የፖላንድ የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ እና ውዝግቡ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የፖላንድ የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ እና ውዝግቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤአታ ሲዚድሎ ትናንት ለህዝባቸው ባሰሙት ንግግር ፕሬዝዳንቱ ማሻሻያዎቹ እንዲጓተቱ ቢያደርጉም ፓርቲያቸው የህግ እና የፍትህ ፓርቲ በምህጻሩ PiS የፍትህ ሥርዓቱ ለውጥ እስኪደረግበት ድረስ ከእርምጃው ወደ ኋላ እንደማይል አስታውቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:08

ማሻሻያዎቹ የፍትህ ስርዓቱን ነጻነት ይገድባሉ በሚል ይተቻሉ

የፖላንድ  ምክር ቤት የፍትህ ሥርዓቱን ለመቀየር ካፀደቃቸው ሦስት ህጎች ሁለቱን የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት መሻራቸው ህጉን የሚቃወሙ ወገኖች አስደስቷል። የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ከየአቅጣጫው እየተወደሰ ቢሆንም አንደኛውን የሕግ አንቀፅ ምጽደቃቸው ግን ደስታውን ሙሉ አላደረገውም። ወግ አጥባቂው የፖላንድ መንግሥት በበኩሉ በፍትህ ስርዓቱ ማሻሻያዎች እንደሚገፋበት እየተናገረ ነው። ከሳምንት በላይ ሰላማዊ የህዝብ እና የፖለቲካ ድርጅቶች ተቃውሞዎች ተካሂደውባቸዋል፤ የውጭ መንግሥታትም ማሳሰቢያ እና ማስጠንቀቂያዎች ሰጥተውባቸዋል፤ የፖላንድ ፓርላማ የፍትህ ሥርዓቱን ለማሻሻል ይረዳሉ ብሎ ያጸደቃቸው ህጎች። የተቃውሞው መነሻ ማሻሻያ የተባሉት ህጎች ለፍትህ ሚኒስትሩ እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ሥልጣን ይሰጣሉ መባሉ ነው።

የመጀመሪያው ህግ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በሙሉ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የማድረግ እና ማን በሃላፊነቱ መቀጠል እንዳለበት የመወሰኑን ሥልጣን ለፍትህ ሚኒስትሩ የሚሰጥ ነው። ይህ ህግ አቃቤ ህግም የሆኑት የፍትህ ሚኒስትሩ  አሁን በሥራ ላይ ከሚገኙት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች መካከል በሥራቸው እንዲቀጥሉ ከሚያደርጓቸው በስተቀር ሌሎቹን በሙሉ በአስቸኳይ ከሃላፊነታቸው እንዲያነሱ ሥልጣን ይሰጣል።

ሁለተኛው ህግ ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን አጭቶ ለፕሬዝዳንቱ ከሚያቀርበው ብሔራዊው የፍትህ ምክር ቤት አባላት አብዛኛዎቹ የገዥው ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲሆኑ መብት የሚሰጥ ነው ። በእስካሁኑ አሠራር ዳኞች የሚታጩት በገለልተኛ አካል እና በፖለቲከኞች ነበር። ሦስተኛው ህግ ደግሞ የበታች ፍርድ ቤት ዳኞችን የመምረጥ እና የማባረርን ሥልጣን ለፍትህ ሚኒስትሩ ይሰጣል። የፖላንድ የፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ህግም ነው።  

የፖላንድ የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያዎች ተብለው በሀገሪቱ ምክር ቤት የጸደቁት እነዚህ ቁልፍ ህጎች በመላ ፖላንድ ለቀናት ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደውባቸዋል። ተቃውሞዎቹ ከፖላንዶቹ ከተሞች ከፖዝናን ከሉብሊን እስከ ካራካው ግድናስክ እና ርዕሰ ከተማ ዋርሳው ድረስ ተቀጣጥለው ነበር። የጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ዳኞችን በመንግሥት ተመራጮች ለመተካት የወጡትን  ህጎች ተቀባይነት የሌላቸው ያሏቸው የፖላንድ ፕሬዝዳንት አንዥሬ ዱዳ ውድቅ እንደሚያደርጓቸው ትናንት ተናግረዋል። «በፖላንድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችም ሆነ አቃቤ ህግ እንደ ተቋም ሥራቸውን በሚያካሂዱበት መንገድ ላይ እንዲዚህ ዓይነት ተጽእኖዎችን ማሳደሩ ታይቶ  የማይታወቅ እንደሆነ አጽንኦት ልሰጠው እወዳለሁ። እናም ይህ ተቀባይነት የለውም መወገድ አለበት ከሚሉት ጋር እስማማለሁ። »

ዱዳ  የመንግሥትን ድጋፍ ካገኙት ሦስት ህጎች መካከል ያልተቀበሏቸው ሁለቱ በሀገሪቱ ደህንነት እና ፍትህን ያሰፍናሉ የሚል እምነት የላቸውም ። በፖላንድ ለአቃቤ ህግ ይህን የመሰለ ሰፊ ሥልጣን የመስጠት ልምድ እንደሌለ ያስታወሱት ዱዳ አሁን በጸደቀው ረቂቅ እንደማይስማሙ ግልጽ አድርገዋል። ሆኖም  የሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት መሻሻል እንዳለበት አልካዱም።  ህግ አውጭዎቹ ያቀረቧቸው ለውጦች ጨቋኝ ሥርዓት እንዳይፈጥሩ ግን ስጋት አላቸው። የሰሞኑ ተቃውሞዎች እንደሚያሳዩት ለውጦቹ ህብረተሰቡን መከፋፈላቸው አይቀርም ያሉት ዱዳ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ይደረግ የተባለው ለውጥ መንግሥትን ከህብረተሰቡ መለየት የለበትም ብለዋል።  ዱዳ እንደተናገሩት ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ማሻሻያ ተብሎ የተረቀቀው ህግ ለምክር ቤቱ ከመመራቱ በፊት ለርሳቸው አልመድረሱ ሌላው ችግር ነው። 

«ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የተመለከተው ረቂቅ ህግ ወደ ምክር ቤት ከመመራቱ በፊት ለኔ ባለመቅረቡ አዝናለሁ። በዚህ ሳቢያም በኔም ሆነ በሌሎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው ወገኖች በኩል ምክክር ማካሄድ አልተቻለም። ስለዚህ የሚከተለው ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ። ወደ ምክር ቤቱ ተመልሼ  ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እና ብሔራዊ የፍትህ ሥርዓቱን የሚመለከቱትን ስርዓቶች ውድቅ አደርጋለሁ።»

ዱዳ እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት በጉዳዩ ላይ ጠበቆችን የማህበራዊ ጉዳዮች አዋቂዎችን ፖለቲከኞችን እና የፍልስፍና ምሁራንን ጨምሮ ከብዙ ጠበብት (አዋቂዎች) ጋር መመካከራቸውን ተናግረዋል። ከሁሉም በላይ ግን «ክቡር ፕሬዝዳንት አቃቤ ህግ ለማመን የሚያስቸግር ሥልጣን በያዘበት እና ሁሉንም ነገር ማድረግ በሚችልበት መንግሥት ውስጥ ነው ኖሬያለሁ። ወደዚያ መንግሥት መመለስ አልፈልግም።»ያሏቸው  በጎርጎሮሳዊው 1970ዎቹ እና በ80 ዎቹ ፀረ ኮምኒስት ታጋይ የነበሩት ሶፍያ ሮማሴቭስካ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድሩባቸው እንደቻሉ ትናንት ተናግረዋል። ከትናንቱ የፕሬዝዳንት ዱዳ ውሳኔ በኋላ ወግ አጥባቂው የፖላንድ መንግሥት የፕሬዝዳንቱን እርምጃ በመቃወም ማሻሻያዎቹ ተግባራዊ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል ትናንት  አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤአታ ሲዚድሎ በቴሌቪዥን ማምሻውን ለህዝባቸው ባሰሙት ንግግር ፕሬዝዳንቱ ማሻሻያዎቹ እንዲጓተቱ ቢያደርጉም ፓርቲያቸው የህግ እና የፍትህ ፓርቲ በምህጻሩ PiS የፍትህ ሥርዓቱ ለውጥ እስኪደረግበት ድረስ ከእርምጃው  ወደ ኋላ እንደማይል አስታውቀዋል። 

«ለየጎዳናዎቹ ተቃውሞዎች እና ለውጭ ተጽእኖዎች አንንበረከክም። የፖለቲካ እና የግል ፍላጎቶቻችንን ወደ ጎን ትተን የፖላንድ ህዝብ ከኛ የሚጠብቀው ላይ ማተኮር አለብን። የማይናጋ አብላጫ ድምጽ አለን። በተፈጠረው ጫና አንመራም። መርሃ ግብራችንን ከዳር እናደርሳለን። ተስፋ እንዳትቆርጡ እጠይቃለሁ።ቃል የገባንባቸውን ጉዳዮች እናሟላለን።ፖላንድን እንጠግናታለን።» 

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ይህን ቢሉም እንደገና ወደ ፓርላማ የሚመሩት ማሻሻያዎቹ እንዲጸድቁ ከምክር ቤቱ አባላት ከ3 አምስተኛ በላይ ድምጽ መገኘት አለበት። PiS ደግሞ ይህን ያህል ድምጽ የለውም። ዱዳ ከባለሞያዎች ጋር ሰፊ ውይይት ካካሄዱ በኋላ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እና የፍትህ ምክር ቤቱን ማሻሻያ አዳዲስ ህጎች በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ አርቅቀው እንደሚያቀርቡም ቃል ገብተዋል።

የዱዳ እርምጃ ህጎቹን እንዲጥሉ ሲወተውቷቸው ከነበሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት አድናቆት ተቸሮታል። ይሁን እና ዱዳ ሦስተኛውን እና የበታች ፍርድ ቤቶችን አሠራር የሚመለከተውን ህግ ማጽደቃቸውን ግን አልተቀበሉትም። ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንቱ ሦስተኛውንም ህግ ውድቅ እንዲያደርጉ እየጠየቁ ነው። ሦስተኛው ህግ ለሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ለፖላንድ የበታች ፍርድ ቤቶች ሃላፊዎችን መሾም የሚያስችል መበት ይሰጣል።የሲቪክ መድረክ የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ግዤጎዥ ሴትና ፕሬዝዳንት ዱዳ አንድ ህግ መጣል ይቀርዎታል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። 

«ከጥቂት ቀናት በፊት ይህ ህግ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ነው ብዬ ነበር። እናም ትክክል ነበርኩ። ሦስት ጊዜ ድምጽን በድምጽ መሻር የዚህ ቀውስ መፈክር ነው። በዚህም መጽናት አለብን። እናም ለፕሬዝዳንቱ  አንድ ውድቅ የሚያደርጉት ህግ እንደሚቀራቸው ዛሬ ልነግራቸው እፈልጋለሁ። ይህ የበታች ፍርድ ቤቶችን የሚመለከት በጣም አስፈላጊ ህግ ነው። ምክንያቱም ህጉ አቃቤ ህግ ለሚሆነው  የገዥው የህግ እና ፍትህ ፓርቲ ተወካይ ፖለቲከኛ ፍርድ ቤቶችን የማስተዳደር ሃላፊነትን እንዲይዙ ያደርጋልና። ይህ አደገኛ ነው።»   
ኖቮቴስና ወይም ዘመናዊ ፓርቲ የተባለው የሌላው ተቃዋሚ ፓርቲ የቀድሞ መሪ ሪሻርድ ፔትሩ የፕሬዝዳንት ዱዳን እርምጃ አድንቀው ሆኖም የሦስተኛው ህግ አለመሻር ለሌባ ሌላ መንገድ እንደ መክፈት የሚቆጠር ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። 

«ፕሬዝዳንቱ ከሃላፊነታቸው የተወሰነውን ክፍል ተወጥተዋል። ሌቦች እንዳይገቡ እንዳደረገ ጠባቂ ነው የሠሩት። ሆኖም ሦስተኛውን ህግ አለመሻራቸው አሁንም ሌባው የጓሮ በሮችን መጠቀም ይችላል ማለት ነው። የፖላንድን የፍትህ ሥርዓት የሚሰብረውን ሦስተኛውን ህግ ፕሬዝዳንቱ እንዲሽሩት ጥሪ እናቀርባለን።»

የፍትህ ስርዓቱን ነጻነት ይገድባሉ በሚል በሀገር ውስጥ ተከታታይ ተቃውሞዎች ሲካሄዱባቸው የቆዩት ረቂቅ ህጎቹ ከምዕራቡ ዓለምም ትችቶች ሲሰነዘሩባቸው፤ ማስጠንቀቂያዎችም ሲሰጡባቸው ነበር። ፓርላማው ያጸደቃቸው ህጎች የቀኝ ክንፉን የፖላንድ መንግሥት ከአውሮጳ ህብረትም ጋር አጋጭቷል። የአውሮጳ ህብረት ህጎቹን የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ፣የተጠያቂነት እና የሚዛናዊነትን አሠራር የሚጻረሩ በማለት አጣጥሏቸዋል። የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን በህጎቹ የተካተቱት ማሻሻያዎች በዚህ ሳምንት ካልተነሱ ፖላንድ ላይ ማዕቀቦችን እንደሚጥልባት አስጠንቅቆ ነበር። የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት  የቀድሞ የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ መንግሥት በእቅዱ የሚፀና ከሆነ ሀገሪቱ ከአውሮጳ ህብረት ልትገለል እንደምትችል አስጠንቅቀው ነበር። ህብረቱ ፖላንድን በህብረቱ ውስጥ የመምረጥ መብት ሊነፍግ እንደሚችል ሲዝት ቆይቷል።

በሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት ላይ እንደተቃጡ ጥቃቶች ከተቆጠሩት ሦስት ህጎች ዱዳ ሁለቱን መሻራቸው ከገዥው የህግ እና የፍትህ ፓርቲ በምህጻሩ ከPiS መሪ ከያሮስላቭ ካዚንስኪ ጋር መለያያታቸውን በይፋ ያረጋግጣል  ተብሏል። ዱዳ በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም የገዥው ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ሆነው የቀረቡት በካዚንስኪ ከተመረጡ በኋላ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶም እስካሁን የፓርቲውን ወግ አጥባቂ ብሔራዊ አጀንዳ በታማኝነት በመደገፍ ፓርቲው የሚያወጣቸውን ህጎች ያለ አንዳች ተቃውሞ ሲያሳልፉ ቆይተዋል።

ካዚንስኪ በአውሮጵላን አደጋ ከሞቱት ከቀድሞው የፖላንድ ፕሬዝዳንት እና ከመንታ ወንድማቸው ሌህ ካዝንስኪ ጋር የPiS መሥራች ናቸው። ህጎቹን ህዝብ ሳይመክርባቸው የፖላንድ ፓርላማ እንዲያጸድቃቸው መደረጉ የዋርሳውን መንግሥት በማን አለብኝነት አስወቅሶታል። በጎርጎሮሳዊው 2015 በተካሄደ ምርጫ 38 በመቶ ድምጽ አሸንፎ ሥልጣን የያዘው የፖላንድ ገዥ ፓርቲ PiS ህጉን ካጸደቀ በኋላ ከአውሮጳ ህብረት እና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከባድ ወቀሳ ቢቀርብበትም ለመረጠው ህዝብ ታማኝ ሆኖ መቀጠሉን ነው የመረጠው።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች