የፖሊስ ዘመቻ፣ የድሬ ግጭትና ሚሊዮናት ለጌዲኦ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 17.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የፖሊስ ዘመቻ፣ የድሬ ግጭትና ሚሊዮናት ለጌዲኦ

የድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ በከተማው የተከሰተው ግጭትን ማብረዱን ሲያስታውቅ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ሕገወጥ ያላቸው ላይ በምሽት አሠሣ ዘመቻ ተጠምዶ ነበር።  በ«ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት» በኩል ለጌዲኦ ተፈናቃዮች የተሰባሰበ 31.4 ሚሊዮን ብር ርክክብ መደረጉ የተሰማውም እዛው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:37

«ርዳታውን በብሔር ልንመነዝረው ከሞከርን በጣም ወደ እንስሳነት እየሄድን ነው»

በድሬደዋ ከተማ በሰርግ ስነስርዓት ላይ ጀምሮ መልኩን ቀየረ የተባለው ግጭት በከተማው በረድ ማለቱ ሲነገር፤ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ግን አገርሽቶ ነበር። ከባድ ድብደባ የደረሰባቸው ተማሪዎች ወደ ሐኪም ቤት ሲወሰዱ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ አንዳንድ ተማሪዎች ደግሞ ወደ መጣንበት ክልል እንመለሳለን ማለታቸው ተሰምቷል። ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ ከጊቢው እንዳይወጡ ማድረጉም ተገልጧል። የድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ በከተማው የተከሰተው ግጭትን ማብረዱን ሲያስታውቅ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ሕገወጥ ያላቸው ላይ በምሽት አሠሣ ዘመቻ ተጠምዶ ነበር።  በ«ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት» በኩል ለጌዲኦ ተፈናቃዮች የተሰባሰበ 31.4 ሚሊዮን ብር ርክክብ መደረጉ የተሰማውም እዛው አዲስ አበባ ውስጥ ነው።  

ግጭት በድሬዳዋ ከተማ

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በብሔር ነክ ግጭት ጉዳት ደርሶባቸው ቢያንስ ሁለት ተማሪዎች ሆስፒታል ገብተዋል። ከዚህ ግጭት ቀደም ብሎ ከተማዪቱ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ለሦስት ቀናት ውጥረት ሰፍኖባት ነበር። በሰርግ ሥነሥርዓት ላይ ተቀሰቀሰ የተባለው ግጭት ወደ ቡድን ግጭት ተሻግሮ ድሬዳዋ ከተማ ላይ ስጋት አጥልቶ አልፏል።

«ድሬ ባለጋሪው» የተሰኘ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «መንግስት ድሬዳዋ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል» ሲል ጽሑፉን ይጀምራል። «ድብን አርገው ሰርግ በልተው እናት አባት ህፃናት ወጣቶች ተደብድበዋል» ያለው ድሬ ባለጋሪው፦ «አድማ በታኝ ችግር ፈጣሪዎችን መያዝ ሲችል ንፁሀን ወንድሞቻችን ላይ ተፅኖ አድርጓል። አሁን መከላከያ ሰላም አውርዶ ቢሄድም ቸል ሊባል አይገባም፤ አንድ ተቋም እኩል ማገልገል አለበት» ብሏል።

«የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ወደ ግጭት ማስተማሪያነት ተቀይረው ቀሩ በቃ» ሲል ትዝብቱን ያካፈለው ደግሞ ፋኖ ፋኖ የተባለ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው። ዳኒ ፈረደ ለማ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «አይ የዘንድሮ ተማሪዎች ተምራችሁ አገር ትገነባላችሁ ብለን ስንጠብቅ በወረደ በዘር ላይ ተመስርታችሁ ትጋጫላችሁ» በማለት ትዝብቱን አስፍሮ በእንግሊዝኛ ቋንቋ «ታሳፍራላችሁ» በማለት ጽሑፉን ያጠቃልላል።

የአቡ ሰዒድ መልእክት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚታየው ብሔር ተኮር ግጭት የውጭ ጋዜጣ ርእስ መኾኑ የከነከነው ይመስላል። «የእንግሊዙ ታዋቂው ኢኮኖሚስት ጋዜጣ ኢትዮጵያ በብሄርና ጎሳ ፖለቲካ እየታመሰች መሆኑን ጠቅሶ በመፈናቀል ከዓለም የመጀመሪያው ረድፍ ቁጥር 1 ላይ አስቀምጧታል፡፡ ታድያ ከእዚህ በላይ ውርደት አለ?» በማለት ጠይቋል። «ይህ በዓለም አደባባይ በእዚህ መልክ መፈረጃችን ሁላችንንም አንገት አስደፍቷል» ሲልም ቁጭቱን አስፍሯል።

