የፕሬዚደንት ኦማባ የአፍሪቃ ጉብኝት እና ዓላማው | አፍሪቃ | DW | 25.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የፕሬዚደንት ኦማባ የአፍሪቃ ጉብኝት እና ዓላማው

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ከትናንት ጀምረው ኬንያን በመጎብኘት ላይ ሲሆኑ፣ በነገው ዕለት ደግሞ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ። የፕሬዚደንቱ የኬንያ እና የኢትዮጵያ ጉዞ በተለይ በሽብርተኝነት አንፃር በሚካሄደው ትግል ላይ ያተኮረ መሆኑን ተንታኞች አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዩኤስ አሜሪካ በአፍሪቃ ከሚታየው ግዙፍ የኤኮኖሚ እድገት ተጠቃሚ ልትሆን የምትችልበት ጉዳይ ሌላው በጉብኝታቸው የሚነሳ ዓቢይ ርዕስ ነው። ይሁንና፣ ከቻይና ትልቅ ፉክክር ተደቅኖዋል።

ይኸው የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ጉዞ ምናልባት ዩኤስ አሜሪካ ለፓሲፊክ አካባቢ የሰጠችውን ልዩ ትኩረት አሁን ወደ አፍሪቃ ማዞርዋ ይሆን በሚል የሚያጠያይቁ አልጠፉም። ፕሬዚደንት ኦባማ ወደ ኬንያ እና ወደ ኢትዮጵያ ከመነሳታቸው ከጥቂት ቀናት በፊት፣ ባለፈው ሰኞ የናይጀሪያውን አቻቸው መሀማዱ ቡሀሪን በዋይት ሀውስ ቤተ መንግሥት ተቀብለው ማነጋገራቸው ይታወሳል። ይሁንና፣ በዋሽንግተን የሚገኘው የሥልታዊ እና ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ሪቻርድ ዳውኒ እንደሚሉት፣ ዩኤስ አሜሪካ ለአፍሪቃ የሰጠችው ትኩረት ያን ይህል ለውጥ አልታየበትም።

USA Muhammadu Buhari und Barack Obama in Washington

ኦባማ ከናይጀሪያ አቻቸው መሀማዱ ቡሀሪ ጋር በዋይት ሀውስ

« ምንም እንኳን አፍሪቃ ለዩኤስ አሜሪካ የያዘችው ሥልታዊ ትርጓሜ በወቅቱ ከፍ እያለ ቢመጣም፣ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር ዩኤስ አሜሪካ ሀብቷን የምታፈስበት እና ትኩረት የምታሳርፍበት ሂደት አፍሪቃ ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። »

ለዋሽንግተን በአፍሪቃ ካሉ ናይጀሪያን እና ኬንያን ከመሳሰሉ ጠንካራ መንግሥታት ጋር ሥልታዊውን አጋርነት ማሳደግ ትልቅ ትርጓሜ አለው። ዩኤስ አሜሪካ ፈጣን እድገት እና ብልፅግና እያሳየ በምትገኘው አፍሪቃ ውስጥ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ከምታደርገው ጥረት ጎን፣ በሽብርተኝነት አንፃር ለምታካሂደው ትግሏ የሚተባበሩዋት ተጓዳኞች ማግኘቱ ላይ ነው ትኩረቷን ያሳረፈችው። የቅርብ እና የመካከለኛውን ምሥራቅ ያሰጋው ዓይነቱ የሽብርተኝነት ተግባር ወደ አፍሪቃም ሊስፋፋ የሚችልበት ስጋት አሜሪካውያኑን አብዝቶ አሳስቦዋል። ይሁንና፣ ይህ አፍሪቃ ውስጥ ገሀድ ሆኖዋል። በናይጀሪያ የሚንቀሳቀሰው እና በሀገሩ እና ባካባቢ ሀገራት የሽብር ጥቃት የሚያካሂደው የፅንፈኞቹ ሙሥሊሞች ቡድን ቦኮ ሀራም ራሱን «እሥላማዊ መንግሥት» ብሎ ከሚጠራው አሸባሪ ቡድን ጋር ጉድኝት መፍጠሩን አስታውቋል፣ ይህም ለናይጀሪያ እና ለአዲሱ ፕሬዚደንትዋ መሀመዱ ቡሀሪ ትልቅ ችግር ደቅኖዋል። ኬንያም ምንም እንኳን በንግዱ ግንኙነት ላይ ወሳኛ ሚና ብትይዝም፣ አሳሳቢ የፀጥታ ችግር እንዳለባት ነው ሪቻርድ ዳውኒ የሚያመለክቱት።

Kenia ermordete Studenten Trauerfeier und Begräbnis

ጋሪሳ

« ኬንያ ዋነኛ የንግድ አጋር ናት። ብዙ ያሜሪካ ኩባንያዎች ኬንያ ውስጥ ይገኛሉ። ባካባቢ ፀጥታ እና ባካባቢ የተነሱ ውዝግቦችን በመሸምገሉ ረገድ ኬንያ ዋነኛ ሚና ትጫወታለች። ያም ሆኖ ግን የሀገርዋ የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ነው። ኬንያ ባንድ በኩል በጎረቤት ሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው ያማፅያኑ ቡድን አሸባብ በሚጥላቸው ፣ በሌላ በኩል በራሷ በሀገሯ ውስጥ በሚሰነዘሩ የሽብር ተግባራት ችግር ተደቅኖባታል። የኬንያ መንግሥት በነዚህ ጥቃቶች አንፃር የወሰደው ርምጃ ግን ሁኔታውን በማሻሻል ፈንታ ይበልጡን እንዲበላሽ አድርጓል። »

በተለይ በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ከተካሄደው እና ወደ 150 ሰዎች ሕይወት ካጠፋው ጥቃት በኋላ የኬንያ ፀጥታ ኃይላት በፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ትዕዛዝ በሶማልያ ዜጎች እና የሶማልያ ዝርያ ባላቸው ኬንያውያን ላይ በማነጣጠር የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀማቸውን ዳውኒ አጥብቀው ወቅሰዋል።

በኬንያ እና በኢትዮጵያ ሥርዓት ዴሞክራሲ ይስፋፋ እና የሰብዓዊ መብት ይከበር ዘንድ ፕሬዚደንት ኦባማ ግፊት እንዲያደርጉ የመብት ተሟጋቾች እያሳሰቡ ነው። «ፎርን ፖሊሲ ጀርናል» የተባለው ያሜሪካውያን የድረ ገፅ መጽሔት ከፕሬዚደንት ኦባማ የአፍሪቃ ጉዞ ቀደም ሲል ባወጣው ዘገባ፣ ዩኤስ አሜሪካ አምባገነን መንግሥታትን የመደገፍ የቆየ ልምድ እንዳላት ጽፏል። ኦባማ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል በነበሩበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን አሰራር እንደሚያስቆሙ ነበር ማናገራቸውን ሪቻርድ ዳውኒ ያስታውሳሉ።

« ፕሬዚደንት ኦባማ እና ዩኤስ አሜሪካ፣ ዴሞክራሲን እና መልካም አስተዳደርን የመደገፍ ፅኑ ፍላጎት አላቸው። እንደሚታወሰው፣ ኦባማ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ጋናን በጎበኙበት ጊዜ ባሰሙት ንግግራቸው ጠንካራ መሪዎችን ሳይሆን ጠንካራ መንግሥታትን ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸው ነበር። »

ይሁንና፣ ይላሉ ዳውኒ፣ የኢትዮጵያን እና የዩኤስን ግንኙነት ሲመለከቱት፣ ዩኤስ አሜሪካ በዚችው ሀገር የራሷን ጥቅም ከማስጠበቁ ድርጊት ጋር የሚጋጭ ሁኔታ ሲያጋጥማት ያስቀመጠችውን መመሪያ ማስከበሩ አዳጋች ይሆንባታል።

Dr Peter Pham

ፒተር ፓን

« ኢትዮጵያ ባለፈው ግንቦት ባካሄደችው ምርጫ ገዢው ፓርቲ እና አጋር ድርጅቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 100% ማግኘታቸው ይታወቃል፣ ይህ ግን ዩኤስ አሜሪካ በአፍሪቃ ልትደግፈው የምትፈልገው ዓይነት ዴሞክራሲ አይደለም። »

አሜሪካዊው ፕሬዚደንት በተለይ ወደ ኢትዮጵያ ምርጫውን ተከትሎ ባሁኑ ጊዜ መጓዛቸውን የመብት ተሟጋቾቹ አጥብቀው ተችተዋል። ይሁንና፣ «አትላንቲክ ካውንስል» የተባለው በዋሽንግተን የሚገኘው ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተመልካች ተቋም ባልደረባ ፒተር ፓም እነዚህ የመብት ተሟጋቾች የሰነዘሩትን ወቀሳ እንዲህ ሲሉ አጣጥለውታል።

« የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዓላማ እንከን የሌላቸውን ወይም በተሳካ የልማት ደረጃ ላይ የሚገኙትን ሀገራት ማሞገስ ወይም ማድነቅ ሳይሆን፣ በውይይት መሻሻልን ማስገኘት ነው። ኦባማ ወደ ኢትትዮጵያ መሄዳቸውን በተመለከተ ግን ቀደም ሲል የተሰነዘረውን ወቀሳ፣ ሁሉንም በአንድ መለኪያ የማይመዝን አስተያየት ነው በሚል በፍፁም አልቀበለውም። ለምሳሌ፣ ፕሬዚደንቱ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ያላትን እና ዴሞክራሲያዊት ሀገር ያልሆነችውን ቻይናን ቢጎበኙ፣ እነዚህ ሰዎች ተመሳሳይ ትችት አይሰነዝሩም ነበር ፣ በሁለተኛ ደረጃ ፣ የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ጉብኝት ዋነኛ ዓላማ የዩኤስ አሜሪካን ጥቅም ማስጠበቅ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ዩኤስ አሜሪካ ደግሞ የፀጥታ ጥበቃ፣ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ጥቅሞችዋን በማስጠበቁ ረገድ ከኢትዮጵያ ጋር አብራ መስራቱን ትፈልገዋለች።»

አፍሪቃ እያስመዘገበችው ባለው ግዙፍ የኤኮኖሚ እድገት የተነሳ ገፅታዋ በዓለም እየተቀየረ በመሆኑ ለዩኤስ አሜሪካ የንግድ ተቋማት ጥሩ አጋጣሚ እንደከፈተች ነው ፒተር ፓም የሚስረዱት። ይሁንና፣ ይላሉ ፓም፣ አሜሪካውያኑ ባለተቋማት አፍሪቃ ውስጥ ወረታቸውን ሊያሰሩ በሚፈልጉባቸው ዘርፎች ሁሉ ቻይናውያኑ ቀድመዋቸው መስራት በመጀመራቸው ፉክክሩ ቀላይ አይደለም። ቻይናውያን ከአፍሪቃ ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት በዩኤስ እና በአፍሪቃ መካከል ያለውን በእጥፍ በልጦ በያመቱ 200 ቢልዮን ዶላር ወረት በአህጉሩ ያሰራሉ።

ጌሮ ሽሊስ/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic