የ2014 የዓለም የሰብዓዊ መብት ይዞታ | አፍሪቃ | DW | 30.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የ2014 የዓለም የሰብዓዊ መብት ይዞታ

ጎርጎሪዮሳዊዉ 2014ዓ,ም ለአፍሪቃ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ አስጨናቂ ዘመን እንደነበር ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተመልካች ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ዎች አመለከተ።

ድርጅቱ ይህን የገለፀዉ ያለፈዉን ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የአህጉሪቱን የመብት በቃኘዉ ዘገባዉ ነዉ። በዚህ ዓመት አፍሪቃ ዉስጥ የደረሱ ጥቃቶችና የመንግሥት ኃይሎች መብትን የጣሰ ምላሾች ታክለዉበት የሰብዓዊ መብቶች ይዞታዉን የከፋ እንዳደረጉት ሂዉማን ራይትስ ዎች በዘገባዉ አመልክቷል።

ያለፈዉን ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2014ን መለስ ብሎ የቃኘዉ 656 ገፆች ያሉት የሰብዓዊ መብቶች ይዞታን የተመለከተዉ ዘገባ በዓለማችን ከ90 የሚበልጡ ሃገራትን ሁኔታ የዳሰሰ ነዉ። በተለይ ክፍለ ዓለም አፍሪቃን በተመለከተ ባሰፈረዉ ዝርዝር፤ በአፍሪቃ ደቡባዊ አካባቢ የሚገኝ እያንዳንዱ ሀገር የሰብዓዊ መብቶች ይዞታዉን ለማሻሻል ያን ያህል አጥጋቢ እርምጃ አለመዉሰዱ ስጋት እንዳሳደረበት ድርጅቱ ጠቁሟል። ጆሀንስበርግ ደቡብ አፍሪቃ ላይ ይፋ የተደረገዉ ዘገባ ዚምባብዌ፣ አንጎላ እና ደቡብ አፍሪቃ በዚህ ረገድ በተሳሳተ አቅጣጫ ያሉ ሃገራት መሆናቸዉንም አመልክቷል። የሂዉማን ራይትስ ዎች የሕግ አማካሪ ኤስሊንግ ራይዲ በተጠቀሰዉ ዓመት የደቡብ አፍሪቃ ሃገራት በዚህ ረገድ ያደረጉት እንቅስቃሴ ያን ያህል አጥጋቢ የሚባል እንዳልሆነ ይናገራሉ።

«በአረቡ ዓለም ከታየዉ የፖለቲካ መነሳሳት አኳያ ከነበረዉ አዎንታዊ ግምት በ2014 በጣም ፈታኝ እንደነበር አስባለሁ። የኤቦላ ቀዉስን ብንመለከት ለሱ የሚሰጠዉ ምላሽ ዴሞክራሲና መረጋጋትን ኖሮ መብቶች ካልተከበሩ ዉጤት አይኖረዉም። እናም በእኔ ግምት ክፍለ ዘመኑ ሲጀመር ጀምሮ ያልነበረዉን ቀዉስ 2014 እንዳላመጣዉ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።»

በሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ዘገባዉ መሠረት አግባብ ያለዉ አፈፃፀም ካላሳዩ ሃገራት አንዷ ደቡብ አፍሪቃ ናት። እንደዘገባዉ ሀገሪቱ የዜጎቿን ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ መብቶች ማስጠበቅ ተስኗታል። የሀገሪቱ ፖሊስ የተካሄዱ ተቃዉሞና ረብሻዎችን ለመበተን እንዲሁም መሠረታዊ መብቶችቻችንን ተነፍገናል ባሉ ወገኖች ጥገኝነት ጠያቂዎች ና ስደተኞች ላይ ሁሉ ኃይል የተቀላቀለበት ርምጃ ወስዷል። በተጠቀሰዉ ዓመት በዚምባብዌ ቢሆን ጥሩ መገር እንዳልታየ የድርጅቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ዴዋ ማቪንጋ ገልጸዋል።

«መንግሥት የሕዝቡን መሠረታዊ መብቶች እንኳን ማሟላት አልቻለም። ለምሳሌ ዉኃና የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት፣ በዚያ ላይ በስፋት የተካሄደዉ ሰዎችን ከቦታዉ ማፈናቀል። ከግድቡ አካባቢ 20 ሺ የቶካዌ ሙኮሲ ሰዎችን ከማዛዌ እርሻ መንቀል፣ ነገር ግን አሁንም ፍፃሜዉን የማየቱ ነገር እጅግ አስቸጋሪ ነዉ።»

ከዚህም ሌላ ዘገባዉ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ዉስጥ በተለይ በቅርቡ መንግሥት የተነሳበትን ተቃዉሞ ለመበታተን የተጠቀመበትን ሕገወጥ እና ከመጠን ያለፈ ኃይልም ተችቷል። አንጎላ ዉስጥ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ ነፃነት፣ የመሰብሰብና ማኅበር የማቋቋም መብት ላይ የደረሰዉን መዋከብም ጠቅሷል። ኢትዮጵያ ዉስጥም እንዲሁ ሃሳብን በፃነት የመግለፅ መብትና መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ አደጋ ላይ እንደሆኖ ያመለከተዉ የሂዉማን ራይትስ ዎች ዘገባ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2012ዓ,ም ወዲህ ለዉጥ ሊኖር ይችላል የሚለዉ ግምት ምንም ፍንጭ እንዳላሳየም ዘርዝሯል። በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ ነፃነት ጥያቄ ላይ ከወደቀ መቆየቱን፤ የዘፈቀደ እስርና በእስረኞች ላይ የሚፈፀመዉ መጥፎ አያያዝም የሀገሪቱ ዋነኛ ችግሮች ሆነዉ መቀጠላቸዉንም ገልጿል። አያይዞም ዘገባዉ በክፍለ ዓለም አፍሪቃ የሰብዓዊ መብቶችን በማስከበሩ ረገድ ችግሮች መኖራቸዉ ከቀጠለ ሃገራቱ ከግጭትና አለመራራጋት ጋ መፋለማቸዉ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

ቱሶ ኩማሎ /ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic