1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት ሲካሄድ የቆየው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት

ዓርብ፣ ኅዳር 20 2017

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ላለፉት ዘጠኝ ወራት ሲያደርጉት የነበረው ውይይት መቋጨቱን ቦርዱ ዛሬ አስታወቀ። ፓርቲዎቹ በስምንት ዋና ዋና ጉዳዮች እና 50 ንዑስ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4naS4
የፖለቲካ ፓርቲዎች
ፓርቲዎቹ በስምንት ዋና ዋና ጉዳዮች እና 50 ንዑስ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል። ምስል Solomon Muche/DW

የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት 

 የፓርቲዎቹ የውይይቱ ሂደት ከስድስት ዓመታት በፊት የተጀመረ ቢሆንም ከግንቦት 2015 ዓ.ም ጀምሮ በመድብለ ፓርቲ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥራዓት ግንባታ፣ በምርጫ እና ምርጫ ነክ ጉዳዮች፣ በሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች፣ በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ፣ በውጪ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ቆይተዋል። ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎቹ የተወያዩባቸውን አጀንዳዎችን የያዘውን ሰነድ ፈርሞ ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ግብዓት እንዲሆን በሚል ዛሬ አስረክቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱይህንን የፓርቲዎች ውይይት ማዕቀፍ ሂደት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ አዘጋጅቶት የነበረው «በወቅቱ የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንድ ፓርቲ ተሞልቶ ስለነበር እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወያዩበት መድረክ አስፈላጊ ስለነበር» መሆኑን የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ አስታውቀዋል። የውይይት ሂደቱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የፌዴራሊስት ንቅናቄ የሚባል ስብስብ ተመስርቶ ስለነበር 2014 ዓ. ም ላይ ተቋርጦ ቆይቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በአቀረቧቸው እና ቅደም ተከተላቸውን በቀረጹላቸው አጀንዳዎች ላይ ከግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ተከታታይ ጊዜ መካሄዱን የገለፁት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ ሂደቱ ቀላል የሚባል ተግባር እንዳልነበር በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረዋል።

ምርጫ ቦድር
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ይህንን ፓርቲዎች የተወያዩበትን ሰነድ ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክቧል።ምስል Solomon Muche/DW

ፓርቲዎቹ በስምንት ዋና ዋና ጉዳዮች እና 50 ንዑስ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን ይህም ለሀገር የሚበጅ ሂደት እንደነበር የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ገልፀዋል።

ውይይቱ በተለያዩ ባለሙያዎች በጥናትና ምርምርበቀረቡ ሀሳቦች መነሻ ምክክር የተደረገባቸው ናቸው ተብሏል። ዋናው የምክክሩ ዋጋ ግን ሰነዱ ወደ ተጨባጭ ሥራ እንዲለወጥ በማድረግ ለፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፍ መነሻዎች ሆነው እንዲያገለግሉ ጥቅም ላይ ማዋል ነው ተብላል።

ቦርዱ ከዚህ ውይይት ባገኛቸው ግብአቶች መነሻ የሕግ ማሻሻያዎችን ማድረግ መጀመሩንና ሌሎችም ጥቅም ላይ እንዲያውሉት ጠይቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ይህንን ፓርቲዎች የተወያዩበትን ሰነድ ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክቧል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