ዘ ኢኮኖሚስት የተሰኘው ጋዜጣ በእርግጥም ረቡዕ ግንቦት 7 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ለንባብ ባበቃው ጽሑፉ፦«ከድርቅ፤ ረሐብ እና ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያን የጎሣ ግጭት እያመሳት ነው» የሚል ርእስ ይዞ ወጥቷል። ከተመሰረተ 176 ዓመታት ያስቆጠረው አንጋፋው ጋዜጣ፦ «ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ትግሏ ከድርቅ እና ጠኔ ጋር» መኾኑን ጠቅሶ ያም በመኾኑ «ሰዎችም ምግብ እና ውኃ ፍለጋ በየጊዜው እንዲንቀሳቀሱ ያደርግ ነበር» ብሏል። አሁን ሌላ አሳሳቢው ጉዳይ መደቀኑን ሲያስረግጥ፦ «አሁን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሽሽታቸው ግጭትን ነው» ሲል አስነብቧል።

«ዘረኛ ወጣት ከማስተማር ፡ ሙዚየም ቢያደርጉት ይሻላል፡ ግለሰብ በተጣላ ቁጥር ወደ ብሔር ማዞር ፋሽን ሆነ» የአዲሱ ማቴዎስ መልእክት ነው። ጎበና ለማ፦ «የጎጥ ፖለቲካ መጨረሻው ይኼና ገና ወደፊት የምንሰማቸው እና የምናያቸው ጉዶች ናቸው። ይልቁንስ፤ ጎሣን መሰረት ያደረገ ፖለቲካን እምቢኝ በሉ» ብሏል።

አዲስ አበባ ፖሊስ ዘመቻ

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ብሔር ነክ ያለውን ግጭት ለማብረድ ከተማሪዎች ጋር ውይይት ላይ እንደነበር በገለጠበት ወቅት ከአዲስ አበባ የተሰማው ዜና በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ፖሊስ ድንገተኛ የምሽት ዘመቻ እንዳኪያሄደ ነው።  በዘመቻው የአዲስ አበባ ፖሊስ ከ200 በላይ ሕገ-ወጥ አሽከርካሪዎችን እንደያዘ ገልጧል። መጠኑ ያልተገለ ሕገ-ወጥ መድሐኒትና 23 ሞተር ብስክሌቶች እንዲሁም ከ2500 የሚበልጡ የሺሻ ማጤሲያዎች መያዛቸውን ፖሊስ ለዶይቸ ቬለ ዐስታውቋል።

ይኽን ዘገባ የሰማ ቼ ጉ ቬራ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ጫትና ሺሻ ከምድራችን መጥፋት አለበት አምራች መሆን የሚገባው ወጣት እኮ በሱስ ተጥመልምሏል» ብሏል። «ነገ ሀገር ማን ይረከባል?- ሲል የጠየቀው ቼ ጉቬራ፦ «ኧረ ትውልድ ይዳን» ሲል ጽሑፉን ቋጭቷል። «ዝም ብሎ የሰዉ ቤት ዘው ብሎ መፈተሽ አለ እንዴ? ይደብራል» ያለው ጆኒ ጸጋዬ ነው። «ተጠነክሮ መቀጠል አለበት!» ያለው ደግሞ ሴና ገመቹ ቢቂላ ነው። «እግረ መንገድ ሕገ ወጥ ፖሊሶችንም ሾፍ ማድርግን [መመልከት]አትርሱ» የሚል አስተያየትም አክሏል።

ጌዲዮን ተካ፦ «ጥሩ ነው! ከዚህ የበለጠ ሥራ ከፖሊስ ይጠበቃል» በማለት ጽሑፉን ያንደረድራል። «የተደራጀ ዘረፋና በመኪና የታገዘ ንጥቂያ በሰሚትና አካባቢው ስለበረከተ ቢተኮርበት መልካም ነው» የሚል መልእክትም አስተላልፏል። ፖሊስ በድንገተኛ አሠሣው ያዝኳቸው ካላቸው ሕገወጥ ቊሳቊሶች በተጨማሪ ከዚሕ ቀደም በሠሯቸዉ ወንጀሎች የሚፈለጉና የሚጠረጠሩ ያላቸውን 8 ሰዎች በቊጥጥር ሥር ማዋሉንም ተናግሯል። 

