የፖሊሶችን ጥፋት ያጋለጠችው ሶኒያ ኡመር ማን ናት? | ወጣቶች | DW | 15.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

የፖሊሶችን ጥፋት ያጋለጠችው ሶኒያ ኡመር ማን ናት?

ቅርብ ጊዜ አንዲት ወጣት ሴት በሁለት የፖሊስ መኮንኖች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስትደበደብ የሚያሳየውን ቪዲዮ በፍጥነት ተሰራጭቶ ጉዳዮ የከተማዋ ከንቲባ ጋር ሳይቀር ደርሶ ነበር። ለመሆኑ ከዚህ ቪዲዮ በስተ ጀርባ ያለችው ወጣት ሶኒያ ኡመር ማን ናት?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:16

የወጣቶች ዓለም: ጠብ-መንጃዋ የእጅ ስልኳ ነበር

ሕግ አስከባሪዎች ሕግ ሲጥሱ አብዛኛውን ጊዜ ተበዳዮች ተጎድተው ከማለፍ በቀር ብዙ አማራጭ አልነበራቸውም። አሁን አሁን ግን በተለይ ከፖሊስ ጋር አለመግባባት ሲፈጠር ብዙ ሲቪሎች በእጅ የሚይዙትን ስልክ እንደ ጠብ-መንጃ ይመዛሉ። ከዛም ወይ እየተከናወነ ያለውን ነገር በቀጥታ እየቀረጹ እንደ ፌስ ቡክ ባሉ ገፆቻቸው ያስተላልፋሉ አልያም የቀረፁትን ቪዲዮ ቆየት ብለው በማኅበራዊ መገናኛ ገፆች ያሰራጫሉ። ሶኒያ ኡመር ከሰሞኑ ይህንን ለማድረግ ተገዳለች። አጋጣሚው አንዲት ወጣት በሁለት የፖሊስ መኮንኖች አዲስ አበባ ውስጥ ያለርህራሄ ስትደበደብ የታዘበች ጊዜ ነው። « ስልክ እያወራሁ ነበር። ድምጿን ስሰማ በጣም ደንግጬ ስልኩን ዘጋሁና ሁኔታውን መታዘብ ጀመርኩ፤ ለማገላገል አቅሜ ስለማይፈቅድ ቪዲዮውን ለመቅረፅ ተገደድኩ» 
ከዚያም ሶኒያ «ለሚመለከተው አካል ማድረስ ከቻልኩኝ በሚል» ቪዲዮውን በፌስ ቡክ እና ኢንስታግራም ገጾቿ ላይ ለጠፈችው። ውጤቱም ፈጣን ነበር። ብዙ ሰዎች ቪዲዮዋን ተቀባበሉት። ጉዳዩም የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጋር ደርሶ እሳቸውም በትዊተር ገፃቸው፤ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቱን አወገዙ። ፖሊሶቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ክትትል እንዲያደርጉም ገለፁ። ይህ ብቻም አይደለም። ተደብዳቢዋ ወጣት እናት መጠለያ እና ህክምና እንድታገኝ እንደሚመቻች እና በአንድ ምገባ ማዕከል ውስጥም ሥራ እንደምትጀምር ይፋ አደረጉ።  ሶኒያ ይህንን አጭር ቪዲዮ ለወጣቷ እናት ፍትህ ለመጠየቅ ስትቀርፅ የተደብዳቢዋን ሕይወት ምን ያህል ሊቀይር እንደሚችል አላወቀችም። ከሆነ በኋላ ግን በውጤቱ ደስተኛ ናት። « እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልጠበኩም ነበር። ምላሹ በጣም ደስ ይላል። የከተማችን ከንቲባ ፈጣን ምላሽ ነው የሰጡት።»  በማለት ደስታዋን የለገለፀችው ሶኒያ ፖሊሶቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ሚናም ጉልህ እንደነበር ለዶይቸ ቬለ DW ገልጿለች። 

Kalifornien | Denkmal im San Diego Museum | George Floyd

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፖሊስ አንገቱ ከመሬት ጋር ተጣብቆ «መተንፈስ አልቻልኩም» እያለ ሲማጸን በማኅበራዊ መገናኛ የታየው የጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ቪዲዮ በሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሃገራትም በፖሊስ የተፈፀመውን ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ይፋ አድርጓል

በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ  ከተማ የምትኖረው የ 23 ዓመቷ ወጣት ሶኒያ የጅማ ልጅ ናት። የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ተማሪ ስትሆን ሥራ ፈላጊ ናት።  « በተማርኩበት ሙያ ስራ ባገኝ ደስ ይለኛል» የምትለው ሶኒያ በተለያዩ ቦታ ለመስራት ያመለከተች ቢሆንም እስካሁን ስራ አላገኘችም።  ሶኒያ የቀረፀችውን ቪዲዮ ይዛ ወደቤት ከሄደች በኋላ እህቷን ነው ያማከረችው። እህቷም የማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንድትለጥፈው አበረታታቻት። ወጣቷ ቪዲዮውን ካዩ ሰዎች ያገኘችውም ምላሽ አመረታታች እንደነበር ትናገራለች። አብዛኛው ሰው ግን ከዚህ ቪዲዮ በስተጀርባ ያለችውን ልጅ በአካል አያውቋትም።  ቪዲዮው  በግል ሕይወቷ ላይ ተፅዕኖ እንዳይኖረው የምትጠነቀቀው ሶኒያ እስካሁን በዕለት ከዕለት ሕይወቷ ውስጥ ይህ ብዙም የተለየ ነገር አልፈጠረባትም። የተለየው ነገር ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰጡትን አስተያየት ለማንበብ ሶኒያ ከወትሮው የበለጠ ጊዜዋን ኢንተርኔት ላይ ታጠፋለች።
ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ገብታ እንደማታውቅ የገለፀችልን ሶኒያ ቪዲዮውን ከተመለከቱትም ሆነ ፈጣን ምላሽ ከሰጡ ወገኖች ያገኘችው ምላሽ ጥሩ ስለነበር ወደፊት እንደዚህ አይነት ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶች ሲፈፀሙ ብታይ ለማጋለጥ ቆርጣ ተነስታለች። ሌሎች ወጣቶችም የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዘዴዎችን ለበጎ እንዲያውሉ እና ወንጀልን ለማጋለጥ እንዲበረታቱም ትመክራለች።  ቪዲዮውን በቀረፀችበት ወቅት ፖሊሶቹ ሽጉጥ መያዛቸው ቢያስፈራትም ሁኔታው ስሜቷን ስለነካው « የመጣው ይምጣ» ብላ ለመቅረፅ ወስናለች።
ሶኒያ ወደፊት ቀን ቀን እየሠራች ማታ ማታ ደግሞ ለዲግሪ ትምህርትዋን የመቀጠል አላማ አላት።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ገለሠ

Audios and videos on the topic