የ107 ፓርቲዎች ወግ! | ኢትዮጵያ | DW | 22.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የ107 ፓርቲዎች ወግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ 107 የፖለቲካ ድርጅቶች የሚመሩበትን «በፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እንዲሁም በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ሥርዓት ቃል ኪዳን» ፈርመዋል። ከቃል ኪዳኑ ይልቅ ዜና ሁኖ የሰነበተው እና ብዙ መቀለጃ የነበረው ግን «ኢትዮጵያ 107 የፖለቲካ ድርጅቶች አሏት» የሚለው ጉዳይ ነበር።

180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

በፍቃዱ ኃይሉ

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 80 ሲባሉ የነበሩት ፓርቲዎች ባንድ ጊዜ ዘለው 107 መድረሳቸውም በራሱ አንድ ዜና ነው። ይሁንና እውን ኢትዮጵያ እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች አሏት? ቢኖሯትስ ምንድ ነው ችግሩ? ቃል ኪዳኑን የመፈረማቸው ፋይዳስ ምንድን ነው?

ለአቅመ ፓርቲ ያልደረሱ ፓርቲዎች

አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ ዕውቅና ኖሮት እንዲቀጥል፥ የተለያዩ መሥፈርቶችን አሟልቶ መዝለቅ አለበት። ይህ በየትም አገር ያለ አሠራር ነው። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም ዐሠራ አንድ መሥፈርቶችን አስቀምጦ ያሟሉት እና ያላሟሉትን የለየበት የጥናት ሰነድ አለው። በእነዚህ መሥፈርቶች በቅርቡ ቦርዱ ባደረገው ጥናት ላይ እንደተመለከተው፥ በአሁኑ ወቅት «ንቁ» ሊባሉ የሚችሉትና የተመዘገቡት ፓርቲዎች ጠቅላላ ብዛት 62 ነው። ከእነዚህ ውስጥ 22ቱ አገር አቀፍ እና 40ዎቹ ደግሞ ክልላዊ ናቸው።

ከ22ቱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች መካከል የሚጠበቅባቸውን መሥፈርት ሁሉ ያሟሉት ሰባቱ ብቻ ሲሆኑ፥ ከክልላዊዎቹ ውስጥ ደግሞ ዘጠኙ ብቻ ናቸው። በዚህ መሠረት፥ በተሟላ ሁኔታ የሚገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች 16ቱ ብቻ ናቸው። የሚገርመው ደግሞ የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶች ተብለው ክልሎችን ከሚያስተዳድሩ ፓርቲዎች ውስጥም ሁለትም፣ ሦስትም መሥፈርቶችን ያላሟሉ ድርጅቶች መኖራቸው ነው። ይህ ጥናት ከተደረገ በኋላ ሰማያዊ ፓርቲ በይፋ ራሱን ሲያከስም፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ደግሞ ዕውቅና ተቀብሏል።

«የሽግግር ጊዜ» ዕዳ

የሆነው ሆኖ «107 የሆኑት ከየት መጥተው ነው?» የሚል ጥያቄ መከተሉ አይቀርም። በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የፖለቲካ ለውጥ ላይ ተስፋ በማድረግ በርካታ ቡድኖች የፖለቲካ ድርጅት እየመሠረቱ ነው። ከእነዚህ ውጪም ከስደት የተመለሱ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ሁሉ በማደራጀት ሥራ ላይ ናቸው። እንደ ኦነግ እና አርበኞች ግንቦት ሰባት ያሉት ደግሞ ከነባሮቹ ካልበለጠ የማይተናነስ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ መሆናቸው የተመዘገቡ፣ ሁሉንም መሥፈርት ያሟሉትን ድርጅቶች ካልተመዘገቡትም፣ ተመዝግበው መሥፈርቶችን ከማያሟሉትም ጋር እኩል የፖርቲ ማዕረግ እንዲያገኙ አስገድዷቸዋል።

በዚህ «የሽግግር ጊዜ» የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ እና ሌሎችም የምርጫ ሕግጋት እየተከለሱ ነው። ምናልባት ሁሉም ፓርቲዎች ዳግም ምዝገባ ሊጠየቁ ይችላሉ። «ሽብርተኛ» ይባሉ የነበሩ ድርጅቶችም ፍረጃው ተነስቶላቸው አገር ውስጥ አባላት እየመለመሉ፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን እየከፈቱ ነው። በዚህ ጊዜ ሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖች በአንድ የአሠራር ቃል ኪዳን አፈራርሞ ማስማማት ለምርጫ ቦርድ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ለቡድኖቹ የሕጋዊነት ስሜት ሊሰጣቸው አይችልም።

ችግሩ ምንድን ነው?

የፓርቲዎች ቁጥር መብዛቱን ብዙ ሰዎች እንደ ችግር ተመልክተውታል። እውነተኛው ችግር ግን ብዛታቸው አይደለም። የፖለቲካ ድርጅቶች መብዛት፣ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ክፍፍሎሽ በበዛበት እና ባልዳበረ ዴሞክራሲ ውስጥ፥ የሁለት እና ሦስት ፓርቲዎች ሥርዓት የገነነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥም በርካታ ፓርቲዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ ያክል በአሜሪካ 40፣ በእንግሊዝ ከ76 በላይ እና በጀርመን 47 ያክል የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ።

ችግሩ ያለው ፓርቲዎቹ ሕጋዊ መሥፈርቶችን የማያሟሉ፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሥራ አስፈፃሚውን የሞሉባቸው፣ የፖለቲካ አፈና በበዛበት ወቅት የይስሙላ «መድብለ ፓርቲ ሥርዓት» አለን የሚለውን ለማረጋገጥ ይህ ድክመታቸው እየታወቀ በቸልታ የታለፉ፣ ሕዝብን ለመወከል የሞራልም የሕግም ብቃት የሌላቸው መሆናቸው ነው።

የፍርድ ቀን ዘመቻ

«የሽግግር ጊዜው» በይፋ ከታወጀ ዓመት ሞልቶታል። በዚህ «የሽግግር ጊዜ» የማስታረቅ ስሜት እና የማስተካከያ ዕድል እየሰጡ ከዚህ በላይ መቆየት አግባብ አይሆንም። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ (ይራዘማል እየተባለ የሚታማው አገር አቀፍ ምርጫ) የቀረው አንድ ዓመት ብቻ መሆኑ ነው። የቅድመ ምርጫውን ጊዜ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እና መሥፈርቶችን አሟልተው ያቀረቡ የፖለቲካ ድርጅቶች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን አቅርበው የሚፎካከሩበት እና ቅስቀሳ የሚያደርጉበት ጊዜ እንጂ በ«ሽግግር ጊዜ» ሥም «እሹሩሩ» የሚባሉበት መሆን አይኖርበትም።

ስለሆነም፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአስቸኳይ ለእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች የመጨረሻ የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ የትኞቹ ሕጋዊ ቅቡልነት ያላቸው እና የትኞቹ የሌላቸው መሆናቸውን ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግበት የፍርድ ቀን ዘመቻ ማኖር አለበት። ከዚያ የጊዜ ገደብ በኋላ ቦርዱ መደበኛ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቱን በይፋ በማወጅ እንደ የፖለቲካ ድርጅት «ዕውቅና» መስጠት የሚኖርበት ለተመዘገቡትና መሥፈርቱን ለሚያሟሉት ድርጅቶች ብቻ መሆን አለበት።

 

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።