የ2ቱ ሱዳን መንግሥታት ግጭትና የነዳጅ ዘይቱ ይዞታ | አፍሪቃ | DW | 26.04.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የ2ቱ ሱዳን መንግሥታት ግጭትና የነዳጅ ዘይቱ ይዞታ

ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ፤ ድንበር አካባቢ ግጭት ካደረጉና አሁንም የካርቱም መንግሥት የጦር አኤሮፕላኖች፣ ሂጅሊጅ ነዳጅ ዘይት ማውጫ አካባቢ ድብደባቸውን እንደቀጠሉ፣ በመሃሉ ወደ ህዝባዊት ቻይና ጎራ ብለው የነበሩት

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልባ ኪር፣ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ከሁለቱም መንግሥታት ጋር ፣ በነዳጅ ዘይትና በንግድ ጽኑ ትሥሥር እንዳላት  የሚነገርላት  ቻይና፤ ፕሬዚዳንቷ  ሁ ጂንታዎ ለደቡብ ሱዳኑ አቻቸው ትናንት እንደገለጡት፣ ሁለቱም የሱዳን መንግሥታት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት መመለስ ይኖርባቸዋል።  
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው፣ የካርቱም መንግሥት ጦር አኤሮፕላኖች፣  ያለማቋረጥ  በደቡብ ሱዳን ላይ  በመፈጸም ላይ ባሉት  ድብደባ ፣ በትናንቱ ዕለት፤ 16 ሰዎች ናቸው የተገደሉት። ደቡብ ሱዳን ነጻነት ካወጀች ወዲህ አሁን የገጠማት ውዝግብና ውጊያ፤ በአፍሪቃ ኅብረት ሸምጋይነት  እንዲቆምና ድርድር እንዲካሄድ ማድረግ ካልተቻለ፣ ሁለቱም ወገኞች፤ በተለይ በነዳጅ ዘይት ሀብት ሽያጭ ረገድ ብርቱ ኪሣራ ነው የሚደርስባቸው።  የነዳጅ ዘይቱ ሽያጭ መቋረጥ ፣ የህዝቡን ዕለታዊ ኑሮ እስከምን ድረስ ጎንጦት ይሆን? የዶቸ ቨለ የእንግሊዝኛው ክፍል ባልደረባ፣ ማርክ ኮልድዌል፤ ያነጋገራቸው  በሱዳን የአውሮፓውያን የነዳጅ ጉዳይ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ  ወ/ሮ ካትሊነ ሸንክል፣ ----
«ዜጎቹ ፣ በአሁኑ ጊዜ፣ የነዳጅ ዘይት ማውጫ ቦታዎች ከተዘጉ ከ 3 ወራት ወዲህ ፣ ችግሩ ያን ያህል አልተሰማቸውም። ጊዜው አጭር በመሆኑ! ከመዘጋቱ በፊት ፤ ቀደም ባለው ጊዜም ቢሆን፣ ዘርፈ ብዙ በነበረው የሁለቱ ወገኖች ስምምነት፣ ሰሜንና ደቡብ ሱዳን፣ ነዳጁን ግማሽ-በግማሽ እንደሚካፈሉት በተነጋገሩበት ዘመንም ቢሆን፣ ከነዳጅ የሚገኘው ገቢ፣ህዝቡ ኪስጋ ደርሶ አያውቅም ነበር። ስለዚህ ገቢው ቢያሽቆለቁልም፤  ህዝቡ  ጉዳቱ አሁን በቀጥታ አልታየውም። ይህ ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ ከቀጠለ ግን፣ ሳይጎንጠው አይቀርም።»
ዜጎቹን ፣ ችግሩ ፣ በምን፣ በምን ዓይነቱ ዘርፍ ይሆን የሚሰማቸው?
«አንዱ ችግር፤ የዩኒቨርስቲዎች ነው። ለፕሮፌሰሮች ደመወዝ መክፈል አይችሉም። ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ አስፈላጊው የገንዘብ አቅም ይጓደልባቸዋል። የጤና ጥበቃው ሥርዓትም ቢሆን፣ ደካማ ነው። ህዝቡ ደግሞ በመንግሥት በኩል ልማት እንዲንቀሳቀስ ይጠብቃል። እርግጥ ነው በአሁኑ ቅጽበት፤ ከሞላ ጎደል፣ ሁሉም የጦርነት ሁኔታ መኖሩን ያውቃል። እናም፣ እምብዛም የሚጠብቁት ነገር የለም። ይህ ሁኔታ ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ ከሆነ ግን፣ በአገሪቱ፤ የላቀ ችግር መከሠቱ አይቀሬ ነው።»
የደቡብ ሱዳን ህዝብ፣ የነዳጅ ዘይቱ ትሩፋት እንደሚደርሰውና ፍትኀዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንደሚሆንም  ያምናል። ይሁንና አሁን፤ አገሪቱ የምትገኝበትን ሁኔታ ስለሚያውቅ፣ እስከዚህም በመንግሥት ላይ የሚያማርርበት ሁኔታ የለም።  ለዘለቄታው ደግሞ፣ የነዳጅ ዘይቱ  ሀብት አገራቸውን እንዲገነባ ይፈልጋሉ።
ባለፈው ሳምንት፤ ፕሬዚዳንት ኧል በሺር፣ ሱዳን ለነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ ቧንቧ ክፍያ አትሻም፤ ቧንቧውንም ክፍት አታደርግም ማለታቸው ታውቋል። ሁኔታው በእንዲህ ከቀጠለ፣ ለደቡብ ሱዳን ፤  የጨፈገገ ሁኔታ አያስከትልም ወይ? ለሰሜን ሱዳንስ? አሁንም ካትሊነ ሸንክል---


