የ 144 ሰዎች ክስ ይቋረጥ ተባለ | ኢትዮጵያ | DW | 11.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የ 144 ሰዎች ክስ ይቋረጥ ተባለ

የኢትዮጵያ ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ  በተለያዩ የሽብር ወንጀሎች ተጠርጥረዉ ክሳቸዉ በሂደት ያሉ 114 ተከሳሾች ክሳቸዉ እንዲቋረጥ ፍርድ ቤትን ጠየቀ።  በዛሬዉ ዕለት ክሳቸዉ እንዲቋረጥ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስማቸዉ ከተላለፉት   ተከሳሾች ዉስጥ  ሁለቱ የዋልድባ መነኮሳት እንደሚገኙበት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገልጿል።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:38

«መንግስት የጀመረዉን እንዲቀጥል ነዉ የምማፀነዉ»ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ


 ዛሬ ለመደበኛ ቀጠሮ ወደ ፍርድ ቤት ካመሩ ተከሳሾች መካከል  9 ያህሉ  ክሳቸዉ መቋረጡን  ከፍርድ ቤቱ መስማታቸዉን  የተከሳሾቹ  ጠበቆች ገልጸዋል።
መንግስት ለብሄራዊ መግባባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ካለፈዉ ጥር ወር ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ታሳሪዎችን ከዕስር ሲለቅ ቆይቷል። በዛሬዉ ዕለትም ተጨማሪ 114 ሰዎች ክሳቸዉ ተቋርጦ እንዲፈቱ  የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ  ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለልደታ ምድብ ችሎት ጥያቄ ማቅረቡን የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ማዕረጉ አሰፋ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
«ያዉ ለፍርድ ቤት ነዉ የሚቀርበዉ ጥያቄዉ።ፍርድ ቤት የተላለፈ መሆኑ ነዉ የተነገረዉ።።የፍርድ ቤቱ ድርሻ ነዉ ።መለቀቅ አለመለቀቃቸዉን ማረጋገጥ አልቻልንም ።በፍርድ ቤት በኩል ስለሆነ የሚለቀቁት ።ዉሳኔዉን «ኦልሬዲ»አቃቬ ህግ ክሱን ካነሳ ዞሮዞሮ ፍርድ ቤቱ የሚለቅበት ሁኔታ ስለሚኖር ዉሳኔዉ «ኦልሬዲ» ተላልፏል።»
በዚህ የዓቃቤ ህግ ጥያቄ መሰረትም  በከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ነኛ ወንጀል ችሎት  ዛሬ ረፋድ ላይ  ሶስት የብይን ቀጠሮ የነበራቸዉ ፣ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ ፤በሶስት መዝገብ ከተከሰሱት ደንበኞቻቸዉ መካካል የ5ቱ ክስ መቋረጡን  በዚሁ ችሎት ፍርድ ቤቱ እንደገለፀላቸዉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«ችሎቱ አሁን ዛሬ ሚያዚያ 3 ቀን 2010 ዓ/ም ጠዋት አራት ሰዓት ላይ ተሰይሞ ከነዚህ ሰዎች መካከል 5ቱ ሰዎች ክሳቸዉ ተቋርጧል ተብሎ በ19ነኛዉ ወንጀል ችሎት ተነገረን።ስም ተጠራና የነዚህ ሰዎች ክስ እንደተቋረጠ የፌደራል ዓቃቬ ህግ ደብዳቤ እንደ ፃፈ አነበቡልን።»ሲሉ ነዉ የገለፁት።
ሌላዉ በዛሬዉ ዕለት በከፍተኛዉ ፍርድቤት ልደታ ምድብ ችሎት  ቀጠሮ የነበራቸዉ፤ ጠበቃ ደሳለኝ ቀንዓ ናቸዉ።  እሳቸዉም በዚሁ ችሎት የ4 ደንብኞቻቸዉ ክስ መቋረጡን በፍርድ ቤቱ ተነግሯቸዋል።
«ተቋርጧል ብሎ ፍርድ ቤቱ በችሎት ነዉ የተነገረን።ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የተነገረን እንደዚያ ነዉ።ለዛሬ ያደረዉ የአቃቤ ህግ ምስክር ሂደቱ ተቋርጦ ብይን ለመስጠት ነበር ይከላከሉ አይከላከሉ ለማለት እና በዛሬዉ ደግሞ ብይኑ አልደረሰንም ከነዚህ ዉስጥ ብለዉ ስማቸዉን ዘረዘሩና እነዚህ ክሳቸዉ ተቋርጧል ።» ተብሎ እንደተነገራቸዉ ገልፀዋል። 


እንደ ጠበቃዉ ወንድሙ ገለፃ  በዛሬዉ ዕለት ክስ የተነሳላቸዉ ሰዎች  በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዉ ክስ የተመሰረተባቸዉና   ከአንድ አመት ከ6 ወር በላይ ታስረዉ የቆዩ ናቸዉ።  ክሱ የተቋረጠዉ  ከአሁን ቀደም ለብሄራዊ መግባባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ይጠቅማል በሚል  መንግስት ሌሎች ታዋቂ  ፖለቲከኞችና ጋዜኞች በለቀቀበት መንገድ መሆኑን  አቶ ወንድሙ ገልፀዉ ፤ያም ሆኖ ግን  ፍርድ ቤቱ  ተከሳሾቹን  ከክሱ ነፃ ባለማድረጉ  ዓቃቤ ህግ በማንኛዉም ጊዜ የተቋረጠዉን ክስ ሊያንቀሳቅስ እንደሚችል ነዉ የሚናገሩት።
የሽብር  ክስ ለተመሰረተባቸዉ ስድስት መቶ ተከሳሾች ጥብቅና መቆማቸዉን የሚናገሩት አቶ ወንድሙ  ከነዚህ መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት ከአሁን ቀደም ከዕስር መለቀቃቸዉን ገልፀዋል።የታሳሪዎቹ ክስ መቋረጥም ይሁን መለቀቅ ለእርሳቸዉና ለደንበኞቻቸዉ  ተስፋ ሰጭ ነዉ የሚሉት አቶ ወንድሙ ፤  ይሁን እንጅ አሁንም ድረስ በርካታ ወጣቶች በተመሳሳይ ክስ ዕስር ላይ በመሆናቸዉ   የታሰበዉን ብሄራዊ መግባባት ለማምጣት የቀሩትም  ሊፈቱ ይገባል ሲሉ ይገልፃሉ።


«ለብሄራዊ መግባባት ሆነ ለዲሞክራሲ መስፈን አስተዋፅኦ  ስለሚያደርግ እኔም ካለኝ ደስታ አንፃር ከፍተኛ እርካታ ነዉ የተሰማኝ።ግን ሙሉ እርካታ እንዲሆንልን በዚህ ጉዳይ የተከሰሱ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ከዳር እስከዳር ክሱ ተቋርጦ ብሄራዊ መግባባትና ወደ ዲሞክራሲ መድረስ ቢቻል በጣም ትልቅ ተስፋ ነዉ የማደርገዉ።አሁን ባለዉ ሁኔታ ግን ግማሽና ትልቅ ስም ያላቸዉ ታዋቂ ሰዎች ብቻ ናቸዉ የተፈቱት።በርካታወቹ ፣የማይታወቁት ፣ከግማሽ በላይ የሚጠጉት አሁንም እስር ቤት ናቸዉ።ክሱ በመቋረጡ ትልቅ እርካታ ነዉ የተሰማኝ ።እርካታዉ ግን ፍፃሜ እንዲያገኝ መንግስት የጀመረዉን እንዲቀጥል ነዉ የምማፀነዉ»

ካለፈዉ ጥር ጀምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ክሳቸዉ በሂደት የነበሩና የተፈረደባቸዉ በሺህ የሚቆጠሩ ታሳሪወችን መንግስት በምህረትና በይቅርታ ከዕስር የለቀቀ ሲሆን ሁለተኛዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ ክስ ሲቋረጥ እነዚህ 114 ሰዎች የመጀመሪያወቹ ናቸዉ። በሽብር ወንጀል ተከሰዉ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በዕስር ላይ የሚገኙት ሁለቱ የዋልድባ መነኮሳትም ክስ ከተቋረጠላቸዉ ሰዎች መካከል መሆናቸዉን ከፌደራል ጠቅላይ ዓቃቬ ህግ የተገኘዉ መረጃ ያሳያል።

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic