የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ስልጣን ዘመን መራዘም | አፍሪቃ | DW | 25.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ስልጣን ዘመን መራዘም

የደቡብ ሱዳን ምክር ቤት የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን የስልጣን ዘመን ለተጨማሪ ሶስት ዓመታት አራዝሟል። ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን እስከ ጎርጎሮሳውያኑ 2018 በፕሬዝዳንትነት መንበረ ስልጣኑ ላይ የሚያቆየው ውሳኔ በዋና ከተማዋ ጁባ በሚገኙ ተቃዋሚዎች ዘንድም ተቀባይነት አላገኘም። የፖለቲካ ተንታኞች ግን ጉዳዩ አዲስ አይደለም እያሉ ነው።

መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የደቡብ ሱዳንን የሰላም ድርድር ከተቃዋሚያቸው ሪየክ ማቻር እኩል አደናቅፈዋል የሚል ትችት የቀረበባቸው ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የስልጣን ዘመናቸውን ለተጨማሪ ሶስት ዓመታት አራዘሙ። የደቡብ ሱዳን ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱን የስልጣን ዘመን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር እስከ 2018 ድረስ ማራዘሙን ተሰምቷል። የደቡብ ሱዳንን የፖለቲካ ምስቅልቅል የሚከታተሉት ኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም ዓቀፍ ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አቤል አባተ «ከአንድ ወር በፊት የፕሬዝዳንት ስልጣን የማራዘም ጥያቄውን አጽድቆት ነበር» ሲሉ ጉዳዩ አዲስ አለመሆኑን ይናገራሉ።

የፕሬዝዳንቱ የስልጣን ዘመን በተራዘመበት በትናንትናው እለት የተሰበሰበውና 15 አባላት ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር መደናቀፍ እንዳስቆጣው አስታውቋል። ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንቱ ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቻር በፖለቲካ ልዩነታቸው የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት ባለመቻላቸው እና የሰላም ድርድሩ በመደነቃቀፉ ተጠያቂ መሆናቸውንም ገልጿል። የአፍሪቃ ህብረት የደቡብ ሱዳንን ቀውስ አስመልክቶ ባዘጋጀው ይፋ ባልሆነ ዘገባ ሁለቱ መሪዎች ከስልጣን እንዲወገዱ ሃሳብ ማቅረቡን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የጸጥታው ምክር ቤት ካሁን ቀደም ያቀረባቸውን የጦር መሳሪያ ግዢን ማገድ እና የከፍተኛ ባለስልጣናትን እና ሐብታቸውን ዝዉዉርን የመንፈግ ማዕቀብ እንደገና አቅርቧል።

የደቡብ ሱዳን ምክር ቤት ቃል አቀባይ ቶማስ ኩንዱ የፕሬዝዳንቱ የስልጣን ዘመን መራዘም በአገራቸው ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር አስፈላጊ ነው ሲሉ መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ውሳኔው ፕሬዝዳንቱን በስልጣን ለማቆየት የተደረገ ሲሉ ተቃዋሚዎች ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት አዲስ አበባ ላይ ሲካሄድ በነበረው ድርድር ከተቀናቃኛቸው ጋ የሽግግር መንግስት ለመመስረት በሂደትም ምርጫ ለማካሄድ የገቡትን ቃል የዘነጉት ወይም የናቁት ይመስላል። ውሳኔው አሁን በተቋረጠው ድርድር ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ የፖለቲካ ተንታኞች ያምናሉ። አቶ አቤል አባተ የደቡብ ሱዳን መንግስት ውሳኔ በድርድሩ ከሚሳተፉ አካላት ምን አይነት አቀባበል እንደሚያገኝ ለመናገር አስቸጋሪ ነው መሆኑን ተናግረዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የደቡብ ሱዳን ቀውስ ከ110,000 በላይ የአገሪቱ ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መጠለያዎች እንዲኖሩ አስገድዷል። እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሆነ ሌሎች 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በዚያው በደቡብ ሱዳን 500,000 ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት ለመሰደድ ተገደዋል።

በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት እና የጎረቤት አገራት አማካኝነት ሲካሄድ የከረመው ድርድር በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ተቋርጧል። ለያዥ ለገራዥ ያስቸገሩት ተቀናቃኝ ሃይሎችም ጋብ ብሎ የነበረውን ጦርነት እንደገና የጀመሩት ወዲያውኑ ነበር። የሰላም ድርድሩ መቼ፤ እንዴት እና የት ሊቀጥል እንደሚችል እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። የአፍሪቃ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግን ወደ ማዕቀቡ ያዘነበሉ ይመስላል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic