የፕሮቶኮሉ ሰው፣ ኢቢሲ እና ኢሬቻ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 06.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የፕሮቶኮሉ ሰው፣ ኢቢሲ እና ኢሬቻ

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ «የፕሮቶኮል ሹም» ናቸው የተባሉ ሰው ለስራ በተጓዙበት አሜሪካ ለመቅረት መወሰናቸው እና ማንነታቸዉ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት እሁድ በቢሾፍቱ የተከበረው የኢሬቻ ዓመታዊ ክበረ በዓል የኢትዮጵያ መንግስት በሚቆጣጠረዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሽፋን አለማግኘቱ በርካታ ትችቶች ቀስቅሶ ነበር፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:03 ደቂቃ

የኢቢሲ ማስተባበያ ይበልጥ ትችቶች አስከትሏል

ጉዳዩ መጀመሪያ የተደመጠው ማክሰኞ ምሽት ነበር፡፡ በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ (ቪኦኤ)፡፡ የሬድዮ ጣቢያው ዘግየት ብሎ ዜናውን በድረ ገጽ ሲያወጣ ብዙዎች ወዲያውኑ ነበር የተቀባበሉት፡፡ ርዕሱ “የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮቶኮል ኃላፊ ከዱ” ይላል፡፡ ከዜናው ጋር የተያያዘ ፎቶ ለሰውየው የተሰጠውን የአሜሪካ ቪዛ ያሳያል፡፡ በቪዛው ላይ የሰውየው ስም ባዬ ታደሰ ተፈሪ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ምስላቸውም ተካትቷል፡፡ ቪዛው የተሰጣቸውም ከሁለት ሳምንት በፊት ኒውዮርክ በተካሄደው 72ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲገኙ እንደሆነም ይጠቁማል፡፡

እርሳቸው የተካተቱበት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተመራው ልዑክ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ሰውየው ግን በአሜሪካ የፖለቲካ ጥገኝነት ለመጠየቅ መወሰናቸው በዜና ዘገባው ላይ ተገልጿል፡፡ “በመንግስት እና በጸጥታ ኃይሉ መካከል የተፈጠረው ከፍተኛ መከፋፋል ለእኔም ሆነ ለሀገሪቱ አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ” በአሜሪካ ለመቅረት ወስኜያለሁ ብለዋል አቶ ባዬ፡፡ ዜናውን በፍጥነት ያጋሩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች የሰውየውን የስራ ድርሻ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ከታዘቧቸው የፕሮቶኮል ግድፈቶች ጋር እያነጻጸሩ ተሳልቀዋል፡፡ 

በስላቃዊ ጽሁፎቹ የሚታወቀዉ አበበ ቶላ (በብዕር ስሙ አቤ ቶኪቻው)  በጉዳዩ ላይ ተከታታይ አስተያየቶች ካስነበቡ መካከል አንዱ ነው፡፡ አቤ ቶኪቻው ረቡዕ ዕለት በፌስ ቡክ ገጹ “ ‘የአቶ ሃይለማሪያም ፕሮቶኮል ከዱ’ የሚለው ዜና ላይ በጣም አስገራሚው ነገር ሰውየው ለካ እስከዛሬ ፕሮቶኮል ነበራቸው? የሚለው ነው። እስቲ የአቶ ሃይለማሪያምን ፕሮቶኮል የሚያሳየን ፎቶግራፎች አዋጡ፡፡ ድሮውኑም የፕሮቶኮል ሃላፊው የስራ ማቆም አድማ ላይ ነበሩ የሚያስብሉ ብዙ አስቂኝ ፎቶግራፎችን በዛ ሰሞን ስናይም አልነበር…?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ 

ሳሙኤል አራጌ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚም ተመሳሳይ ሀሳብ አላቸው፡፡ “የአቶ ኃይለማሪያም ፕሮቶኮል ኃላፊ ከዱ የሚል ወሬ ሳነብ በማንዴላ ቀብር ላይ ሰውየውን ቢራቢሮ ከረባት አስሮ እንዲሄድ ያደረጉ ጊዜ አደል እንዴ የከዱት [ብያለሁ]” ሲሉ አስተያየተቻውን አጋርተዋል፡፡ ልዋ በትዊተር “አንድ የቤተ መንግስት ፕሮቶኮል አገር ጥሎ ጠፋ ተብሎ ይህ ሁሉ ከተወራ እኔ ብጠፋ እንዴት ሊወራ ነው” ሲሉ ቀልደዋል፡፡ ሄኖክ ጸጋዬ ደግሞ በዚያው በትዊተር “ህይወቴና የቤተመንግስት ታላላቅ ሚስጥሮች የሚል መጽሃፍ በቅርብ ጊዜ እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡ 

