የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነትን በተመለከተ የሕዝብ አስተያየት ከትግራይ ክልል
ዓርብ፣ ጥቅምት 22 2017የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት ነገ ጥቅምት 23 ቀን 2017 ሁለተኛ ዓመቱን ይደፍናል። አቶ ሬድዋን ሑሴን የፌድራል መንግሥቱን አቶ ጌታቸው ረዳ ህወሓትን ወክለው በደቡብ አፍሪካ የተፈራረሙት ሥምምነት ደም አፋሳሹን ግጭት ቢገታም በውሉ የተዘረዘሩ ጉዳዮች በሙሉ እንደታቀደው ተግባራዊ አልሆኑም።
የሥምምነቱን ሁለተኛ ዓመት በማስመልከት ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ያነጋገራቸው የትግራይ አቶ በሪሁ ተክሉ “ሰላም መኖሩ አንድ ትልቅ ነገር ነው። የመድፍ ድምጽ የለም። ሞትም ቢሆን በተወሰነ መልኩ ቀንሷል” ሲሉ የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት አዎንታዊ ለውጥ እንዳስከተለ ተናግረዋል።
በህወሓት አመራሮች ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት የፕሪቶሪያን ሥምምነት “ባለቤት አልባ” ሊያደርግ እንደሚችል ጌታቸው ረዳ ተናገሩ
ይሁንና አቶ ሬድዋን ሑሴን የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥትን እንዲሁም አቶ ጌታቸው ረዳ ሕወሓትን በመወከል የፈረሙት ሥምምነት “እየተፈጸመ አይደለም” የሚል አቋም አላቸው።
በተፈናቃዮች መጠለያ የሚገኘው ደስታ ገብሩ ግጭት የማቆም ሥምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ “ውጊያ ቆሟል፤ ወጣቱን ከሞት እና ጉዳት ታድጓል” ይበል እንጂ እንደ አቶ በሪሁ ሁሉ በአፈጻጸሙ ረገድ ቅሬታ አለው።
“ወጣቱ ተስፋ አጥቷል፤ ወደ ቀየው አልተመለሰም። ይኸ መዓት ችግር እና ጭንቀት እየፈጠረበት ነው። ወደ ሱስ እየገባ ነው” የሚለው ደስታ “ቶሎ ወደ ቀየው መመለስ አለበት” በማለት ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።
“የጥይት ድምጽ አለመስማት አንድ ትልቅ ነገር ነው” የሚሉት መምህርት ንግሥቲ ጋረድ በበኩላቸው በፕሪቶሪያ የተፈረመው ሥምምነት ያመጣቸው “ጸጋዎች” መኖራቸውን ቢናገሩም ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ።
"ድምጽ የሌለው ሞት እየሞትን ነው" ከባድመ የተፈናቀሉ የልጆች እናት
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነትን ሲፈራረሙ “ትግራይ ወደነበረችበት ትመለሳለች የሚል ዕምነት ነበረን። ምክንያቱም ብዙ ችግሮች አጋጥመዋል” የሚሉት መምህርት ንግሥቲ “አሁን ያለውን ሁኔታ ከነበረው ጋር ስናነጻጽረው ሰላም ከማግኘታችን ውጪ ምንም ያገኘንው ጥቅም እንደሌለ ሁላችንም ይገባናል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
“በውሉ ላይ የተፈራረሟቸው ነገሮች ተግባራዊ ባለመሆናቸው ሕብረተሰቡም አስተማሪውም ችግር ላይ ወድቋል” ብለዋል።
ዓመት ስለደፈነው የፕሪቶሪያው ስምምነት የፖለቲከኞች አስተያየት
ከማይካድራ በጥቅምት 2013 መፈናቀላቸውን የገለጹ ሌላ አስተያየት ሰጪ ወደ ቀያቸው መመለስ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት “እንደዚህ አይነት ሁኔታ እንዳይከሰት” ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
“የተፈናቀለው ወጣት ተስፋ እያጣ ወደ ሌላ ስደት እየገባ ነው። ባሕር ላይ እየቀረ ነው” የሚሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ “በተለይም ወጣቱን ከመጥፎ ነገሮች ለማዳን ቶሎ ወደ ቀያችን እንዲመልሱን እና ሠርተንም ይሁን ተምረን ሕይወታችንን የምንቀይርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።
ሚሊዮን ኃይሥስላሴ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር