የ «DNA» ምርመራ 6 ወር ይፈጃል ተባለ | ኢትዮጵያ | DW | 16.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የ «DNA» ምርመራ 6 ወር ይፈጃል ተባለ

በተከሰከሰዉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዉሮፕላን ዉስጥ የነበሩ የ 157 ተጓዦችን ማንነት ለመለየት የሚደረገዉ የ «DNA» ምርመራ ስድስት ወር ሊፈጅ እንደሚችል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለፀ። በነገው እለት(እሁድ) ጠዋት ለሟቾች ለሁሉም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ፀሎተ ፍትሀት ይደረጋል፡፡

ባለፈዉ እሁድ ቢሾፍቱ/ ደብረዘይት አካባቢ በተከሰከሰዉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዉሮፕላን ዉስጥ የነበሩ የ 157 ተጓዦችን ማንነት ለመለየት የሚደረገዉ የ «DNA» ምርመራ ስድስት ወር ሊፈጅ እንደሚችል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለፀ። ፖሪስ የሚገኘው የአዉሮፕላኑ የመረጃ ሳጥን መርማሪ ቡድን የቦይንግ 737 ማክስ 8 አዉሮፕላን የመረጃ ሳጥን የያዘዉን የድምፅ ቅጂ ዛሬ መመርመር መጀመሩን ተናግሯል። «BEA» የተሰኘዉ የፈረንሳይ የአደጋና ዝግጁነት ተቋም በትዊተር ባሰራጨዉ መረጃ መርማሪዎቹ የረዳት አብራሪዉን የድምጽ ቅጂ ምርመራ ዛሬ ጀምረዋል፤  ምርመራዉ የበረራዉን የመረጃ ቅጂን ሁሉ ያካትታል። 
የተከሰከሰዉ የአዉሮፕላን የመረጃ ማጠራቀምያ ሳጥን ከትናንት በስትያ ለምርመራ ፓሪስ ፈረንሳይ መግባቱ ይታወቃል። ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፍያ ወደ ናይሮቢ ለመጓዝ መብረር በጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ በወደቀዉ አውሮፕላን ዉስጥ ከ 35 በላይ የዓለም ሃገራት የመጡ ተጓዦች እንደነበሩበት ይታወቃል። የምርመራዉን ዉጤት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት የአዉሮፕላኑ ተሳፋሪ ቤተሰቦች ነገ እሁድ በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስትያን በተዘጋጀዉ ፀሎተ ፍትሀት ሥነ-ስርዓት ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል።

Äthiopien Flugzeugabsturz Ethiopian Airlines Flight ET 302 | Black Box

የቦይንግ 737 ማክስ 8 አዉሮፕላን ብላክ ቦክስ

አንድ የአዉሮፕላኑ አደጋ ሰለባ የሆኑ ቤተሰብ አባል ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በቅድስት ስላሴ በተዘጋጀዉ ሥነ-ስርዓት ላይ የአደጋዉ ሰለባ ቤተሰቦች ከድርጅቱ አንድ አንድ ኪሎ አፈር ተሰጥቶን በተዘጋጀዉ ቦታ የቅብር ሥነ-ስርዓት እንፈፅማለን ማለታቸዉ ተዘግቦአል። ይህን የተናገሩት ግለሰብ ስማቸዉ እንዳይገለጽ መናገራቸዉን ሮይተርስ ዛሬ ይፋ ያደረገዉ ዜና ያመለክታል።          
ዛሬ  ቅዳሜ በ«ስካይ ላይት ሆቴል» በተዘጋጀዉ ሥነ-ስርዓት ላይ ለአደጋዉ ሰለባ ቤተሰቦች « ከዚህ ዓለም በሞት መለየትን የሚገልፅ ሰርተፊኬት በሁለት ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ተዘጋጅቶ እንደሚሰጥ እንዲሁም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ሁሉ አስቸኳይ ክፍያ እንደሚደረግ የሚገልጽ ወረቀት መሰጠቱን» ሮይተርስ ዘግቦአል። በአደጋዉ አካባቢ የተገኙ ቁሳቁሶች በአብዛኛዉ እጅግ የተጎዱና ምንነታቸዉ  በማይታወቅ ደረጃ ላይ ቢገኝም ለባለቤቶቻዉ ቤተሰቦች ለመመለስ ስድስት ወራት እንደሚያስፈልግም ተመልክቶአል።  ይሁንና በአደጋዉ አካባቢ የተዘገነ አፈር ለቤተሰብ እንደሚሰጥ ተያይዞም ተዘግቦአል።   
 የአዉሮፕላኑ አደጋ መንስኤን ለማወቅ ጊዜዉ አሁን ገና መሆኑን ባለሞያዎች ቢስማሙበትም በዓለም ዙርያ የሚገኙ ሃገራት መንግሥታት 737 ማክስ 8 የተባለዉ አዉሮፕላን እንዳይበር እገዳ መጣላቸዉ ይታወቃል።  ባለፈዉ ጥቅምት ወር 189 ሰዎችን አሳፍሮ ሲበር ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የተከሰከሰዉ የኢንዶኔዥያ አዉሮፕላን ጉዳይ በኢትዮጵያ ቢሾፍቱ ደብረዘይት አካባቢ ከተከሰከሰዉ አዉሮፕላን ስሪት ጋር አንድ እይነትና የአወዳደቁ ሁኔታ ተመሳሳይ መሆኑ መነገሩ ይታወቃል።  
 

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