ጌታቸው ሽፈራው  በበበኩሉ ተከታዩን አስተያየት በፌስ ቡክ ገጹ ሰጥቷል፡፡  “ትህነግ/ኢህአዴግ ፕሮቶኮል አያውቅም። ገዥዎቹ ፕሮቶኮል የሚያሳያቸውን ሳይሆን ተንኮል የሚመክራቸውን ነው የሚቀጥሩት። ለስሙ ካልሆነ በስተቀር የፕሮቶኮል ሹም የሚባለውን ይጠቀምበታል ለማለት ይከብዳል። ካላቸው እንኳ ከሙያ ይልቅ በዘመድ አዝማድ፣ በታማኝነት የመጣ እንጅ በሙያው ሊቀጠር አይችልም። ሙያውን የሚያውቁ ፕሮቶኮል ሹምና ዲፕሎማት እንደሌለ ኦባማ በመጣ ወቅት እንደዛ ሲንጋደዱና ሲደናበሩ አስተውለናል። የአቶ ኃይለማርያም የፕሮቶኮል ሹም ከዳ ተብሎ ካድሬዎቹ ተበሳጭተዋል። ለምን ይህን ያህል እንደተበሳጩ ግራ ያጋባል። ሀይለማርያምን ስልጣን የለውም ብሎ የሚያስብ ህዝብ ሰውዬው ሊያጋልጥ ይችላል ስለሚባለው የፕሮቶኮል ዝርክርክነት ቁም ነገር ብሎ ሊጨነቅለት አይችልም። ከቀልድና ፌዝ ያለፈ!” ብሏል።

ጌታቸው በጽሁፉ ጠቆም እንዳደረገው አቶ ባዬ ከዱ የሚለው ዜና ከተሰማ ጀምሮ በመንግስት ደጋፊነታቸው የሚታወቁ የፌስ ቡክ ጸሃፊዎች “የሰውየው እውነተኛ ማንነት ነው” የሚሉትን በማጋለጥ ተጠምደዋል፡፡ አቶ ባዬ የፕሮቶኮል ኃላፊ ሳይሆኑ ቀድሞ “አትክልተኛ የነበሩ” አሁንም ደግሞ አንዳንዶቹ ቡና እና ሻይ አቅራቢ፤ ሌሎቹ ደግሞ “የመስተንግዶ ሰራተኛ ናቸው” ሲሉ ምንጮቻቸውን እየጠቀሱ አጣጥለዋቸዋል፡፡ በማስተናገድ ስራ ላይ ሳሉ የተነሷቸውን ፎቶዎች በማስረጃነት ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ ይህ አካሄድ መንግስት ዘመም የሚባለዉን ጦማሪ ዳንኤል ብርሃነን ሳይቀር ያስገረመው ይመስላል፡፡ “የመንግስት የፌስቡክ ፔጆች የአቶ ባዬ ታደሰን ስም ለማጥፋት ዘመቻ መክፈታቸው ጠቃሚም አስፈላጊም አይመስለኝም። ውሸት ከሆነ ማስተባበል ቀላል ነው። በአሁን ሰዓት የፕሮቶኮል ሀላፊ የሚሰራው እና የሌሎች ሹመኞች ማንነት ይነገረን። ዲሞክራሲያዊ በሆኑ ሀገሮች እነዚህ ነገሮች ሚስጥር አይደሉም። በመንግስት ደረጃ የግለሰብ ስም ማጥፋት ውስጥ መግባት አይገባም” ሲል በፌስ ቡክ ገጹ ጽፏል፡፡

በመንግስት ጎራ የቆሞት ረዳኢ ገብረእግዚአብሔር በፌስ ቡክ ገጻቸው ምክር ለግሰዋል፡፡ “አንድ ጥገኛ ተሳደብን ብለን የተከበረ ሙያ እየዋረድንና የሌሎች ሞራልም እየነካን እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡ ፕሮቶኮል አንድ ትልቅ ስራ ነው፡፡ ፕሮቶኮል ላይ የተሰማራ ደካማ ሰው ካደ ተብሎ ድሮስ የሻይ ቡና አቅራቢ አይደለም እንዴ ስንል ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥም እንዳይሆን! በኔ እምነት ሰውየው ከቤተ መንግስት ስለ ከዱ ከዳተኛ እንበላቸው፡፡ ስራቸው ግን ሌሎች ዜጎችም የሚሰሩት ወይም የተሰማሩበት የተከበረና መልካም የስራ መስክ ስለሆነ እሳቸውን ለመሳደብ ሲባል የስራ መስኩ ወይም ሙያውን ማቃለል ተገቢ አይደለም፡፡ ከተፈለገ ሰውየው በግል አገር የካዱ ስለሆኑ ከሃዲ ወይም ጥገኛ ማለት የተሻለ ይመስለኛል” ሲሉ ከወቀሳ እንዲታቀቡ መክረዋል፡፡

ሰላም ስዩም ደግሞ ተከታዩን በፌስ ቡክ አጋርተዋል፡፡ “የፕሮቶኮል ሐላፊ ነው፣ የከረቫት ፕሮቶኮል ነው፣ የሱሪ ፕሮቶኮል ነው፣ የሻይ ቡና ፕሮቶኮል ነው የሚለው ንትርክ ቀጥሏል ። ሰውየው ይሻለኛል ብሎ የመረጠውን መርጧል ... መቼስ! ባጭሩ ቁልፍ የሚይዝ ቁልፍ ሰው ነው ካልተባለ የነበረውን ስራ [ምንነት] ዜናውን ያመጡልን ሰዎች ከቪዛው ይልቅ የሰውየውን መታወቂያ ቢያሳዩ አይሻልም ነበር? እንዲህ ማለቴ አንድም የቪዛው ፎቶ ጥቅም ስላልታየኝ አንድም መታወቅያው ቢታይ የተነታሪኮቹ ንትርክ አቅጣጫው ይቀይር ነበር በሚል ነው” ብለዋል፡፡

መላኩ ብርሃኑ በሌላኛው ወገን ያሉ ሰዎች በተደጋጋሚ ከሚያነሱት አመክንዩ ጋር የሚቀራረብ መከራከሪያ በፌስ ቡክ አጋርቷል፡፡ “አሁን ጠፉ የተባሉት ሰውዬ ፕሮቶኮል ሃላፊ ካልሆኑ ወይም ለሌላ ስራ ካልተመደቡ በቀር፤ ‘ሻይ ለማፍላት ሲባል ጠቅላይ ሚኒስትሩን አጅበው ኒውዮርክ ድረስ ሄደው ነበር’ ለማለት በእውነቱ እቸገራለሁ። እንዲያ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድም ሻይ አፍዪና አቅራቢያቸውን ኒውዮርክ ወስደው የሚያስጎበኙ ደግ ሰው ናቸው፣ አልያም እንደጋዳፊ አይነት ብኩንነት ሊጀማምራቸው ነው ማለት ነው” ብሏል፡፡ 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር አቶ ዳግም አፈወርቅ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ለዶይቼ ቬለ ሙያዊ አስተያየታቸውን አካፍለዋል፡፡ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ እያበረከቱት ካለው አስተዋጽኦ አንዱ በነባሩ የጋዜጠኝነት ሙያ እና መገናኛ ብዙሃን የሚፈጸሙ ስህተቶችን የመንቀስ እና ማጋለጥ እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡ “ማህበራዊ ሚዲያው እንደውም አንዳንዴ ዋንኛው ጋዜጠኝነት ያሉበትን ችግሮች ሁሉ እንደ ተቆጣጣሪ (watch dog) ሆኖ ሁሉ ያገለግላል፡፡ ዋናው ጋዜጠኝነት (conventional journalism) ያየኃቸውን ችግሮች እያነሳህ የምትወያይበት መድረክ ነው” ብለው ነበር መምህሩ፡፡ 

የመምህሩን አባባል በማስረጃ ለማስደገፍ በዚህ ሳምንት የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች መወያያ የሆነውን ርዕሰ ጉዳይ መጥቀስ ይበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የተሰኘው ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለፈው ሳምንት እሁድ የተከበረውን የኢሬቻ ክብረ በዓል በሌሎች ሃይማኖታዊም ሆነ ህዝባዊ በዓላት እንዳስለመደው በቀጥታ ስርጭት አላስተላለፈም፡፡ ጣቢያው የበዓሉን አከባበር እንዴት እየዘገበው እንደነበር ከዋዜማው ጀምሮ ሲከታተሉ የቆዩት የፌስ ቡክ እና ትዊትር ተጠቃሚዎች በኢቢሲ ላይ ትችቶች አዝንበዋል፡፡

ለቀናት የቀጡለት እነዚህ ትችቶች ያሳሰቡት የመሰሉት ኢቢሲ ረቡዕ ዕለት ከአንድም ሁለቴ ማስተባበያዎችን በፌስቡክ ገጹ አወጣ፡፡ ማስተባበያዎቹ ይበልጥ ነቀፌታዎችን ማስከተላቸውን ያስተዋለው ኢቢሲ ሁለቱንም መግለጫዎቹን በአጭር ጊዜያት ውስጥ ከይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ መልሶ ማጥፋቱ አነጋግሯል፡፡ የጣቢያዎቹን ማስተባበያዎች “በስክሪን ሾት” ያስቀሩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች መግለጫዎቹን እየተቀባበሉ የኢቢሲን መከራከሪያዎች አብጠልጥለዋል፡፡ 
ሚልኪሳ ጪምዴሳ ወዳጆ በፌስ ቡክ ገጻቸው “ኢቢሲ በኦሮሞ አክቲቭስቶች ስም የማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደብኝ ነዉ አለ፡፡ የኢሬቻ በዓልን በልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ መሰረት የዘገብኩ ቢሆንም በማህበራዊ ሚዲያ በእኔ ላይ ያነጣጠረ  ዘመቻ ተከፍቶብኛል ብሏል ኮርፖሬሽኑ፡፡ አረ ተዉ እናንተ ሰዎች ያለ ፕሮግራማችን አታስቁን!” ብለዋል፡፡ ሳሙኤል ኃይለስላሴ በዚያው በፌስ ቡክ “ ‘የኢሬቻ በዓል ለምን የቀጥታ ሽፋን አልተሰጠውም’ ለሚለው ቅሬታ ኢብኮ የ ‘ኢሬቻን በዓል ለማክበር ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ገና ከዋዜማው ነበር’ የሚል መልስ ሰጥታለች፡፡ ያው የለመድነው ነው እንግዲህ፡፡ እንደወትሮው ቅሬታን አድማጭ የለም። ጥያቄውና መልሱ አልተገናኘም፡፡ካልተጣላ በቀር ካልራቀ ከነብሱ፤ ደህና ዋል አይሆንም ለደህና ደር መልሱ፡፡ ብለናል! ያ ሌላ ይሄ ሌላ” ሲሉ አስተያየታቸውን በግጥም አስደግፈው አስፍረዋል፡፡

ዳዲ ዲ ጎሳ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ “ ጥፋታችሁን ሌላ ላይ ለማላከክ ከመጣር ይቅርታ ጠይቁ” ሲሉ ለጣቢያው ምክር አስተላልፈዋል፡፡ ሳምቤ ቦና “የአዞ እምባችሁ ተቀባይነት የለውም፡፡  ድሮም የእኛ አልነበራችሁም ወደፊትም የእኛ አትሆኑም፡፡ ከህዝብ ጋር አብራችሁ እስካልቆማችሁ ድረስ ህዝብ ተቃራኒያችሁ ነው የሚሆነው” ብለዋል በፌስ ቡክ፡፡ 

የኢሬቻ በዓል ዕለት ጉዳዩን የታዘቡት ኪያ ኪኮ ደግሞ “ኢቢሲ ትልቁን የምስጋና ቀን ኢሬቻን ሳይዘገብ ቀረ፡፡ ብሔራዊ መግባባት የመገንቢያ መንገዱ ይሄ ነውን? የትኛው ክልል ነው ትልቁ ግብር ከፋይ? ከየትኛው ክልል ነው ለውጭ ገበያ የሚላከው አብዛኛው ምርት የሚመጣው? ይህ በቅርቡ ይቀየራል” ሲሉ በፌስ ቡክ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
ኪያብ ሄልሂቭሜብ ወርቅ “ስለ መገናኛ ብዙሃን ለምን እንጨነቃለን?” በሚል ርዕስ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን በህዝብና በመንግስት ባለስልጣናት፣ በተለያዩ ማህበረሰቦች፣ በተለያዩ ሀገራት መካከል ለሚደረግ ወዳጅነትና መወራረብ፣ መግባባትና መተማመን ለመፍጠር ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የባህል መወራረስን፣ አዲስ ባህል የማምጣትም ሆነ የነበረውን የመበረዝ እንዲሁም የአንዱን አካል መጥፎም ሆነ ጥሩ ሀሳብ ወይም ፍላጎት ወደሌላው በግድ እንዲጫን በማድረግ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ በጥቅሉ ግን መገናኛ ብዙሃን እንዳጠቃቀሙ በሁሉም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፤ እያሳደረም ይገኛል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ እንደሀገር ፍትሀዊ ሚዲያ ሊኖረን ይገባል እያልኩኝ ሁሌም የምከራከረው” ብለዋል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ
 

Audios and videos on the topic