ግሎባል አሊያንስ ድጋፍ

ሌላው በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ርእሰ ጉዳይ የነበረው «ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት»  ከ31.4 ሚሊዮን ብር በላይ ለወርልድ ቪዥን የማስረከቡ ዜና ነው። ገንዘቡ በጌድዮ ጉጂ ዞን ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም እንደሚውል በርክክቡ ወቅት ተነግሯል።

ኢንተርኔት ላይ ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥሪ የተደረገበት የጎ ፈንድ ሚ ማሰባሰቢያ 1 ነጥብ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ግብ አስቀምጦ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር መስብሰቡን ያሳያል። በሁለት ወራት ጊዜያት ውስጥም  17.941 ሰዎች ርዳታ በመስጠት መሳተፋቸውን ረቡዕ፤ ግንቦት 6 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ኢንተርኔት ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ያመለክታል።

«ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት» ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለርዳታ መሰብሰቡን በርካቶች በማድነቅ ምሥጋና ሰንዝረዋል። ገንዘቡ ለምን ለእዚህ እና ለእዚያ አልተሰጡም የሚሉ አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል። ጉሬ ኩምሳ በእንግሊዝኛ የፌስቡክ ጽሑፉ፦ «ለቤንሻንጉል ጉሙዝ ነዋሪዎች፤ ለመተከል እና ጃዊ አካባቢዎችስ?» ብሏል።

አብዱጀባር ሙስጠፋ ኢብራሂም፦ «ምንድነው ወደ ብሄር መቀየር? ለጉጂ ጌዲዬ ተብሎ ከመጣ መጀመሪያ ጉጂ እና ጌዲዬ ወደ ቄዬው ይመለስ እና ያብቃ ከዛ ደግሞ ወደ ሌላው መመለስ ይቻላል እንጂ ብሩ የተባለው መጀመሪያ ለታለመለት ውሎ ካበቃ ወደ ሌላው የባሰበት መዞር ነው። ምንያቱም በአሁኑ ሰዓት ከዚህ አካባቢ በላይ በቁጥርም ሆነ በጉዳት የተጎዳ አለ ብዬ አላምንም» የሚል አስተያየቱን አስነብቧል።   

የሻላ ሲምቦ ገለቶ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፦ «የጌዲኦ ተፈናቃዮች ከሌላው ተፈናቃይ ትኩረት ያገኘው በፖለቲካዊ ፍላጎት ወይስ በምንድነው? የሀገሪቷ ተፈናቃይ ዜጎች በሙሉ የሀገሪቷ ተፈናቃይ ናቸውና ለምን በእኩል አለመታየቱ መጣ? ተፈናቃዮችንም ለፖለቲካ መጠቀም ያሳዝናል» ይላል።

የ«ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት» ፕሬዚደንት ታማኝ በየነ በገንዘቡ ርክክብ ወቅት ያስተላለፈው ቀጣዩ መልእክት ኢንተርኔት ላይ በርካቶች ዘንድ ደርሷል።

«ርዳታውን በብሔር ልንመነዝረው ከሞከርን በጣም ወደ እንስሳነት እየሄድን ነው። ኢትዮጵያዊ የኾነ ዜጋ ሁሉ ርዳታ ማግኘት አለበት። ስንዴን በብሔር መለካት አይቻልም። ስለዚህ የምናደርገው ዜጎች ኹሉ መፈናቀል የለባቸውም። ዜጎች ኹሉ በተፈጥሮ መብት ያሉበት መሬት ላይ የመኖር መብታቸው መኾኑ መታመን አለበት። በዚህ መንፈስ ነውና የምንሠራው ከተለያየ አቅጣጫ ለበጎ ምግባር የተጀመረውን እንኳን ለማጣመም ሲሞከር ያሳዝናል። አሳባችን አንዱን ብሔር ለመርዳት አንዱን ለመግፋት አለመኾኑን እንድትረዱ እፈልጋለሁ።»

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች