የፕሬዝደንት ትራምፕ ዉሳኔ | ዓለም | DW | 02.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የፕሬዝደንት ትራምፕ ዉሳኔ

ዩናይትድ ስቱትስ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ጉዳይ ስምምነት እንደምትወጣ ማሳወቋ በሌላዉ ዓለም ዘንድ ሁለት ዓይነት ስሜት ፈጥሯል። በአንድ ወገን የአብዛኞቹ ሃገራት መሪዎች የዋሽንግተን ቃሏን ማጠፍ የአየር ንብረት ለዉጥን ይቀለብሳል በሚል የተሰማሙበትን ዉሳኔ ተግባራዊ ከማድረግ እንደማያግዳቸዉ እየዛቱ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:54

የፕሬዝደንት ትራምፕ ዉሳኔ

ሩሲያ በበኩሏ የተባለዉ ሁሉ አሜሪካን ከሌለችበት ዉጤታማ አይሆንም እያለች ነዉ። ሞስኮ ስምምነቱን ብትፈርምም እስካሁን ያላጸደቀች ሀገር ናት። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ደግሞ የዋሽንግተንን ርምጃ አሳዛኝ ብለዉታል።

«ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ጉዳይ ስምምነት መዉጣት በጣም የሚያሳዝን ነዉ፤ እጅግ የተመጠነ ቋንቋ መምረጤ ነዉ። የፓሪሱ ስምምነት ለዓለም አቀፉ ትብብር አንድ የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነ ይቀጥላል። ስምምነቱም በ2030 አጀንዳ ማለትም ዘላቂ እድገት ላይ ለመድረስ አስፈላጊ ነዉ። ለዚህም ነዉ የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ትናንት ምሽት ይህን ይፋ ካደረገ በኋላ ትኩረታችንን የወደፊቱ ላይ ማድረጋችን አስፈላጊ ነዉ የምንለዉም ለዚህ ነዉ። ይህ ዉሳኔ ምድራችንን ለመከላከል ኃላፊነት የሚሰማንን ሁሉ ያሰብነዉን ከማድረግ ሊያግደን አይገባም።»

የቻይና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም እንዲሁ ኃላፊነት እንዳለበት ሀገር ቻይና በስምምነቱ ዉል እንደምትፀና አመልክተዋል። ከምርጫ ቅስቀሳቸዉ ጀምረዉ አሜሪካንን ዳግም ታላቅ ሀገር አደርጋለሁ የሚሉት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ግን ፓሪስ ላይ የተፈረመዉ የአየር ንብረት ጉዳይ ዉል ሀገራቸዉን ገንዘብ ለማስወጣት የታለመ ነዉ በማለት ዉሳኔያቸዉን ትናንት እንዲህ አሳዉቀዋል።

«ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ጉዳይ ስምምነት ትወጣለች። ይህ ስምምነት ስለአየር ንብረት የሚለዉ አነስተኛ ሆኖ የሚበዛዉ ሌሎች ሃገራት ከዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ጥቅም እንዲያገኙ ነዉ። ሌሎች ሃገራትና መሪዎች ከእንግዲህ በእኛ ላይ እንዲስቁ አንፈልግም። እናም አይሆንም። የተመረጥኩት የፒትስበርግን ዜጎች ልወክል እንጂ የፓሪስን አይደለም።»

እንዲያም ሆኖ የአየር ንብረት ለዉጥን በተመለከተ በሃገራት መካከል የሚካሄደዉ የዉይይት መድረክ  ቃል አቀባይ ጆነተን ላይን፤ በዚህ ደረጃ አሁን ዋሽንግተን እንዴት ከፓሪሱ ስምምነት ልትወጣ እንደምትችል ግልፅ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

 

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሐገራቸዉ የአየር ንብረት ብክለትን ለመቀነሰ ካለመዉ ዓለም አቀፍ ስምምነት እንድትወጣ መወሰናቸዉን የመላዉ ዓለም መሪዎች፤የማሕበራት ተጠሪዎችና የተፈጥሮ ሐብት ተሟጋቾች ሲተቹት ነዉ የዋሉት። ፕሬዝደንት ትራምፕ የፓሪስ የዓየር ንብረት ሥምምነት ከሚባለዉ ዉል ሐገራቸዉ እንድትወጣ የወሰኑት ስምምነቱ «የምወደዉ» ያሉትን የአሜሪካን ግብር ከፋይ ሕዝብ ሥለሚጎዳ ነዉ ባይ ናቸዉ። የትራምፕ ዉሳኔ ዩናይትድ ስቴትስን ከመላዉ ዓለም ነጥሎ በጦርነት ከምትወድመዉ ሶሪያና ከትንሺቱ ደቡብ አሜሪካዊት ሐገር ኒካራጓ ጋር የሚመድብ ነዉ።

መክብብ ሸዋ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic