የ2014 የአፍሪቃ ዓበይት ክንውኖች | አፍሪቃ | DW | 20.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የ2014 የአፍሪቃ ዓበይት ክንውኖች

2014 ዓም የዓለም አቀፉ ትኩረት በአፍሪቃ ላይ ያረፈበት ዓመት ነበር። ዓመቱ አራተኛው የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ ጉባዔ፣ የመጀመሪያው የዩኤስ እና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባዔ የተካሄደበት፣ ከፍተኛ የአፍሪቃ ባለሥልጣናት

እና የዓለም መሪዎች በሀገሮቻቸው መካከል ጉብኝት ያደረጉበት፣ አፍሪቃ ከቆዩ አጋሮችዋ እና እያደጉ ከመጡ አዳዲስ መንግሥታት ጋር የጋራ የንግድ ግንኙነቷን እና ወረት የማሳደግ ጥረቷን ያጠናከረችበት ነበር።ይሁን እንጂ፣ከዚሁ አዎንታዊ ሂደት ጎን በርካታ አሳሳቢ ሁኔታዎችም የታዩበት ዓመት ነበር። በምዕራብ አፍሪቃ ለብዙ ሽዎች ሞት ተጠያቂ የሆነው አስከፊው የኤቦላ ወረርሽኝ መከሰት፣ በደቡብ ሱዳን እና በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የርስበርሱ ጦርነት እና ቀውስ መቀጠል፣ በናይጀሪያ የአሸባሪው ድርጅት ቦኮ ሀራም ጥቃት መጠናከር በቡርኪና ፋሶ ምክር ቤቱ በእሳት መጋየትን ለመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። .

መጋቢት 2014፣ በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጊኒ የኤቦላ ወረርሽኝ ዲ,ታየባት የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗ ይፋ ሆn። የወረርሽኙ አስተላላፊ ተኀዋሲ ተፋጥኖ በመስፋፋት ወደ ጎረቤት ላይቤሪያ እና ሲየራ ልዮን ተዛመተ። ጥቂት ጊዜ እንዳለፈም ሌሎች አፍሪቃውያት ሀገራት፣ እንዲሁም፣ አውሮጳ እና ዩኤስ አሜሪካም አንዳንድ ዜጎቻቸው በኤቦላ ወረርሽኝ መያዛቸውን በተናጠል አስታወቁ። የተመድ ዋና ጸሐፊ ፓን ኪ ሙን የኤቦላ ወረርሽኝ አሳሳቢእንደሆነ እና ልዩ ርምጃ እንደሚያስፈልገው ባለፈው መስከረም በጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ በተካሄደ አንድ ልዩ ስብሰባ ላይ አስገነዘቡ።

«ወረርሽኙ እስከዛሬ በዓለም ከተከሰተው ሁሉ እጅግ የከፋ ነው። በወረርሽኙ አስተላላፊ ተኀዋሲ የሚያዘው ሰው ቁጥር በየሶስት ሳምንቱ በእጥፍ እየጨመረ ነው። አሁን በላይቤሪያ በተኀዋሲው የሚያዘው ሰው ቁጥር በሽታው መኖሩ በታወቁባቸው ባለፉት አራት አሰርት ዓመት ከተያዘው ሰው ይበልጣል። የሰው ሕይወት ለማትረፍ እና ሰላም እና ፀጥታን ለማስከበር ይቻል ዘንድ ለዚህ ያልተጠበቀ ሁኔታ ሁነኛ ርምጃዎች ያስፈልጋሉ። በዚህም የተነሳ ይኸው ዓለም አቀፍ ተልዕኮ «የተመ የኤቦላ ተልዕኮ » የሚባል አንድ የተመድ አስቸኳይ የጤና ተልዕኮ ለማቋቋም ወስኛለሁ። »

በዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት፣ «ዳብል ዩ ኤች ኦ» ዘገባ መሠረት፣ እስከያዝነው ታህሳስ ወር ድረስ ከ17,000 የሚበልጥ ሰው በተኀዋሲው ሲያዝ፣ ከዚሁ 6,000 መሞቱ ይፋ ሆኖዋል። በተኀዋሲው የተያዙት እዚህ አውሮጳ ውስጥ በተከፈቱ ልዩ ክሊኒኮች ህክምና ሲደረግላቸው፣ ምዕራብ አፍሪቃ የገጠመውን ህሙማንን የሚያስታምሙ ሀኪሞች፣ የጤና ረዳቶች እና ህሙማኑ የሚታከሙባቸው የተከለሉ ክሊኒኮች እጥረት ችግር ለማሸነፍ ሲታገል ይታያል። ይኸው እጥረት እጅግ አስከፊ መዘዝ አስከትሎዋል። እጅግ ብዙ ሕፃናት ካለወላጅ ቀርተዋል፣ በሌሎች ወባን እና ታይፈስን በመሳሰሉ በሽታዎች የሚሰቃዩ ሰዎችም የሚያክማቸው አጥተዋል፤ የላይቤሪያ፣ ጊኒ እና ሲየራ ልዮን ኤኮኖሚሚም ተንኮታኩቶዋል። የተጠቂዎቹ ሀገራት ሕዝቦችም በሽታውን ለመከላከል ያስችላል በሚል ተመራማሪዎች እና የመድሀኒት አምራች ኩባንያዎች ባወጡት እና አሁን በሙከራ ላይ በሚገኘው ክትባት ላይ ተስፋቸውን ጥለው ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

ነፃነቷን ካወጀች ሶስት ዓመት በሆናት በደቡብ ሱዳን ታህሳስ 15፣ 2013 ዓም የፈነዳው እና በ2014 ዓም ተጠናክሮ የቀጠለው የርስበርስ ጦርነት ወደ ሁለተኛ ዓመቱ ተሸጋገረ። የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ምክትላቸው ሪየክ ማቸርን መፈንቅለ መንግሥት አሲረዋል በሚል በወነጀሉበት ጊዜ በሁለቱ ባለሥልጣናት ደጋፊዎች መካከል ለተጀመረው ውጊያ በተፋላሚዎቹን ወገኖች መካከል የሽምግልና ጥረት በጀመረው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ፣ በምሕፃሩ ኢጋድ ድርድር የተደረሱ የተኩስ አቁም ስምምነቶች በመጣሳቸው ሙከራዎቹ እስከዛሬ እንደከሸፉ ይገኛሉ። ተፋላሚዎቹ ወገኖች ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ አለመሆናቸው በደቡብ ሱዳን የተመድ ተጠሪ፣ ኤድመንድ ሙሉትን እጅግ አስቆጥቶዋል።

ከሶስት የነፃነት ዓመታት በኋላ ደቡብ ሱዳን አሁን በሰብዓዊ ቀውስ እና ሊጓተት በሚችል ጦርነት አፋፍ ላይ ትገኛለች። ይህ ሰው ራሱ የፈጠረው ቀውስ ነው። »

ኢጋድ ለደቡብ ሱዳን ውዝዝብ መፍትሔ ለማስገኘት በወቅቱ ሶስተኛውን የድርድር ዙር በጀመረበት ባሁኑ ጊዜ የሪየክ ማቸር ደጋፊዎች ከጁb ወደ ኒሙል በሚወስደው መንገድ ላይ ጥቃት መጀመራቸውን ያማፅያኑ ቡድን ገልጾዋል። ሰሞኑን አንድ ዓመት በሆነው የደቡብ ሱዳን የርስበርስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን ሲያጡ፣ 1,3 ሚልዮን ሕዝብ ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰዶዋል።


በናይጀሪያ የሚንቀሳቀሰው ፅንፈኛው የሙሥሊሞች ቡድን «ቦኮ ሀራም» እአአ ሚያዝያ 16፣ 2014 ዓም በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከምትገኘው የቺቦክ ከተማ ከ200 የሚበልጡ ልጃገረዶችን አገተ። ልጆቻቸው ትምህርት እንዲማሩላቸው የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረጋቸውን ሁለት ልጆቻቸው በቡድኑ በኃይል የተወሰዱባቸው አንድ አባት ገልጸዋል።

« ሁለት ልጆች አሉኝ፣ ትምህርታቸውን ሊጨርሱ ተቃርበው ነበር። የመታገታቸው ዜና በጣም አስደንግጦኛል። እነሱን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ስል መሬቴን ሸጫለሁ። »

የልጃገረዶቹ መታገት እንደተሰማ ወዲያው «ልጆቻችንን መልሳችሁ አምጡልን ወይም «Bring Back Our Girls» የሚል ዓለም አቀፍ ዘመቻ በመገናኛ መረቦች መጀመሩ የሚታወስ ነው። የናይጀሪያ መንግሥት ከዘጠኝ ወራት እገታም በኋላ፣ ምንም እንኳን ላጃገረዶቹ ያሉበት ቦታ ይታወቃል ቢባልም፣ ልጃገረዶቹን ማስፈታት ባለመቻሉ ብዙ ናይጀሪያውያን እጅግ ቅር እንደተሰኙ ይገኛሉ። ልጆቹን ለማስፈታት እንደሚታወቀው ከአጋቾቹ ጋር የተካሄዱት ድርድሮች ፍሬ አልባ ሆነው ነው የቀሩት። የፕሬዚዳንት ጉድላክ መንግሥት ልጆቹን ለማስፈታት እየሰራ መሆኑን እንደሚጠራጠሩት ነው በምሕፃሩ APC የተራማጆች ኮንግረስ የተባለው የተቃዋሚው ፓርቲ የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ ዲኖ ሜላዬ ያስታወቁት።

« መንግሥት እና ፕሬዚዳንቱ በበቂ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ አይደለም ። የፀጥታ አስከባሪ ድርጅቶች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እየረወጡ አይደለም። ፕሬዚዳንቱ ልጃገረዶቹ ተመልሰው እንዲመጡ ከመታገል ይልቅ በሚመጣው ዓመት በሚደረገው ምርጫ ተጠምደው ይገኛሉ ለማለት እደፍራለሁ።»

የቦኮ ሀራም ጥቃቶችም እየተበራከቱ የመጡበት ድርጊት በጥቃቱ የሞተውን ሰው ጥር ከፍ አድርጎታል። ግዎዛን የመሳሰሉ ዋነኛ የሰሜን ናይጀሪያ ከተሞች በዚህ ወር በቦኮ ሀራም ቁጥጥር ከገቡ ወዲህ፣ በ2015 ዓምህረቱ ምርጫ እንደገና የሚወዳደሩት ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ውሳኔን እንዳገኙ ባካባቢው ያወጁትን የአስቸኳይ ጊዜ ለማራዘም እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

የሙስሊሞቹ የሴሌካ ዓማፅያን እና የክርስትያኖቹ ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች እአአ ታህሳስ 2013 ዓም አስከፊ ጭፍጨፋ ያካሄዱባት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ 2014 ዓምን የጀመረችው በአዲስ ተስፋ ነበር፣ ካትሪን ሳምባ ፓንዛ ያማፅያኑን መሪ ሚሼል ጆቶጂያን በመተካት የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት የሆኑት ጥር 20 ቀን 2014 ዓም ነበር። ባለፈው ጥቅምት ወር ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት፣ ሀገሪቱን ለማረጋጋት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በድል ለመወጣት ከመስራት ወደኋላ አይሉም።

« ሥልጣን ላይ የመጣሁት ልክ እንደ እሳት አደጋ ሀገሪቱን ለማረጋጋት ነው። የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዜጎች በኔ ላይ ብዙ ትስፋ አሳድረዋል እና ቅር ላሰኛቸው አይገባም። በሀገሪቱ ሰላም፣ ፀጥታ እና በተለይ ልማት ለማረጋገጥ የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ። ምክንያቱም ቀውሱ በመጀመሪያ ደረጃ የልማት መጓደል እና የድህነት የፈጠሩት ቀውስ ነውና። »

ይሁንና፣ ተፋላሚዎቹ ወገኖች ውዝግባቸውን እንዲያበቁ ፕሬዚደንቷ ያሰሙት ጥሪም ሆነ ያደረጉት ጥረት ሰሚ ጆሮ እስካሁን አላገኘም። በየማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የተሰማሩት ከ9,000 የሚበልጡ የአውሮጳ ህብረት፣ የአፍሪቃ ህብረት እና የተመድ ወታደሮች እስካሁን የሴሌካ ዓማፅያን እና የክርስትያኖቹ ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎችን የኃይል ተግባር መቆጠጠር አልተሳካላቸውም።

መስከረም 28፣ 2014 በጀርመን በተደረገው 41ኛው የበርሊን የማራቶን ውድድር ከተጀመረ ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ነበር ኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ ጥሩ አካሄድ መያዙን የተረዳው። ያልተጠበቀ ጥሩ ውጤት ሊያስመዘግብ እንደሚችልም ገመተ። እስዳሰበውም፣ 42 ኪሎ ሜትሩን በ2:02:57 ሰዓት ጨርሶ የአዲስ ክብረ ወሰን ባለቤት ሆነ።

« ጥሩ ስሜት ተሰምቶኛል፣ ምክንያቱም፣ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግቤአለሁና። በጣም ተደስቻለሁ። »

ኪሜቶ በሀገሩ ዜጋ ዊልሰን ኪፕሳንግ ተጠብቆ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን በ26 ሰከንድ ያሻሻለው የ30 ዓመቱ ዴኒስ ኪሜቶ ለረጅም ርቀት ሩጫ ውድድር አዲስ ቢሆንም፣ በዚሁ የበርሊኑ ጅምር ድርብርብ ሽልማት ነበር ያገኘው።

ሞዛምቢክ ሰሞኑን በሚገባደደው አውሮጳዊ ዓመት በርስ በርሱ ጦርነት አፋፍ ላይ ተግኘ ነበር። ትልቁ የተቃዋሚ ፓርቲ፣ ሬናሞ መንግሥት በአባለቱ አንፃር ፈፅሞታል ያለውን ጥቃት በመቃወም የብረቱን ትግል ለመጀመር ጥሪ አስተላልፎ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ፣ ሸምጋዮች ተቀናቃኞቹን ገዚው የፍሬሊሞን ፓርቲ እና ሬናሞን ለማቀራረብ ካካሄዱት ቀላል ያልነበር ድርድር በኋላ ሁለቱ ወገኖች የደረሱት አዲሱ የሰላም ውል በሀገሪቱ ባለፈው ጥቅምት ወር በሀገሪቱ 5ኛው ዴሞክራሲያዊው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተደረገበትን ሁኔታ አመቻቸ። ብዙው መራጭ ሕዝብ ድምፁን እ ጎ አ ከ 1975 ዓ ም አንስቶ እስካሁን በአመራር ላይ ለሚገኘው የገዢው የፍሬሊሞ ፓርቲ ዕጩ ፊሊፔ ንዩዚ ሰጠ። ንዩዚ ውጤቱ በይፋ ከወጣ በኋላ ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት ድላቸው የብዙ ዓመት ስራቸው ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

« በሆነ ጊዜ አንድ ሰው ድል እቀዳጃለሁ የሚል እምነት እንደነበረኝ ጠይቆኝ ነበር፣ ያኔ እንደማሸንፍ እርግጠኛ እንደሆኑኩ ነበር የገለጽኩለት። እኔ እና ፓርቲያችን ያከናወነውን ስራ ሕዝቡ በሚገባ ተከታትሎታል። በጋራ ያከናወነው ነው። ትክክለኛው ዝግጅት የተደረገበት እና ለብዙ ዓመታት የዘለቀ ጥረት ነው። ውጤቱም አሁን አንተን እና የሞዛምቢክን ሕዝብ በማነጋገር ላይ ያለው ዕጩ - ማለትም - የእኔን ድል የሚያስገኝ ይሆናል። »

በማሊ እአአ መስከረም 2013 ዓም የተደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ቀደም ሲል በተካሄደው የርስበርስ ጦርነት የተፈጠረው ውዝግብ ያበቃል የሚል ተስፋ ነበር። ይሁንና፣ በማሊ መንግሥት እና በሰሜናዊ የሀገሩ አካባቢ በሚንቀሳቀሱት ተቀናቃኞቹ የቱዋሬግ ዓማፅያን መካከል የተፈጠረው ውጥረት በመረገብ ፈንታ እንደተጠናከረ ነበር የቀጠለው። ዓማፅያኑ ባለፈው ግንቦት የኪዳልን ከተማ እንደገና ተቆጣጠሩ። ከዚህ በተጨማሪ፣ በሰሜን ማሊ ሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር የሚኖረው የአዛዋድ መንግሥት ለማቋቋም የተነሱበትንም ዓላማ እንደሚቀጥሉ በድጋሚ አረጋገጡ። የማሊ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አብዱላይ ዲዮፕ ግን ይህንኑ ያማፅያኑን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል።

« በሰሜን ማሊ አንድ ፌዴራዊ መንግሥት የማቋቋም ዕቅድ የለንም። መታወቅ ያለበት ጉዳይ ድርድሩ እኛ ባቀረብነው ሀሳብ ዙርያ ላይ መሆን እንዳለበት ነው። የመንግሥት ተሀድሶ ፣ ማለትም፣ ያካባቢ መስተዳድሮችን በማጠናከር ለማድረግ ዝግጁ ነን። ይሁንና፣ ይህ በአንድ ብሔራዊ መንግሥት ሥር መከናወን ይኖርበታል። »

የማሊን ተቀናቃኞች ለማስታረቅ በቡርኪና ፋሶ ሸምጋይነት በዋጋዱጉ የተጀመረው ድርድር ግን ባለፈው ህዳር ወር ለሶስተኛ ጊዜ ከሽፎዋል።

ቡርኪና ፋሶን ለ27 ዓመታት የመሩት ፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት በማሻሻል ለተጨማሪ የሥልጣን ዘመን ለመቆየት ባለፈው ጥቅምት ወር ያደረጉት ሙከራቸው ለውድቀታቸው ምክንያት ሆኖዋል። ካምፓዎሬ ሥልጣን መራዘምን ያልደገፈው የሀገሪቱ ሕዝብ ርምጃውን በጥብቅ በመቃወም አደባባይ መውጣቱን በዚያን ወቅት ትክክለኛ ያሉት ድሪሳ ሱማንዴ የመንግሥት ኃላፊነት ምን ላይ መሆኑን አጠያይቀዋል።

« እኒሁ ፕሬዚደንት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ነው የሚያስቀድሙት። ለኛ ለሕዝቡ የሚሰሩት ነገር የለም። ብዙ ችግሮች አሉብን። ሀገራችን እጅግ ድሀ ናት። እና መንግሥታችን ካምፓዎሬን የዕድሜ ልክ ፕሬዚደንት ለማድረግ ከመጣር የተሻለ ሌላ ስራ የለውም እንዴ? »

ተቃዋሚዎች በዋጋዱጉ የሚገኘውን የሀገሪቱን ምክር ቤት በእሳት ካጋዩበት የተጠናከረ ተቃውሞ በኋላ ካምፓዎሬ ወደ ጎረቤት ኮት ዲቯር መሸሽ ተገደዱ። ከዚያ የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት ለመሸፈን የጦር ኃይሉ የሽግግሩን መንግሥት አመራሩን ያዘ። ይህን ተከትሎ በጦር ኃይሉ እና በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም፣ በሲቭሉ ማህበረሰብ መካከል በተካሄደ ድርድር በተደረሰ ስምምነት መሠረት፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲደረግ ተወስኖዋል።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ዜጋ የሆኑት የማሕፀን ሀኪም ዴኒስ ሙክዌጌ የአዉሮጳ ህብረት በያመቱ የሚሰጠዉ እና 50 ሺሕ ዩሮ የያዘው የዘንድሮዉ የሳኻሮቭ ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። በትዉልድ ሀገራቸዉ ለተደፈሩ ሴቶች ርዳታ በመስጠታቸው እና በሴቶች ላይ በሚደርሰው ወሲባዊ ጥቃት አንፃር በመታገላቸዉ ነዉ ሙክዌጌ ለሽልማት የበቁት። ሙክዌጌ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ስለሚፈፀመው የኃይል ተግባር ለአውሮጳ ህብረት ያቀረቡበት ገለጻቸው አውሮጳውያኑን እንደራሴዎች እጅግ ነበር ያስደነገጠው። በምሥራቃዊ ኮንጎ በምትገኘው የቡካቩ ከተማ ባለው የፓንዚ ሀኪም ቤት ስለሚያካሂዱት ዕለታዊ ስራቸው ሲገልጹ፣

« በአሳፋሪ የኤኮኖሚ ምክንያቶች እነዚህን የመሰሉ በስብዕና አንፃር የሚፈፀሙ ወንጀሎች እየታቀዱ መሆናቸውን እያወቅሁ እንዴት ዝም ልል እችላለሁ? እነዚሁ ኤኮኖሚያዊ ምክንያቶች ክብረ ንፅሕና መድፈርን እንደ ጦር ስልት ሲውል እያየሁ እንዴት ዝም እላለሁ? እያንዳንዷ ክብረ ንፅሕናዋን የምትደፈር ሴትን ስመለከት፣ ባልተቤት ትታየኛለች፣ እያንዳንዷ ክብረ ንፅሕናዋን የምትደፈር እናትን ስመለከት፣ እናቴ ትታየኛለች። እያንዳንዱ ክብረ ንፅሕናውን የሚደፈር ሕፃንን ስመለከት፣ ልጆቼ ይታዩኛል። እና እንዴት ዝም ልል እችላለሁ? »

