የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኬንያ ጉብኝት | አፍሪቃ | DW | 24.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኬንያ ጉብኝት

ዛሬ ማምሻውን ኬንያ ይገባሉ ተብለው ለሚጠበቁት ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አቀባበል ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ በመደረግ ላይ መሆኑን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት AFP አስታወቀ።

እጅግ ብዙ ፀጥታ አስከባሪዎች በዋና ከተማይቱ ናይሮቢ ለጥበቃ ተሰማርተዋል ። አንዳንድ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ አውሮፕላኖችም ከተማዋን ከአየር ሲቃኙ መታየታቸው ተዘግቧል ። ከዚህም በተጨማሪ የናይሮቢ ጎዳናዎች እና የአየር ማረፊያው ለጊዜው እንደሚዘጉ ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንት ኦባማ በኬንያ ቆይታቸው ሁለቱ ሀገራት በጋራ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች በሚጠናክሩበት መንገድ ላይ ይመክራሉ ።

ኦባማ ወደ ኬንያ ከመጓዛቸው በፊት ለBBC የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ይህ የጉብኝታቸው አንዱ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል ። «በመጀመሪያ ደረጃ ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የአሸባሪ ድርጅቶችን በተመለከተ ከተቀሩት ሀገራት ጋር አብሮ መስራት እንደሚፈልግ ቁርጠኝነቱን ማረጋገጡ አስፈላጊ ይመስለኛል። በመቀጠል ሽብርተኝነትን በተመለከተ በዩናይትድ ስቴትስ እና በኬንያ እንዲሁም በዩጋንዳ እና ሌሎች የምስራቅ አፍሪቃ ሀገሮች መካከል በጣም ጠንካራ ትብብር አለ። እና የጉዞው አንዱ አካል የዚህን ኃላፊነት የበለጠ ጠንካራ የማድረግ ነው።» ወደ አባታቸው ሀገር የተጓዙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከዛሬ እስከ እሁድ ኬንያን ከጎበኙ በኋላ ፤ እሁድ ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ማክሰኞ ያጠናቅቃሉ።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