የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች እና ዕረፍታቸው | ባህል | DW | 03.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች እና ዕረፍታቸው

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 2 ባሉት ቀናት ውስጥ ተሰጥቷል። ከሌላው ክፍል ተማሪዎች ጋር ሲነፃፀር አንድ ወር ግድም ቀድሞው ዕረፍት ላይ የሚገኙት የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወሳጆች በአሁኑ የዕረፍት ጊዜያቸዉ ምን እያደረጉ ይገኛሉ?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:21

የዕረፍት ጊዜ

የ12ኛ ክፍል የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ፤ ስሙ እንደሚጠቁመው ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችል መሸጋገሪያ ድልድይ ነው። ስለሆነም በርካታ ይህንን ድልድይ መሻገር የሚፈልጉ ወጣት ኢትዮጵያውያን በፈተና ወቅት ተግተው ያጠናሉ። ልክ የዚህ የውጥረት ሰሞን ሲያልፍስ ጊዜያቸውን በምን ያሳልፋሉ?የዘንድሮ የ 12ኛክፍል ተፈታኝ ሊንዳ አለማየሁ፤ የ19 ዓመት ወጣት ናት። ለወጣቷ አጠቃላይ የፈተና ጊዜው እና ከዛም በኋላ የነበረው ሁኔታ በአባቷ ህመም እና ኋላም ሞት ምክንያት አስደሳች አልነበረም። አሁንም ሀዘን ላይ የምትገኘው ሊንዳ፤ ትንሽ እንደተረጋጋች ግን በበጎ ፍቃደኝነት ለማስተማር ወስናለች።

ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በግሏ የወሰደችው ወጣት ምህረት ተሾመ ደግሞ ብዙም የዕረፍት ጊዜ የላትም። በአሁኑ ሰዓት በኮሌጅ ደረጃ - ነርስ ለመሆን በመማር ላይ ትገኛለች። ጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆነው ጌትነት መኮንን ደግሞ ጊዜውን የሚያሳልፈው መጽሐፍ በማንበብ እና ፊልሞች በመመልከት ነው። እሱም ሆኑ ጓደኞቹ ከዚህ የተለየ ጊዜ ማሳለፊያ የላቸውም፤

ሌላዋ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወሳጅ ሕብስት መንገሻ ትባላለች። ከከፋ ዞን ቀሎ ፤ ሕብስት ወደፊት በጤናው ዘርፍ፤ ካልሆነ ደግሞ እንደ ጌትነት የኢንጂነሪንግ/ምህንድስና ተማሪ መሆንን ትመርጣለች።

ወጣት አበቅ የለሽ ሙሉጌታም እንዲሁ እንደሌሎቹ ወጣቶች በአሁኑ ሰዓት በዕረፍት ላይ ትገኛለች። ሆኖም የጎንደር ከተማ ነዋሪዋ በዕረፍት ጊዜዬ ብዙም የምሰራው ነገር የለም ትላለች።ያለ ምንም ስራ እቤት የተቀመጠችው አበቅ የለሽ በአሁኑ ሰዓት ስራ ማጣቷ ብቻ ሳይሆን የውጤቷ ጉዳይም ያሳስባታል።

ሌላው ወጣት የአዲስ አበባ ነዋሪ ናሆም አማረ ነው። የ18 ዓመቱ ወጣት ያለፉትን ሶስት ሳምንታት ዘና እያለ እያሳለፈ መሆኑን ገልፆልናል።ይሁንና ናሆም ወጣቶች ሙሉ የዕረፍት ጊዜያቸውን በመዝናናት ማሳለፍ የለባቸውም ይላል።

ናሆም የ12ኛ ክፍሉ ፈተና እንደጠበቀው አልከበደውም። ፈተናውንም እንደሚያልፍ ባለ ሙሉ ተስፋ ነው። ከዚህም ሌላ ወጣቱ ወደፊት መማር የሚፈልገውን ጠንቅቶ ያውቃል። በመጀመሪያ ምህንድስናለሁለተኛ ዲግሪው ደግሞ አርክቴክቸር( የስነ ህንፃ)ትምህርት ማጥናት ይፈልጋል።

የ12ኛ ክፍል የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን ወስደው ለጊዜው ከፈተና ነፃ የሆኑት ወጣቶች በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት የገለፁልንን በድምፅ ማዳመጥ ይቻላል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic