1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖለቲከኞች አስተያየት ሥለ ብርቱካን ሚዴቅሳ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 20 2015

የ2013 ዓ.ም ምርጫ ለምሳሌ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አልተጠናቀቀም ፣ መንግሥት አልትመሰረተም፣ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች እና በሌሎች ክልሎች ምርጫ ያልተደረገባቸው ቦታዎች አሉ ፣ በ2015 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ የነበረው የአካባቢ ምርጫ እስካሁን አልተደረገም።

https://p.dw.com/p/4T83Q
Bild 1. Birtukan Mideksa Chairperson of National Election Board of Ethiopia
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የወይዘሪት ብርቱካን ስኬትና ዉድቀት

   

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ከአራት ዓመታት በላይ የመሩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በዘመነ-ሥልጣቸዉ ሥላከናወኑት ምግባር በጎም  መጥፎም አስተያየት እየተሰጠ ነዉ።ወይዘሪት ብርቱካን ኃላፊነታቸዉን በፈቃዳቸዉ ለመልቀቅ መወሰናቸዉን ትናንት አስታዉቀዋል።ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወይዘሪት ብርቱካን በዘመነ ሥልጣን ሶስት ሕዝበ-ዉሳኔዎችና አንድ አጠቃላይ ምርጫ መርቷል።በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸዉን ከሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አንዳዶቹ የብርቱካንንና የመሩትን ቦርድ ስራና ጥረት ሲያደንቁ፣ ሌሎቹ ግን ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ ማዕከል እንደሆነ ነዉ ይላሉ።

«ጤናዬን በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት የሚያስፈልገኝ ሆኖ በመገኘቱ ከ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ሰብሳቢነቴ በገዛ ፍቃዴ  መልቀቄን ለተወካዮች ምክር ቤት ዐፈ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም አሳውቄያለሁ" በማለት የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ትናንት ያስታወቁት ብርቱካን ሚዴቅሳ የቦርዱን ተአማኒነት በማሻሻል ረገድ እና የፓለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴዎች ለማገዝ አደረግነው ባሉት ጥረት ስኬታማ እንደነበሩ ገልፀዋል።
ቦርዱ በእነዚህ ዓመታት ለኢትዮጵያ ሥርዓት ያለው የፓርቲ ውድድር መር የፖለቲካ ባሕል ዝርጋታ ስላበረከተው አወንታዊም አሉታዊም ጥረት ከጠየቅናቸው ፓርቲዎች ምካከል የቦሮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ አንዱ ናቸው። 
"ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ፣ በየ ዓመቱ በጀት እንዲያገኙ ጥረት አድርገዋል። ቦርዱ ከጋራ ምክር ቤቱ ጋር መልካም ግንኙነት ነበረው። ብዙ ፓርቲዎች በዚህ መልቀቂያ የመደናገጥ ስሜት ተሰምቷቸዋል" ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አርማ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አርማምስል Yohannes Geberegziabher/DW

የ2013 ዓ.ም ምርጫ ለምሳሌ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አልተጠናቀቀም ፣ መንግሥት አልትመሰረተም፣ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች እና በሌሎች ክልሎች ምርጫ ያልተደረገባቸው ቦታዎች አሉ ፣ በ2015 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ የነበረው የአካባቢ ምርጫ እስካሁን አልተደረገም። ዶክተር መብራቱ እንዳሉት የመንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የገዢው ፓርቲ ፍላጎቶች ጎልቶ የሚታይበት እና ፈታኝ ቦታ ነው ያሉት ምርጫ ቦርድ አሁን ሁሉንም አቻችሎ የሚመራ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የአመራር ምደባ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። 

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና "ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀውስ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል ፣ የወይዘሪት ብርቱካን አመዳደብ ላይ ልዩነት ነበረን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦርዱን ሰብሳቢ የመሾም ስልጣን ቢኖራቸውም ፓርቲዎች ከሚመርጧቸው ሰዎች መኃል በመምረጥ ነው ሊሾሙ የሚገባው በማለት በቀጣይም ከአንድ ወገን ሹመት መውጣት አልብን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ( ኢሶዴፓ ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ዶክተር ራሔል ባፌ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መቋቋሙ ትልቅ ነገር ሆኖ ሳለ ነገር ግን የወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዐዋጅ ይህንን የጋራ ምክር ቤት ከቦርዱ ሥር ሆኖ በራሱ ነፃነት ቆሞ የሚንቀሳቀስ አካል ማድረግ አለመቻሉ ትልቅ ጉድለት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወይዘሪት ብርቱካ የተጀመሩ የሕዝበ ውሳኔ ሥራዎችን ፣ ያልተጠናቀቁ የምርጫ ሂደቶችን ጨራርሰው ቢወጡ የተሻለ እንደሆነና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የቀረበለትን የመልቀቂያ ጥያቄ እንደገና ቢያየው ጥሩ ነው ብለዋል። 

ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በአንድ ስብሰባ ላይ
ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በአንድ ስብሰባ ላይ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ወይዘሪት ብርቱካን በስልጣን ዘመናቸው የመሩት ምርጫ ቦርድ ሦስት ሕዝበ ውሳኔዎችን እና አንድ ሀገራዊ ጥጠቅላላ ምርጫን አካሂዷል ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎችን አስተዳድሯል፣ 27 ዓመት ኢትዮጵያን የገዛውን ኢሕአዴግን እና በግንባሩ ቁልፍ ሚና የነበረውን ሕወሓትን አክስሟል ፣ ኢዴፓን የመሳሰሉ ጠንካራ ፓርቲዎችን ፈቃዳቸውን ነጥቆ ከፖለቱካ ምህዳረ አስወጥቷል። በተለይ በቅርቡ ሕወሓት ዳግም ሕጋዉ ሰውነቱን ለማስመለስ የጀመረው ጥረት የቦርዱ ሰብሳቢ ላይ ጫና ሳያሳድርባቸው እንዳልቀረ በመግለጽ ብዙዎች መልቀቂያው ከጤና ችግር ብቻ እንደማይሆን እየተንጋገሩበት ይገኛል። ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ 2011 ዓ.ም ላይ ነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በመሆን የተሾሙት።

ሶሎሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