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከፍተኛ የልዕካን ቡድን አስከትለው በጀርመን ጉብኝት አካሄዱ። የልዑካኑ ቡድን በርሊን ዉስጥ ከመራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና ከተለያዩ የጀርመን መንግሥት ባለሥልጣናት ባለወረቶች ጋር ሀሳብ ተለዋውጦዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የጀርመን ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዲያሰሩ ጠይቀዋል።

በዚሁ አጋጣሚም አንጌላ ሜርክል ጀርመን አፍሪቃ ዉስጥ ባሁኑ ወቅት ያለዉ አጋጣሚ ሊያመልጣት እንደማይገባ አስረድተዋል። በዚሁ ጉብኝት ወቅት በጀርመን ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የመብት ተሟጋቾች የጀርመን መንግሥት የሰብዓዊ መብት ይረግጣል በሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርግ በመጠየቅ ያደባባይ ሰልፍ አድርገዋል።

ዘ ሄግ ፣ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ተመልካች ፍርድ ቤት በኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ላይ የመሰረተውን ክስ ሰረዘ። እአአ ከ2007 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት ይፋ መሆን በኋላ በኬንያ የተፈጠረውን ከአንድ ሺህ የሚበልጥ ሰው ሕይወት ያጠፋውን እና እጅግ ብዙዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ያፈናቀለውን ግጭት በማቀነባበር በስብዕና አንፃር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ዓቃቤ ሕግ መስርቶባቸው የነበረውን ክስ ከሁለት ዓመት በኋላ መሰረዙን ዋና ዓቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ ከጥቂት ቀናት በፊት አስታውቀዋል። የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሚና መሀመድ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በደስታ ተቀብለውታል።

« በዘ ሄግ የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ በተከበሩት የኬንያ ፕሬዚደንት ላይ መስርቶት የነበረውን ክስ በዛሬው ዕለት ሰርዞዋል። »

ዋና ዓቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ በውሳኔው ቅር መሰኘታቸውን ገልጸዋል።

« ይህ ወቅት በአስከፊው የድህረ ምርጫ ግጭት ለተሰቃዩት እና ፍትሕ ለማግኘት ያለፉት ሰባት ዓመታትን በትዕግሥት ሲጠብቁ ለቆዩት ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት በጣም የሚያሳምም ወቅት ነው። »

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት«አይ ሲ ሲ » በዳርፉር ግዛት የጦር ወንጀል ተፈፅሞዋል በሚል ጀምሮት የነበረውን ምርመራ ለጊዜው አቆመ። ፍርድ ቤቱ በዚሁ ምርመራው ላይ ከተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በቂ ድጋፍ አለማግኘቱን ዋና ዓቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ እንደ ምክንያት ገልጸዋል። በዚሁ ዓመፅ ተጠያቂ በሚል በእስር ከሚፈልጋቸው ስድስት የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት እና ዓማፅያን መካከል አንዱ በሆኑት የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን አል በሺር ላይ በጦር ወንጀል እና በስብዕና አንፃር ፈፀሙት ባለው ወንጀል ሰበብ የመሰረተባቸውን ክስ አቋርጦዋል። በተመድ ግምት መሰረት፣ በዳርፉር ውዝግብ እአአ ከ2003 ዓም ከፈነዳ ወዲህ b።ብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ሰው ሲሞት፣ ወደ ሁለት ሚልዮን የሚጠጋ ተፈናቅሎዋል።

የሶማልያ አክራሪ የአሸባብ ቡድን የሚያካሂዳቸው የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች አዘውትረው በሶማልያ ጦር ያሰማራችዋን ጎረቤት ኬንያን ሰላባ አድርገዋል። እአአ ባለፈው ህዳር 22፣ የቡድኑ አባላት በጣሉትም ጥቃት በርካታ ኬንያውያንን ገድለዋል። ስለጥቃቱ የኬንያ ፖሊስ ቃል አቀባይ ዴቪድ ኪማዮ፣

« ዛሬ ንጋት ላይ አንድ ከማንዴራ ወደ ናይሮቢ ይጓዝ የነበረ አውቶቡስ በአራቢያ አካባቢ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶበታል፣ ጥቃቱ የ 28 ሰዎች ሞትን አስከትሎዋል። »

ጥቃቱ ፖሊስ በሞምባሳ ወደብ ከተማ በሚገኙ መስጊዶች ባካሄደው አሰሳ እና የኃይል ተግባር አፀፋ መሆኑን አስታውቀዋል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic