የፕሬዝዳት ቡሽ የአፍሪቃ ጉብኝትና ዉጤቱ | አፍሪቃ | DW | 22.02.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የፕሬዝዳት ቡሽ የአፍሪቃ ጉብኝትና ዉጤቱ

ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ በቦርሳቸዉ ባይሆን በቃላቸዉ ቡዙ በጣም ብዙ ገንዘብ አጭቀዉ ነዉ-አፍሪቃ የገቡት

ቡሽ

ቡሽ

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ በአምስት የአፍሪቃ ሐገራት ለስድስት ቀናት ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቅቀዉ ወደ ሐገራቸዉ ተመልሰዋል።ቡሽ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ አፍሪቃን ሲጎበኙ ያሁኑ ሁለተኛቸዉ ነዉ።አንድ የአሜሪካ መሪ ባንዴ ብዙ የአፍሪቃ ሐገራትን ለረጅም ጊዜ ሲጎበኝ ደግሞ ቡሽ የመጀመሪያዉ መሆናቸዉ ነዉ።ዩሐንስ ቤክ እንደታዘበዉ የቡሽ ጉብኝት ዉጤት ካንድ ጉዳይ በላይ ብዙም አልታየበትም።ዝርዝሩን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ያ አንድ ጉዳይ ቤክ እንደሚለዉ ገንዘብ ነዉ።ብዙ ገንዘብ።በርግጥም ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ በቦርሳቸዉ ባይሆን በቃላቸዉ ቡዙ በጣም ብዙ ገንዘብ አጭቀዉ ነዉ-አፍሪቃ የገቡትን።ቡሽ ቃል እንደገቡት ሰዉነትን እያቆሰለ-አይንን እስከ ማጥፋት የሚደርሰዉን በሽታ (ሪቨርብላንድነስ)ን ለመግታት ዩናይትድ ስቴትስ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ሰወስት መቶ ሐምሳ ሚሊዮን ዶላር ለአፍሪቃ ትሰጣለች።

የኤች አይ ቪ/ኤድስ ሥርጭትን ለመግታት ደግሞ አሁንም በአምስት አመት ሰላሳ ቢሊዮን ዶላር ትለግሳለች።ሠላሳ ቢሊዮን ዶላር።ብዙ ነዉ።እጅግ በጣም ብዙ።ለብዙ የተሕዋሱ ተጠቂዎች ታላቅ የምሥራች።ግን አሜሪካ ከምትሰጠዉ ገንዘብ አንድ ሰወስተኛዉ (በአምስት አመቱ ሥሌት አስር-ቢሊዮኑ) ከጋብቻ ዉጪ ወሲብን ለማቀብ ለሚደረግ ዘመቻ የሚዉል መሆኑ-ነዉ የምሥራቹን ታላቅነት የሚያሳንሰዉ።

ይሕ በአፍሪቃ አይደለም በየትኛሡም አለም ከተጨባጩ ሐቅ ብዙ የራቀ ነዉ።ከሐቅ የራቀዉን ሐቅ ለማድረግ ያን ያሕል ገንዘብ ከመከስከስ ይልቅ-ቤክ እንደሚለዉ የኮንዶምን ጠቃሚነት ለማስተዋወቂያ ቢዉል ኖሩ ዉጤቱ ብዙ ባማረ ነበር።የወግ አጥባቂዉ የሪፐብሊካን ፓርቲ የሚወክሉት በወግ አጥባቂዎቹ የሚገፉት ቡሽ ግን ሐሳባቸዉ ፍንክች አላሉም።

በልማት ርዳታዉ መስክም፡ ቡሽ ለአፍሪቃ በተለይም መልካም አስተዳደር ለመሠረቱ ሐገራት ዩናይትድ ስቴትስ ጠቀም ያለ ርዳታና ጠንከር ያለ ድጋፍ እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል።ብዙ የአፍሪቃ ሐገራት ምርታቸዉ ዩናይትድ ስቴትስን ገበያ እንዲያገኝ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለገበሬዎችዋ የምትሰጠዉን ድጎማ እንድታቆም ለአመታት እንደጠየቁ_እንደታገሉ ነዉ።የሰማቸዉ የለም።

እያንዳዱ የአሜሪካ ገበሬ ባማካይ በወር አስራ-ሁለት ሺሕ ዶላር ከመንግሥት ይደጎሟል።ይሕ ድጎማ ከሚንቆረቆርላቸዉ ገበሬዎች ጥጥ አምራቹ የአለምን የጥጥ ገበያ በጥጥ በማጥለቅለቁ -ጥጥ እንደ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር ከ1930 ወዲሕ የዘንድዉን ያሕል ረክሶ አያዉቅም።የአፍሪቃን ጥጥ-ማንይንካዉ።ከአራት አመት በፊት በወጣዉ በአለም ንግድ ድርጅት ደንብ መሠረት ለገበሬዎች ድጎማ መስጠት ሕገ-ወጥ ነዉ።

በቀደም የጋናዉ ፕሬዝዳት ጆን ኩፉር ይሕን ጉዳይ እንዲያዉ ፈራ-ተባ እያሉ ለቡሽ አነሱላቸዉ።« የዩናይትድ ስቴትስና የጋና ግንኙነት ብለዉ ቡሽ አጠቃላይ ግንኙነትን እየተነተኑ ኩፉርን በኛ አራዶች ቋንቋ ሸወዷቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ አፍሪቃ ዉስጥ ልትመሠርተዉ ያቀደችዉ የጦር ዕዝ ለአፍሪቃ ብዙ እንደሚጠቅም ቡሽ ብዙ ጊዜ ተናግረዋል።ከላይቤሪያ በስተቀር ጦሩን ለማስተናገድ የፈቀደ አንድ የአፍሪቃ ሐገር ግን የለም።

ላይቤሪያ ደግሞ ጦር ለመስፈሪያነት ሰላሟ ገና አልተፈተነም።ለሁሉም ብዙ ገንዘብ ለማዉጣት ቡሽ ብዙ ቃል ገብተዋል።ገንዝብ ብቻዉን ግን ሁሉንም ችግር አይፈታም።የሚቀጥለዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት አፍሪቃን ሲጎበኝ ካሁኑ የተሻለ ይሆናል-የሚለዉ ተስፋ ግን ጠንካራ ነዉ።ተተኪዉ ፕሬዝዳት ከአብዛኛዉ አፍሪቃ ቀለም-ደም፤ ከኬንያ ዘር- የወረሱት ኦባማ ከሆኑ ደግሞ አፍሪቃ-አሜሪካ የሚሆነዉ እስካሁን ከሆነዉ ሁሉ የተለየ ይሆናል-ነዉ የብዙዎቹ እምነት።