ ዓበይት ጉዳዮች ቅኝት

ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚያበቃው ጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም በአፍሪቃ ብዙ አነጋጋሪ ኩነቶች፣ ውዝግቦች ጥቃቶች የታዩበት ዓመት ነው። አከራካሪ የፕሬዚደንታዊ ምርጫዎች አለመረጋጋት አስከትለዋል። የመገንጠል ፍላጎትም ታይቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:34

አፍሪቃ በ 2017 ዓም


በኬንያ እና ላይቤርያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫዎች የተገኘው አከራካሪ ውጤት በሀገራቱ  አለመረጋጋት አስከትለዋል። የእንግሊዝኛ ተናጋሪው የካሜሩን አካባቢ ህዝብ ከሀገሩ ተገንጥሎ ነፃ መንግሥት ለማቋቋም መወሰኑም ውዝግብ ፈጥሯል። በዚምባብዌም የጦር ኃይሉ በፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ አንጻር መፈንቅለ መንግሥት አካሂዷል።  በሶማልያ   መዲና ሞቃዲሾ  ባለፈው ጥቅምት ወር የተጣለው የፈንጂ ጥቃት  ከአንድ አሰርተ ዓመት ወዲህ የተካሄደው እጅግ አስከፊው ተብሏል።
በጥቃቱ ከ350 የሚበልጥ ሰው ሲገደል፣ ከ200 የሚበልጡም ቆስለዋል። ጥቃቱን የጣለው ግለሰብ ፈንጂ የጫነውን ተሽከርካሪውን ሆቴሎችን፣ ምግብ ቤቶች እና መስሪያ ቤቶች በሚገኙበት እንቅስቃሴ በደራበት መንገድ ላይ አፈንድቶ ብዙ ጥፋት አድርሷል። የመዲናይቱ ነዋሪዎች በጥቃቱ እጅግ ነው የተደናገጡት።
«ቅዳሜ ዕለት የተፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ነው ። ባለፉት 27 ዓመታት ይህን መሰል ነገር አላየሁም። የአንድ ህፃን ጭንቅላት መሬት ላይ ወድቆ፣  እናቱ እና ሌሎች ህፃናትም በፍንዳታው አካላቸው ተቆራርጦ ተመልክቼአለሁ።»

ለጥቃቱ እስካሁን በይፋ ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም። የሶማልያ ባለስልጣናት አሸባሪውን የአሸባብ ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል። ጥቃቱ የተጣለበት አካባቢ ተወላጅ የሆነ ግለሰብ የፈጸመው ጥቃት  የሶማልያ እና የዩኤስ አሜሪካ ጦር ኃይላት ከጥቂት ወራት በፊት ባካሄዱት ልዩ ዘመቻ ብዙ ሲቭሎችን ለገደሉበት ድርጊት  የበቀል ርምጃ ነው ተብሎ ይታሰባል።  ጥቃቱን ተከትሎ የዩኤስ አሜሪካ ኃይላት የአብራሪ የለሽ ጦር አይሮፕላን የአሸባብ መሸሸጊያ ናቸው በተባሉ አካባቢዎች በረራቸውን አጠናክረዋል። የኃይሉ አዙሪት እንደቀጠለ ነው። ረሀቡም እንዲሁ። የኃይል ተግባር እና ባካባቢው በተከሰተው ድርቅ የተነሳ በሶማልያ እና በደቡብ ሱዳን ብዙ ሰዎች የምግብ ርዳታ ጠባቂ ሆኗል።

ናይጀሪያም በ2017 እንደገና የአሸባሪዎች ጥቃት ሰለባ ሆናለች። የቦኮ ሀራም ሚሊሺያዎች ከሶስት ዓመት በፊት ካገቷቸው የቺቦክ ልጃገረዶች መካከል  82ን ባለፈው ግንቦት ወር ለቀዋል። ከ100 የሚበልጡት ግን አሁንም የት እንዳሉ አይታወቅም። የቦኮ ሀራም ሚሊሺያዎች ከዚህ ሌላም በሰሜናዊ ምሥራቃዊ ናይጀሪያ የቀጠሉት የሽብር ጥቃትበሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሽሽት እና መፈናቀል በመዳረጉ፣ ብዙ ያካባቢው ነዋሪዎች  በምግብ ርዳታ ላይ ጥገኛ ሆነዋል።  በዚህም የተነሳ የጸረ ሽብርተኝነት ትግሉ በመንግሥቱ አጀንዳ ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ መያዙንየሀገሪቱ  ፕሬዚደንት መሀማዱ ቡሀሪ አስታውቀዋል።


« እኛ ብዙኃኑ በሰላም እና በደህንነት እንድንኖር፣  ሽብርተኞችን እና ወንጀለኞችን መዋጋት እና መደምሰስ አለብን። »    
ይሁን እንጂ ናይጀሪያውያን ቡሀሪ ለብዙ ወራት ለህክምና ለንደን የነበሩት ፕሬዚደንቱ ኅብርተኝነትን ውጤታማ በሆነ መንገድ  ለመታገል አቅሙ አላቸው ወይ ሲሉ ማጠያየቅ ይዘዋል። ስለፕሬዚደንቱ ህመም ከመገመት በስተቀር ሁነኛ መረጃ የሌለው ህዝብ በመንግሥቱ ቅር መሰኘቱን የሲቭል ማህበረሰብ መረብ የተባለው  መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ባልደረባ ኤሞስ ኪንግስሊ አስረድተዋል።
« አለመታደል ሆኖ የዚህች ሀገር መሪዎች ህዝባቸውን ያጭበረብራሉ። ይህ ግን የመጨረሻ አማራጭ ሆኖ መታየት የለበትም። ህዝብን ለማስተዳደር ብቁ ካልሆንክ፣  ከስልጣን ውረድ እና ቢያንስ ችሎታ ያለው ሰው ስልጣኑን ይያዝ ነው የምንለው።»
በናይጀሪያው ፕሬዚደንት መሀመዱ ቡሀሪ አንጻር የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ሌላ ዓይነት ችግር ገጥሟቸዋል። ዙማ እና ወዳጃቸው ባለጸጋው ባለተቋም የጉብታ ቤተሰብ በሙስና ቅሌት  ውስጥ ተዘፍቀዋል። እርግጥ የተቃዋሚው ወገን  በሙስና የሚወቅሳቸው ፕሬዚደንት ዙማ የመሪነት የመታመኛ ድምፅ እንዲነፈጋቸዉ  በምክር ቤት ያቀረበባቸውን የመታመኛ ድምፅ ቢያሸንፉም፣ ህጋዊ ያልሆነ ገንዘብን ህጋዊ የማድረግ፣ ዘመድ አዝማድ የመጥቀም እና ስልጣናቸውን አላግባብ አውለዋል የሚል ሌላ ክስ ተነስቶባቸው ነበር።  እርግጥ ዓቃቤ ሕግ ክሱን በ2009 ቢያስቆሙም፣ ላዕላዩ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ውድቅ አድርጎታል ። ይህም የተቃዋሚው ወገን ጉዳዩ እንደገና በፍርድ ቤት ይታይ ሲል ጥያቄ እንዲያቀርብ ጥሩ ዕድል እንደከፈተለት የዴሞክራቲክ አላያንስ ፓርቲ መሪ ሙምሲ ማይማን አስታውቀዋል።  

    
« ጄኮብ ዙማ ተከሰው በተቻለ ፍጥነት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ብሔራዊውን የዓቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት እና  የብሔራዊ ዓቃቤ ሕግ ዳይሬክተርን በጽሁፍ እጠይቃለሁ። »
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የደቡብ አፍሪቃ ገዢ ፓርቲ የደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃዉያን ብሔራዊ ምክር ቤት ወይም ኮንግረስ ፣ ኤኤንሲ ሰሞኑን ምክትል ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛን አዲሱ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል። ቀጣዩ የሀገሪቱ መሪ ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱት ራማፎዛ ሙስናን እንደሚታገሉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
በኬንያ በአከራካሪው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት የተነሳ በፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና በተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረው የሰው ህይወት ያጠፋው ውዝግብ ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ  መልስ አግኝቷል። 
« እኔ፣ ኡሁሩ ኬንያታ የሚጠበቅብኝን ከፍተኛ ተግባር በመገንዘብ የኬንያ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንትነትን ስልጣን እቀበላለሁ።  »

ኡሁሩ ኬንያታ ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት ስነ ስርዓት ለሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው ቃለ መሀላ ፈጽመዋል። ምንም እንኳን ኬንያታ ባለፈው ነሀሴ በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ድጋሚ ቢመረጡም፣ ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ከከሰሱ በኋላ ፣ ላዕላዩ ፍርድ ቤት የምርጫውን ውጤት መሰረዙ ይታወሳል።
« «ከዚህ የሚከተለዉ ዉሳኔ ተላልፏል። ነሀሴ ስምንት፣ 2017 ዓም የተደገረዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ሕገ መንግሥቱና ተገቢዉ ሕግ በሚያዙት መሠረት ባለመደረጉ የታወጀዉ ዉጤት ዋጋ ቢስ፤ ተቀባይነት የሌለዉ እና ዉድቅ ነዉ። »
ምርጫውም ባለፈው ጥቅምት ወር ድጋሚ እንዲደረግ ቢወስንም፣ ኦዲንጋ ራሳቸውን ከምርጫው በማግለላቸው፣ ኬንያታ ካለተፎካካሪ ተወዳድረው በ98% ድምፅ አሸንፈዋል። ውጤቱም ጸንቷል። ይሁንና፣ ውጤቱ በሀገሪቱ ውስጥ መከፋፈል አስከትሏል። ከነሀሴ ወዲህ በኦዲንጋ ደጋፊዎች እና በፖሊስ መካከል  በተፈጠረ ግጭት ከ50 የሚበልጡ ሰዎች ሞተዋል። ኬንያታ ይህን ክፍፍል ማስታረቅና ah,ገሪቱን አንድ ማድረግ መቻላቸው አጠያያቂ ሆኗል።

በምዕራብ አፍሪቃ ደግሞ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ በጋምቢያ አዳማ ባሮው ሀገሪቱን ለ22 ዓመታት የመሩትን የቀድሞ ፕሬዚደንት ያህያ ጃሜን ተhkeተዋል። ጃሜህ በምርጫ ቢሸነፉም፣ የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበር፣ ኤኮዋስ ጣልቃ እስኪገባ ድረስ፣ ስልጣናቸውን  ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልነበሩም። አዲሱ ፕሬዚደንት አዳማ ባሮው በሀገሪቱ ተሀድሶ የማድረግ ቀላል ያልሆነ ስራ እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል።
«በጋምቢያ 22 ዓመት ስልጣን ይዞ የቆየ መንግሥት ነበር። 22 ዓመት ረጅም ጊዜ ነው። ስለዚህ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ የታወቀ ነው። የመንግሥቱን አውታሮች ሁሉ የመመልከቱ እና አጠቃላይ ለውጥ የማድረጉ ተግባር ለአዲሱ መንግሥቴ ትልቅ ተግዳሮት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። »
በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ የስልጣን ዘመናቸው ታህሳስ 2016ዓም ቢያበቃም፣  የተለያዩ ምክንያቶች በማቅረብ የምርጫውን ጊዜ እንዲገፋ አድርገዋል። ምርጫው አሁን ለ2018ዓም መጨረሻ ተወስኗል። ከብዙ ዓመታት ወዲህ ቀውስ ባልተለያት ሀገር ውስጥ ሁኔታዎች አሳሳቢ መሆናቸውን ብሪታንያዊው የኮንጎ አጥኚ ፊል ክላርክ አስጠንቅቀዋል።
« የኮንጎ መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎች መከልከሉ በወቅቱ ሕዝቡ በሚያሳየው ግዙፍ  ቅሬታ ምን ያህል መስጋቱን ያመለክታል። ፕሬዚደንት ካቢላ የሕዝቡ ቁጣ እየተጠናከረ መምጣቱን የተገነዘቡ ይመስለኛል። ሕዝቡ  ምርጫ በመዘግየቱ ተበሳጭቷል።  ካቢላ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ሲሉ ሕገ መንግሥቱን ሊቀይሩ ይችላሉ ብሎም ሰግቷል። » 

ሁለት የስልጣን ዘመናቸውን ያበቁትን ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን ለመተካት ከተወዳደሩት 20 ዕጩዎች መካከል  የቀድሞዉ የዓለም ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዌይ እና ምክትል ፕሬዝደንት  ጆሴፍ ቦካይ የፊታችን ማክሰኞ በሁለተኛ ዙር ይወዳደራሉ።

ባለፈው ህዳር ሰባት፣ 2017 መደረግ የነበረበት 2ኛው ዙር ምርጫ ፣ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል አንድ ፓርቲ ተቃውሞ ከቀረበ በኋላ ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ  መተላለፍ ግድ ነበረበት። ይሁን እንጂ፣ ይኸው ሁኔታ ያስከተለው ውዝግብ እስከ 2003 ዓም ድረስ በርስ በርስ ጦርነት ተመሰቃቅላ በነበረችው ላይቤሪያ ውስጥ ህጻናት ሳይቀሩ በውጊያ ተግባር የተሰለፉበት ያለፈው አስከፊ ታሪክ እንደገና እንዳይመለስ ብዙዎች መስጋታቸውን  ሴቶች ለሰላም ግንባታ መረብ የተሰኘው ድርጅት ተሟጋች ቤያትሪስ ጆንሰን በመግለጽ፣ ፖለቲከኞች ሀገሪቱን ከዚህ ዓይነት ሁኔታ የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
«የምርጫውን ውጤት መቀበል አለባቸው። ልጆቻችን እንደገና ወደ ጦርነት አውድማ እንዲገቡ ማድረግ የለባቸውም። ላይቤርያ ሀገራችን ናት። የምንሄድበት ሌላ ሀገር የለንም። ስለዚህ ልጆቻችንን እርስበርስ እንዲዋጉ መገፋፋት የለባቸውም፣ በዚህ ፈንታ ሰላማዊ ምርጫ የሚደረግበትን መንገድ ማዘጋጀት ነው ያለባቸው። ምክንያቱም ሰላማዊ ምርጫ በምናካሂድበት ጊዜ ልጆቻችንም በሰላም ሊኖሩ ይችላሉ። »

ለማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ህዝብ የርስበርስ ጦርነት የዕለት ኑሮው ሆናል። ከ2013 ዓም ወዲህ የቀጠለው ውዝግብ በሆነ ወቅት ቀንሶ ነበር ፣ ይሁንና፣ የሂውመን ራይትስ ዎች ባልደረባ ልዊስ መጅን የመሳሰሉ ታዛቢዎች እንደገለጹት፣ ካለፈው ነሀሴ  ወዲህ የኃይሉ ተግባር እየተባባሰ ሄዷል። 
« በማዕከላይ አፍሪቃዊት ሬፓብሊክ ከ2014 ዓም መጀመሪያ ወዲህ  ያየነው ዓይነት አስከፊ ውጊያ በወቅቱ እያየን ያለን ይመስለኛል። እንደሚታወሰው፣ በ2013 መጨረሻ እና በ2014 መጀመሪያ ገደማ ማዕከላይ አፍሪቃዊት ሬፓብሊክ ላጭር ጊዜ ብቻ ነበር በዓለም አጀንዳ  ውስጥ የተነሳችው። ከዚያ በኋላ ሁኔታዎች ለሁለት ዓመታት ያህል ተረጋግተው ነበር። አሁን ግን፣ ሁኔታው በተለይ በሀገሪቱ ምሥራቃዊ እና ደቡብ ምሥራቃዊ አካባቢዎች በጣም ተበላሽቷል። »
በሀገሪቱ የተሰማሩት የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ አባላት ፀጥታ ለማረጋገጥ አልቻሉም። ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸዋል፣ በዚህም የተነሳ ህዝቡ የራሱን ተከላካይ ሚሊሺያዎች ማደራጀት ይዘዋል። ይህ ደግሞ በራሱ የሀገሪቱን ሁኔታ ይበልጡን እንዲበላሽ አድርጓል።  

« እኔ አመርሰን ዳምቡድዞ ምናንጋግዋ እንደ ዚምባብዌ ፕሬዚደንትነቴ ታማኝ ሆኜ ለማገልገል ቃል መሀላ እፈጽማለሁ። »
በ2017 ዓም መጀመሪያ ላይ ማንም ይህ እውን ይሆናል ብሎ ባላሰበ ነበር። ከ37 ዓመት በኋላ የጦር ኃይሉ የረጅም ዓመቱን መሪ ሮበርት ሙጋቤ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ገፋፍቷል። ሙጋቤን ለዚህ ያበቃው ባልተቤታቸውን ግሬስን ተተኪያቸው ለማድረግ ሲሉ ምክትላቸውን ምናንጋግዋን ከስልጣን ማንሳታቸው ነው። ሕዝቡ ቃለ መሀላ ከፈጸሙት አዲሱ ፕሬዚደንት ብዙ ይጠብቃል።
«የወደፊቱ ሁኔታ ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ አለን። ምክንያቱም ሚስተር ምናንጋግዋ ብዙ ነገር ለመስራት ቃል ገብተውልናል። በተለይ ስራ እንደሚፈጥሩ በአጽንዖት ገልጸዋል። ስራ እንደሚያስፈልገን፣ አሁን ካለው በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ስራ ቦታ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ብዙ የስራ ቦታ እንደሚፈጠርልን እና ብሩህ የወደፊት ሁኔታ እንደሚኖረን ተስፋ አድርገናል።»
« ይህ ለብዙ ጊዜ ስንጠብቀው የቆየነው ለውጥ ነው። ይህ በዚህ ሳምንት እውን የሆነ ተዓምር ነው። እና ብዙ ጥሩ ነገሮች እንደሚሰሩ እንጠብቃለን።»
የፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን ማብቃት ዚምባብዌ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በብዙ አፍሪቃ ሀገራትም በተለይ ርዕሳነ ብሔሮቻቸው ከብዙ አሰርተ ዓመታት ወዲህ ስልጣኑን የሙጥኝ ብለው በያዙባቸው ተስፋ ፈንጥቋል። ለምሳሌ በካሜሩን፣ ካለፉት 35 ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱን የሚመሩት ፕሬዚደንት ፖል ቢያ ሙጋቤን ከገጠማቸው እጣ ትምህርት ሊወስዱ ይገባል ብሎ የሀገሪቱ ህዝብ እንደሚያስብ ካሜሩናዊው ቦኒፋስ እምቤይ አስታውቀዋል።
«በካሜሩን የሚታየው ሁኔታ ከዚምባብዌ ብዙም አይለይም። የምንጸልየው በካሜሩን የሀገር አስተዳደሩን ስራ የሚያከናውኑት ወገኖች በስልጣን ብዙ ጊዜ መቆየታቸውን እንዲገነዘቡት ነው። የመንግሥቱን አውታር በአዲስ መልክ ማዋቀር ይኖርባቸዋል።»


 ካሜሩን ውስጥ ግን ዓቢይ መወያያ ሆኖ የቆየው ጉዳይ በደቡብ ምዕራብ ካሜሩን የሚገኘው እንግሊዝኛ ቃንቋ ተናጋሪ አካባቢ የቀጠለው ውዝግብ ነው። በዚሁ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው ቡድን አባላት ባለፈው ጥቅምት ወር የአምባዞንያ ሬፓብሊክን ማቋቋማቸውን ይፋ ካደረጉ ወዲህ ብዙዎች ተገድለዋል። የዚሁ አካባቢ ህዝብ በጠቅላላ ነፃ መንግሥት የማቋቋሙን ሀሳብ ባይደግፉትም፣ አድልአዊ አመራር ይከተላል በሚሉት የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ተጽዕኖ በተጠናከረበት የካሜሩን መንግሥት አንጻር ግዙፍ ቅሬታ እንዳላቸው ኤቡን ፍራንሲስ ገልጸዋል።
«  መንግሥቱን ስንደግፍ ቆይተናል። ነገር ግን ምንም ጥቅም አላመጣልንም። ለዚህ ነው ቅር የተሰኘነው። መንግሥት ችላ ብሎናል። ውኃ፣ ኮሬንቲ የለንም። እና በዚህ መንግሥት ደስተኛ ልንሆን አንችልም።»
የካሜሩን ፖሊስ የሚወሰደው ከልክ ያለፈ የኃይል ተግባር  ሁኔታውን ይበልጡን እንዳባባሰውም ኒየክ ጆርጅ  ይናገራሉ። 
« ስራቸውን በተጋነነ ሁኔታ እየሰሩ ነው። ሰዎች ታስረዋል፣ አንዳንዴም ካለበቂ ምክንያት፣ የቁም ስቅል አይተዋል ተደብድበዋል። ይህ ትክክል አይደለም። »
ፕሬዚደንት ፖል ቢያ እስካሁን ከተገንጣዮች ጋር በሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ለመወያየት ዝግጁ አልሆኑም። የኃይሉ ተግባር ግን የካሜሩንን ችግር መፍታቱ አጠያያቂ እንደሆን ይገኛል።
አርያም ተክሌ/ያን ፊሊፕ ቪልሄልም
እሸቴ በቀለ
 

Audios and videos on the topic