«አሁን ነዳጅ አለመውጣቱ፣ ለደቡብ ሱዳን የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪ ራሱን የቻለ ችግር አስከትሏል። በሺር ቧንቧውን ለመክፈት አልፈልግም ማለታቸው ከአንገት በላይ የሆነ የአነጋገር ፈሊጥ ነው። አስቀድማ በቧንቧው አልጠቀምም ያለች ደቡብ ሱዳን ናት።  ደቡብ ሱዳን ለአንዲህ ዓይነት ችግር ራሷን ሳታዘጋጅ አልቀረችም። ደቡብ ሱዳናውያን፣ ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት ያለነዳጅ፣  መስዋዕትነትን መክፈል ለሚችሉበት ሁኔታ ሳይዘጋጁ አልቀሩም።
ለሰሜን ሱዳን፤ ማንናውም ከደቡብ ሱዳን በኩል ገቢ የሚያስገኝ ሁኔታ፣ተቀባይነቱ እጅግ ከፍ ያለ ነው። እንደሚመስለኝ፣ በሺር ከደቡብ ሱዳን ምንም ዓይነት ነገር እንደማይሹ የሚናገሩት፣ ኀፍረትን ለመሸፈን ነው። ከመጀመሪያውም ፣ ቧንቧውን አልጠቀምበትም  ብላ የዘጋች ደቡብ ሱዳን ናትና። ስለዚህ ሰሜኑ ለገበያ የሚያቀርበው አይኖረውም፤ ደቡብ ሱዳንን መቋጣጠር የሚያስችል አቅምም ሆነ ሥልጣንም የለውም። ቧንቧው፣  በደቡብ ሱዳን ላይ ተጽእኖ ማሳደሪያ  መሣሪያ ሆኖ ነበረ የሚታየው። አሁን ግን፣  በሺር ፣ ያን ማድረግ አይችሉም፤ ከሽፎባቸዋል። ችግሩ ፤ በሰሜን ሱዳን ላይ አፍጥጧል። የዐላቂ ዕቃዎች ዋጋ አለቅጥ ንሯል። በዚህም ሳቢያ ውስጣዊ ችግር አለ።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 26.04.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14l8L
 • ቀን 26.04.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14l8L