የ ሲ ፒ ጀይ(CPJ) ጥሪ | ኢትዮጵያ | DW | 04.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የ ሲ ፒ ጀይ(CPJ) ጥሪ

የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው በኢንግሊዘኛ ምህጻሩ CPJ በመባል የሚታወቀው ድርጅት፣የሙስሊሞች ጉዳይ መጽሔት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ከበደ እንዲፈቱና እና በጋዜጣው ባልደረቦች ላይ የሚደርስ ማስፈራርያ እንዲቆም ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫው አሳስቧል። ።

Symbolbild Pressefreiheit Sudan DW/Grafik: Peter Steinmetz

ሲፒጄ ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫው የሙስሊሞች ጉዳይ መጽሔት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ከበደ ጥር ዘጠኝ ተይዘው እስካሁን ያለ ፍርድ ታስረዋል። ድርጅቱ ኢትዮጵያ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው አቶ ሰሎሞን ሽብርተኝነትን በማነሳሳት ተጠርጥረው ከተያዙ በኋላ ለሁለት ሳምንት ክስ ሳይመሰረትባቸው ታስረዋል። አቶ ሰሎሞን በማዕከላዊ እስር ቤት እንዳሉና ጠበቃ የማማከር መብታቸውም እንዳልተከበረ ተገልጿል። መንግስት በኃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባቱን በመቃወም የጻፉት ጽሁፍ ምናልባት ለመታሰራቸው ምክንያት ሆኗል ተብሎ ይታሰባል። አቶ ሰሎሞን የኢትዮጵያ መንግስት በሙጅሊስ ምርጫ ጣልቃ መግባቱን ስለተቃወሙ ሙስሊሞች እየዘገቡ ነበር።

CPJ logo, COMMITTEE TO PROTECT JOURNALISTS, graphic element on white 2008/11/26


እንደ መግለጫው ተቃውሞው ከጀመረ ወዲህ መንግስት ሶስት የሙስሊም የህትመት ሥራዎችን አግዷል። ባለፈው ህዳር የታሰረው የሙስሊሞች ጉዳይ ዋና አዘጋጅ ዩሱፍ ጌታቸውም በአሸባሪነት ተከሶ በቃሊቲ እስር ቤት ይገኛል። በኢትዮጵያ ዩሱፍ ጌታቸውን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች ሽብርን በማነሳሳት ተከሰው ታስረዋል። በሲፒጄ የአፍሪቃ ክፍል አማካሪ ቶም ሮደስ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን ለማሰር የጸረ ሽብር ህግን ያለአግባብ ይጠቀማል ይላሉ፣

«እኚህን ጋዜጠኞች ወንጀለኛ ለማድረግ ለተጠቀሙትን ማስረጃዎችና ክሶቹን ስንመለከት፣ መረጃ በጭራሽ የለም አሊያም ደካማ ነው። መንግስት ላይ ያነጣጠረ ማንኛውንም ነቀፋ ጸጥ ለማሰኘት የጸረ ሽብር ህግን ይጠቀማሉ።»

ባለፈው ሳምንት ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ባወጣው አንድ ዘገባ፣ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት አያያዝ አሳሳቢ መሆኑ ተነግሯል። የመንግስት አሰራርን በመውቀስ የሚዘግቡ በርካታ ጋዜጠኞች ከሀገር ሸሽተዋል። እንደ ሲፒጄ ጥናትም ከሆነ ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃም ከፍተኛ የጋዜጠኞች ስደት የታየባት ሀገር ናት። የፍትህ እጦት ለጋዜጠኞቹ መሰደድ ሰበብ ሆኗል ይላሉ ቶም ሮደስ፣


«ነጻ የኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ከሆንክ ነጻና ፍትሐዊ ፍርድ አታገኝም። ያለ አግባቡ እንደሚፈረድብህ ታውቃለህ። ስለዚህ ብዙን ጊዜ ለብዙ ጋዜጠኞች ብቸኛው መንገድ ሀገር መልቀቅ ነው።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው መስከረም ሥልጣን ሲይዙ በሀገሪቷ ዲሞክራሲን ለማጎልበት ከነጻ ፕሬስ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ መናገራቸው ይታወሳል። ሆኖም ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ድርጅትና ሲፒጄ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንደሚገልጹት ጋዜጠኞችን ማሰርና የጸረ ሽብር ህግን በመጠቀም የፕሬስ ነጻነትን ማገድ አሁንም እንዳለ ነው። መንግስት ይህን የፕሬስ ነጻነት አያያዝ መቀየር አለበት ይላሉ የሲፒጄው ቶም ሮደስ፣

«ከብዙሃን መገናኛ ጋር ያለው ግንኙነት መቀየር ያለበት ይመስለኛል። መንግስትን መተቸት የመንግስት አስተዳደርን ማጥቃት ተደርጎ የግድ መወሰድ አይገባም። አዎንታዊ ትችት መንግስትን ሊረዳ ይችላል። በመጪዎቹ ወራት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መንግስት የሚቃወሙትን ሐሳቦች መጨፍለቁን ትቶ ለተሻለ እድገት የብዙሃን መገናኛዎችን ያሳትፋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»

ገመቹ በቀለ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic