የፕሬዝዳንት ሙላቱ ንግግር | ኢትዮጵያ | DW | 09.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የፕሬዝዳንት ሙላቱ ንግግር

በየዓመቱ ለሦስት ወራት እረፍት የሚበተነው የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወደ መደበኛ ስብሰባዎቹ የሚመለሰው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በሚያደርጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ጭምር በሚታደሙበት በዚህ የመክፈቻ ስብሰባ ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ መንግሥትን የዓመቱን ዕቅዶችን እና የትኩረት አቅጣጫዎች የሚዘረዝሩበት ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 06:23
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
06:23 ደቂቃ

የምርጫ ህጉ ከመጪው ምርጫ በፊት ይሻሻላል ተብሏል

ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ለተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች አባላት ያሰሙት እና በብሔራዊ ቴሌቪዝን በቀጥታ የተላለፈው ንግግር አንድ ሰዓት ገደማ የፈጀ ነበር፡፡ ንግግራቸው ከኢኮኖሚ፣ እስከ መሰረት ልማት ግንባታ፣ ከትምህርት እስከ ጤና ያሉ ዘርፎችን እንደሁም የወጣቶችን እና ሴቶችን ጉዳይ የዳሰሰ ነበር፡፡ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተነሱት በንግግራቸው ማብቂያ ግድም ነው፡፡  

የዛሬ ዓመት በተመሳሳይ የመክፈቻ ንግግራቸው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች በቀዳሚነት ካነሷቸው ሁለት ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ የወቅቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆነው የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ግጭት በዛሬው ንግግር ከተካተቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የመጨረሻ ስፍራ ተሰጥቶታል፡፡ ፕሬዝዳንት ሙላቱ የሁለቱን ክልሎች ጉዳይ ያነሱት ባለፈው ዓመት ለ10 ወራት በሀገሪቱ ታውጆ ከቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር አያይዘው ነው፡፡ 

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሀገሪቱ ጸጥታ ወደተረጋጋ ሁኔታ መመለሱን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ለግጭቶች መንስኤ የሆኑ የድንበር ማካለል ጉዳዮችም ከሞላ ጎደል በሁሉም አካባቢ ለመፍታት መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም “በኦሮሚያ እና በኢትዮ ሶማሌ አካባቢ ያልተስተካከሉ አፍራሽ አመለካከቶች የወለዷቸው ግጭቶች ተከስተው የሰው ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ መጥፋቱን”፣ መንግሥታቸው በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም እና ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በሚከተለዉ መልኩ ገልጸዋል፡፡ 

“ይህ ሁኔታ በፍጽም መወገዝ ያለበት እና መንግስት ጸጥታውን ከማስከበር ባሻገር አጥፊዎቹን ወደ ህግ ለማቅረብ ሳይታክት እየሰራ ይገኛል፡፡ በ2010 ዓ.ም እንደዚህ ዓየነት በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነት የሚያፈርስ አካሄድ በጭራሽ ሊፈቀድ የሚገባው ባለመሆኑ የሁለቱም ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ባህላዊ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ሴቶች፣ እንደዚሁም መላው የሁለቱ ክልል ህዝቦች ሁኔታው ወደነበረበት እንዲመለስ እና የተፈናቀሉ ወገኖች ወደነበሩበት ተመልሰው እንዲቋቋሙ ለማድረግ ከመንግስት ቀን መልሰው እንዲቆሙ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን ለማቅረብ እፈልጋለሁ ብለዋል” ፕሬዝዳንት ሙላቱ፡፡    

በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች መካከል ለተከሰቱ ግጭቶች ሀገሪቱ የምትከተለውን በብሄር ላይ የተመሰረተ የፌዲራሊዝም ስርዓትን ተጠያቂ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው በዝርዝር ባይገልጹትም ከፌዴራላዊ ስርዓት ጋር የተያያዙ ሕጎች እንደሚወጡ ጠቁመዋል፡፡  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ዓመት ይጸድቃሉ ተብለው የሚጠበቁት አዋጆች እና ፖሊሲዎች “የፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቶችን በተጠናከረ መሠረት ላይ እንዲገነባ የሚያስችሉ” መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ሙላቱ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ አዋጆች መካከል የሀገሪቱ የምርጫ ስርዓትን በተመለከተ ሊደረግ ታስቦ የነበረው ማሻሻያ አንዱ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ዓመት ንግግራቸው ኢትዮጵያ የምትመራበትን የምርጫ ሕግ በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚዎች መካከል በሚደረግ ድርድር እንደሚሻሻል አስታዉቀዋል፡፡ የሚሻሻለው የምርጫ ሕግ “አሁን ያለውን የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ከተመጣጣኝ ውክልና ስርዓት ጋር በትክክለኛ ሚዛን ያጣመረ” እንደሚሆንም አብራርተው ነበር፡፡ ሕጉ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድምጽ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች  እንዲኖሩ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንደሚስተካከልም ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ በዛሬ ንግግራቸው ይህንኑ አዋጅ በድጋሚ አንስተዋል፡፡ 

“ከእነዚህ ውስጥም ባለፈው ዓመት የምርጫ ስርዓታችንን በተመለከተ ሊደርግ የታሰበው ማሻሻያ ውይይት ሲካሄድበት የቆየ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ለተከበረው ምክር ቤት ቀርቦ ለ2012 ዓ.ም ለሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ እንዲደርስ የሚደረግ ይሆናል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡

የቀድሞው አንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ የምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት አላቸው፡፡ “የዛሬ ዓመት ለሚቀጥለው ዓመት የምርጫ ህጉ ይሻሻላል ብለዋል፡፡ የምርጫ ህጉን ለማሻሻል ሕገ መንግስት ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ያሉ ጽሁፉን ያዘጋጁ ሰዎችም አያውቁም፡፡ ፕሬዝዳንቱም አያውቁም ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው መጨረሻ ላይ መጥተው ይህንን ጽሁፍ ለመከላከል ሲመጡ እስከዚያ ደቂቃ ድረስ ህገ መንግስት ማሻሻል ቢያስፈልግ እንኳ ይደረጋል ብለው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ መጥተው ለሚቀጥለው 2012 ዓ.ም ለሚደረገው ምርጫ የምርጫ ህጉ የሚሻሻልበት ስራ በምክር ቤት ይጸድቃል ይላሉ፡፡ እንግዲህ የእዚያ ሰው ይበላቸው” ሲሉ አቶ ግርማ ይናገራሉ፡፡

ሕጉ ከመሻሻሉ በፊት ግን በዚህ ዓመት በመላው ሀገሪቱ የአካባቢ እና ማሟያ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ምርጫው “ዲሞክራሲያዊነቱን ጠብቆ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ” ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፓርላሜንታዊ ስርዓት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ገዢው ፓርቲ ከሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ያለውን ውይይት በአዎንታዊነት ጠቅሰዋል፡፡ ውይይቱ “የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንዲጎለብት እና የፖለቲካ ምህዳሩም ይበልጥ እንዲሰፋ” እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ መንግሥታቸው ሊያደርግ ያሰበውን ደግሞ እንዲህ አስረድተዋል፡፡ 

“መንግስት ሁሉም ያገባኛል የሚሉ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ሁሌም በሩን ክፍት አድርጎ ለሂደቱ ስኬታማነት የሚሰራ ይሆናል” ሲሉ የመንግስታቸውን ፍላጎት ተናግረዋል፡፡

አቶ ግርማ ሰይፉ “በፓርቲዎች መካከል ውይይት እየተደረገ ነው” የሚለውን የፕሬዝዳንቱን ገለጻ አይቀበሉም፡፡ “የተጀመረው የፓርቲ እና የመንግስት ውይይት ይላሉ፡፡ አሁን ፓርቲ የመንግስት ውይይት ተጀምሯል ብለው የእውነት  ያምናሉ ማለት ነው? አሁን ተሰብስበው ውይይት እያደረጉ ያሉትን ሰዎች በምን አይነት ደረጃ እንደሚመዝኗቸው አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ጋር እየተነጋገርን ነው ብለው በአደባባይ ወጥተው ህዝብን መዋሸት በጣም ያሳፍራል” ይላሉ አቶ ግርማ፡፡

የፕሬዝዳንቱ ንግግር ሌላው የጊዜው አነጋጋሪ ጉዳይ የሆነውን የሙስና ጉዳይንም ነክቷል፡፡ አላግባብ የመጠቀም እና የሙስና ጉዳዮች ጎልተው በሚታዩባቸው ዘርፎች መንግሥት ባለፈው ዓመት ተሃድሶ ማካሄዱን ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተናግረዋል፡፡ ተሃድሶ ከተመለከታቸው ዘርፎች ቀልጣፋ እና ውጤታማ የፍትህ ስርዓት ማምጣት፣ የፖሊስ እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ማሻሻል እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

የግብር ስርዓት፣ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር፣ ግዢ እና የግንባታ ሥራዎች ኮንትራት አስተዳደር፣ የመሬት ልማት እና አቅርቦት፣ የመሬት አስተዳደር እና ግንባታ ፍቃድ አሰጣጥ፣ በውድድር ላይ የተመሠረት የንግድ ስርዓት እና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴም ሌሎች በተሃድሶው የተካተቱ ዘርፎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ተሃድሶው በአንዳንድ ቦታዎች ውጤታማ መሆን መጀመራቸውን ገልጸው በብዙ ቦታዎች ግን ገና በዝግጅት ላይ ያሉ እና የተጓተቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መንግሥታቸው በዘርፎቹ ውስጥ በሚስተዋለው ሙስና ላይ ስለሚወስደው እርምጃ ደግሞ ተከታዩን ብለዋል፡፡ “በእነዚህ ዘርፎች በሙስና ተግባር ላይ የተሰማሩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ተባባሪዎቻቸውን በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ የተጀመረው ስራም በ2010 ዓ.ም በጥናት ላይ ተመስርቶ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል” አቶ ሙላቱ፡፡  

ለኢኮኖሚዊ እና ተዛማጅ ጉዳዮች አብዛኛውን ቦታ የሰጠው የፕሬዝዳንት ሙላቱ ንግግር ባለፈው ዓመት መልዕክታቸው ቁልፍ ጉዳይ የነበረውን የወጣቶች ጉዳይ በአለፍ ገደም ጠቅሶ አልፏል፡፡ የቀድሞው የምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ስለፕሬዝዳንቱ ጠቅለል ያለ አስተያየታቸውን ያጋራሉ፡፡ “ሁልጊዜ ተስፈኛ ስለሆንኩ፣ ተስፋ ስለማድረግ ይሆናል የተሻለ ነገር ለማድረግ መጠቀም የሚችሏቸውን አዲስ ምዕራፎች (milestones) ሳይጠቀሙባቸው እያለፉ ነው ያሉት፡፡  ለውጥ ሊኖር የሚችልባቸው አዲስ መንገዶችን አስበን እንሰራለን እንዲሉ እጠብቅ ነበር” ብለዋል፡፡ የጠበቁትን ከፕሬዝዳንቱ ንግግር አለማግኘታቸውንም ጨምረው ገልጻዋል፡፡  
  
ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች