የፕሬዝዳት ቡሽ የአፍሪቃ ጉብኝትና መልዕክታቸዉ | አፍሪቃ | DW | 20.02.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የፕሬዝዳት ቡሽ የአፍሪቃ ጉብኝትና መልዕክታቸዉ

ቡሽ አክራ-ጋና ላይ አፍሪቃ የሚሠፈረዉ የአሜሪካ ጦር የአፍሪቃን ችግር ለማቃለል እንደሚረዳ አስታዉቀዋል።

ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ

ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ በአምስት የአፍሪቃ ሐገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት ዛሬም እንደቀጠሉ ነዉ።እስከ ትናንት ቤኒን፣ ታንዛኒያንና ሩዋንዳን የጎበኙት ቡሽ ዛሬ ጋናን እየጎበኙ ነዉ።ፕሬዝዳት ቡሽ ዛሬ ከጋና ርዕሠ-ከተማ አክራ እንዳስታወቁት ሐገራቸዉ አፍሪቃ ዉስጥ የምትመሰረተዉ ቋሚ ጦር ሠፈር የአፍሪቃ ሐገራት የሚገጥማቸዉን ችግር ለቃለል እንደሚረዳ አስታዉቀዋል።ትናንት ከኪጋሊ እንዳስታወቁት ደግሞ መስተዳድራቸዉ «ዘር-ማጥፋት» የሚለዉን የዳርፉርን ግጭት ለማስወገድ ሐገራቸዉ አበክራ እንደምትጥር ቃል ገብተዋል።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።


«እኩይን-አሉ ቡሽ ትናንት በሩዋንዳዉ ጭፍጨፋ ላለቀዉ ሕዝብ ከቆመዉ መታሰቢያ የአበባ ጉንጉን ሲያኖሩ ትናንት «ሊጋፈጡት ይገባል።»ሩዋንዳ ላይ በመቶ ቀን እድሜ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ቱትሲና ለዘብተኛ ሁቱ ካለቀ ዘንድሮ አስራ-አራተኛ አመቱን ያዘ።ቡሽ ሩዋንዳን የመጎብኘታቸዉ አብይ አለማ ትናንት እሳቸዉ ያሉትን ብቸኛ ልዕለ ሐይል ሐገራቸዉ-የዛሬ አስራ-አራት አመት አለማለት አለማድረጓ ተገቢ እንዳልሆነ ለማሳየት ነዉ።

ይሁንና ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን የዛሬ አስር አመት ትናንት ቡሽ የጎበኙትን ሥፍራ ሲጎበኙ የሚመሯት ሐገራቸዉ አሳዛኙን ጭፍጨፋ ላለማስቆምዋ ይቅርታ መጠየቃቸዉ እዉነት።በዚሕም ሰበብ ሳይሆን አይቀርም የሩዋንዳዋ የአለም አቀፍ ትብብር ሚንስትር ሮዝሜሪ ሙስማኔሊ የቡሽ ጉብኝት ከነበረዉ ይልቅ በሁለቱ ሐገራት ግንኙነት ይልቅ በወደፊቱ በጣሙን በምጣኔ ሐብቱ ትስስር ላይ ላይ ያተኮረ ነዉ።

«USA ገበያችንንም ለማጥናት እየሞከረች ነዉ።ዉጪ የሚወርቱ ባለሐብቶችዋ ሩዋንዳ ሥለሚገኘዉ ሐብት ለማወቅ ለማወቅ እየሞከሩ ነዉ።የሚሰሩበትንም መስክ እያጠኑ ነዉ።ይህን ሁኔታ የሚያመቻች የጋራ ሥምምነት ለማድረግ ደግሞ ሁለታችንም በጋራ እየሠራን ነዉ።ሥምምነቱ ለመወረት አመቺ ድባብን ይፈጥራል።»


የፕሬዝዳት ቡሽ እኩይን እንጋፈጥ መልዕክት ግን ካለፈዉም ከወደፊቱም በላይ አሁን እዚያዉ አፍሪቃ ባለዉ ላይ ያነጣጠረ ነዉ።ምዕራብ ሱዳን።ዳርፉር።የዛሬ አራት አመት ግድም በዳርፉር አማፂያንና በሱዳን ማዕከላዊ መንግሥት መካካል በተጀመረዉ ዉጊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ሁለት መቶ ሺሕ ሕዝብ ተገድሏል።ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አንድም ተሰድዷል።አለያም ተፈናቅሏል።የጦርነቱ ዉጤት ለፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር «ዘር ማጥፋት» ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስና የተቀረዉ አለም የሩዋንዳዉን ጭፍጨፋ ማስቆም እንዳልቻለ ሁሉ የዳርፉሩንም ግጭት፤ጦርነት ይሁን ቡሽ እንዳሉት ዘርማጥፋቱን ለማስቆም ከማለት በላይ ቢያንስ እስካሁን አልቻለም።ትናንት ግን ወስኛለሁ አሉ ቡሽ።አለም አቀፉ ማሕበረሰብ የዳርፉርን ሠላም ለማስከበር የሚያደርገዉን ጥረት እንረዳል።ርዳታዉ ቡሽ እንዳሉት ማዕቀብ መጣል-አንድ።ሠላም ለማስከበር ለሚዘምተዉ ሠራዊት ወጪ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር መስጠት-ሁለት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግን የዳርፉርን ሠላም ለማስከበር ሊያዘምተዉ ላቀደዉ ሠራዊት ሃያ ሔሊኮብተሮች የሚሰጠዉ አጥቶ እስካሁን የደረሱለት ኢትዮጵያና ባንግላዴሽ ብቻ ናቸዉ።የቡሽ ቃል ለተጨባጩ ችግር መፍትሔ ይሆን-ይሆን።

ለሩዋንዳዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሻርልስ ሙሪጋንዳ ግን ቡሽ ሥለ ሩዋንዳ እንጂ ሥለዳርፉር ወይም ሥለመለዉ አፍሪቃ ያሉ-ያደረጉት ብዙም ከቁብ የሚገባ አይደለም።

«ይሕ (ጉብኝቱ) በሁለቱ ሐገሮቻችን መካካል እጅግ በጣም ጥሩ ግንኙነት ለመኖሩ ማረጋገጪያ ነዉ።የእሳቸዉ ጉብኝት እነዚሕን ግንኙነቶች ይበልጥ እንደሚያጠናክር ምንም አያጠራጥርም።»

ታንዛኒያ ላይ ጤናን ለማስፋፋት፣ ሩዋንዳ ላይ ዘር ማጥፋትን ለመዋጋት አፍሪቃዉያን የሚያደርጉትን ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ እንደምትደግፍ ቃል የገቡት ቡሽ አክራ-ጋና ላይ አፍሪቃ የሚሠፈረዉ የአሜሪካ ጦር የአፍሪቃን ችግር ለማቃለል እንደሚረዳ አስታዉቀዋል።