የፖለቲካ ውጥረት በጊኒ ቢሳው | አፍሪቃ | DW | 22.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የፖለቲካ ውጥረት በጊኒ ቢሳው

በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጊኒ ቢሳው አዲስ የፖለቲካ ቀውስ ተፈጠረ። የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ኾዜ ማርዮ ቫዝ በጠቅላይ ሚንስትር ዶሚንጌስ ሲመስ ፔርየራ የተመራውን መንግሥት ከአስር ቀን በፊት ከሥልጣን ካሰናበቱ በኋላ ሕገ መንግሥታዊ ውጥረት ተፈጠረ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:40
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:40 ደቂቃ

የፖለቲካ ውጥረት በጊኒ ቢሳው

ይኸው እየተካረረ የሄደው ውጥረትም በቅርቡ የሚረግብ አይመስልም። ይህ ልዩነት በሃገሪቱ ለቀጣዩ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መንገድ ከፋች እንዳይሆንም የጊኒ ቢሳው ጎረቤት ሃገራት ሰግተዋል።

ጊኒ ቢሳውን ለገጠማት ቀውስ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ለማስገኘት ከተፈለገ ጦር ኃይል በፖለቲካው ጣልቃ መግባት እንደማይገባው እና የጊኒ ቢሳው ፕሬዚደንት ኾዜ ማርዮ ቫዝ ሃገሪቱ ከምትገኝበት ውዝግብ የምትወጣበትን መንገድ ማፈላለግ እንደሚኖርባቸው የሴኔጋል ፕሬዚደንት ማኪ ሳል ጉዳዩን በቅርብ በመከታተል ላይ በሚገኘው በምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ድርጅት ፣ በምህፃሩ ኤኮዋስ ስም አስጠንቅቀው ነበር። አሁን በመሀሉ፣ ፕሬዚደንቱ ባለፈው ሀሙስ ባቺሮ ጃንን ከሥልጣን ያሰናበቱትን የቀድሞ መንግሥት የሚተካውን አዲስ መንግሥት እንዲመሩ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው ሾመዋል።

Guinea-Bissau Ministerpräsident Baciro Dja

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ባቺሮ ጃ

ይሁንና፣ ይኸው ውሳኔአቸው ከራሳቸው የቀድሞው የነፃነት ታጋይ እንቅስቃሴ እና በአህፅሮት "ፔይጄክ" በመባል ከሚታወቀው እና ሃገሪቱ ከፖርቱጋል ቅኛ አገዛዝ ከተላቀቀች እጎአ ከ1974 ዓም ወዲህ ገዢውበመምራት ላይ ከሚገኘውፓርቲ አባላት ብርቱ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፣ ከስራ የተባረሩት የፕሬዚደንቱ የፓርቲ አቻ ዶሚንጎስ ፔርየራ ትክክለኛ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

« የ"ፔይጄክ" መመሪያዎች ግልጽ ናቸው። ፓርቲው በምርጫ ካሸነፈ ያኔ የፓርቲው ፕሬዚደንት ጠቅላይ ሚንስትር ይሆናል። እና የፖርቲያችን ፖለቲካ ጽሕፈት ቤት አሁንም ይህንኑ እምነቱን በኔ ላይ ለመጣል በመወሰን፣ የሃገራችንን መንግሥት እንድመራ መርጦኛል። »

ፕሬዚደንት ቫዝ ጠቅላይ ሚንስትሩን ያሰናበቱት ሙስናን አስፋፍተዋል፣ ስልጣናቸውን ዘመዶቻቸውን ለመጥቀሙ ተግባር አውለውታል እና ፍትሕን አስተጓጉለዋል በሚል ሰበብ ፣ በተጨባጭ ከውጭ የተገኘው የርዳታ ገንዘብ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ በመጥፋቱ መሆኑን አስታውቀዋል።

« የመንግሥቱ አባላት በጠቅላላ እንኳን በአዲሶች ቢተኩም የተቋማቱን አሰራር ያበላሸውን የፖለቲካ ቀውስ በቀላሉ ማስተካከል አይቻልም። በኔ እና በጠቅላይ ሚንስትሩ መካከል መተማመን ጠፍቷል። »

Geberkonferenz von Guinea-Bissau in Brüssel Domingos Simoes Pereira

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ዶሚንጎስ ሲመስ ፔርየራ

ከስልጣናቸው የተባረሩት ፔርየራ ግን ፕሬዚደንት ቫዝ የሰነዘሩትን ወቀሳ ሁሉ ሀሰት ሲሉ አስተባብለው የባቺሮ ጃን ሹመት እንደማይቀበሉት ገልጸዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ባቺሮ ጃ የሃገሪቱን መረጋጋት ለማረጋገጥ ሕዝቡ ተባብሮ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል። እንደሚታወሰው፣ በውጭው ዓለም በጊኒ ቢሳው በ2014 ዓም የተካሄደው ምርጫ ሃገሪቱን ለዘለቄታው ያረጋጋል የሚል ተስፋ ፈንጥቆ ነበር። ያኔ ዴሞክራሲን እና ኤኮኖሚያዊ እድገትን ለማነቃቃት የአውሮጳ ህብረት ስርዓት ለዚችው ሃገር 160 ሚልዮን ዩሮ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅትም ብዙ ሚልዮን ዶላር ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር። የሰሞኑ ቀውስ ገና ያልተጠናከረውን የጊኒ ቢሳው መረጋጋት እንዳያደፈርስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መስጋቱን የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ፌዴሪካ ሞጌሪኒ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ አስጠንቅቀዋል። የፖርቱጋል የዓለ,ም አቀፍ ግንኙነት ጥናት ተቋም ተንታኝ ፓውሎ ጎርኻዎም ዓለም አቀፍ አጋሮች በጊኒ ቢሳው በሚታየው ሂደት እንዳልተደሰተ ነው የገለጹት።

Belgien Brüssel Eröffnung der Geberkonferenz von Guinea-Bissau

የለጋሽ ሃገራት ስብሰባ

« በዚሁ ሂደት ዓለም አቀፍ አጋሮች ከብዙ ዓመታት ወዲህ ተሰላችተዋል። ፖርቱጋል በተሳተፈችባቸው ብዙ ስብሰባዎች ላይ ባለወረቶች ገንዘባቸውን በጊኒ ቢሳው እንዲያሰሩ የማግባባቱ፣ ሃገሪቱ ውስጥ በተደጋጋሚ በሚከሰተው ፖለቲካ ቀውስ የተነሳ አዳጋች ሆኖዋል። ያሁኑ ቀውስም ይህንኑ ጥረት ይበልጡን አስቸጋሪ ማድረጉን እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም ባለወረቶች ገንዘባቸውን እንደመጣል ነው የሚቆጥሩት። »

በዓለም ባንክ መዘርዝር መሠረት፣ ጊኒ ቢሳው ከዓለም 10 እጅግ ድሃ ሃገራት አንዷ ናት፣ ከሕዝቧ መካከል ከሁለት ሦስተኛው የሚበልጠው ድሃ ነው። በድሃው ሕዝብ አንፃር በሃገሪቱ በሕገ ወጡ የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ የተሠማሩት ወንጀለኞች ናቸው ሀብታሞቹ። ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር የኮሎምቢያ አደንዛዥ ዕፅ ኮኬይን ወደ አውሮጳ የሚተላለፍባት ዋነኛዋ ሀገር ናት።

አርያም ተክሌ/ዩሊያ ሀን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic