የፕረስ ነፃነት በናይሮቢ | አፍሪቃ | DW | 03.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የፕረስ ነፃነት በናይሮቢ

እኤአ ግንቦት 3፣ 2018 የዐለም ፕሬስ ነጻነት ቀን በኬንያ ናይሮቢ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቢሮ ታስቧል፡፡ በዝግጅቱም በምስራቅ አፍሪካ እና ታላላቅ ሐይቆች ሀገሮች ካሳለፍነው የፈረንጆች ዐመት ጀምሮ እስከያዝነው 2018 ያሉት ጥቂት ወራት ድረስ የፕሬስ ነጻነት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ፓናል ውይይትም ተካሂዷል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:06

የፕረስ ነፃነት እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል

በምስራቅ አፍሪካ እና ታላላቅ ሐይቆች ሀገሮች የፕሬስ ነጻነት ያለበትን ደረጃ አስመልክተው ሪፖርት ያቀረቡት “አርቲክል 19” የተሰኘው የሃሳብ ነጻነት ተሟጋች ድርጅት ዳይሬክተር ሚስተር ጆን ኒያንዩኪ ናቸው፡፡ ዳይሬክተሩ በሪፖርቱ እንዳሉት ካለፈው የፈረንጆች ዐመት ጀምሮ በቀጠናው የፕሬስ ነጻነት በተለይም ደሞ ጋዜጠኞች ከምንጊዜውም በላይ አደጋ እንደተደቀነባቸው ገልጸዋል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለው በቀጠናው ካለፈው የፈረንጆች ዐመት ወዲህ ከሱማሊያ ቀጥሎ ኤርትራ እና ኢትዮጰያ በቅደም ተከተል የከፋ የፕሬስ ነጻነት እና ጋዜጠኞች መብት ረገጣ የታየባቸው ሀገሮች ሆነዋል፡፡

 

ጋዜጠኞች ከተጋረጡባቸው እክሎች መካከልም አካላዊ ጥቃት፣ እስር፣ የግድያ ዛቻ፣ በፍርድ ቤት እየተጠሩ መጉላላት፣ መረጃ መከልከል፣ አስገድዶ ማፈን፣ የሜዲያ ተቋማት መዘጋት የመሳሰሉት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው በሪፖርቱ ተወስቷል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስታት እና መንግስታዊ ያሆኑ አካላት በጋዜጠኞች ላይ ብቻ ሳይሆን በጦማሪዎች ላይ ጭምር ከባድ አደጋ መደቀናቸውን ነው ሪፖርቱ የጠቀሰው፡፡ በቅርቡ በኡጋናዳ እንደታየው አንዳንድ የቀጠናው መንግስታት በማህበራዊ ሜዲያ ላይ ከባድ እመቃ መጀመራቸውም አዲሱ አሳሳቢ ክስተት እየሆነ መጥቷል- ይላል የአርቲክል 19 ዐመታዊ ሪፖርት፡፡

ጋዜጠኛ እስክንድር የፓናል ውይይቱ አንዱ መወያያ ሃሳብ አቅራቢ ሆኖ ሜዲያ በጠቅላላው ምን ዐይነት እክሎች እንደሚገጥሙት አጠር ያለ ሃሳቡን አጋርቷል፡፡ ከተሰብሳቢዎችም በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውለት መልስ ሰጥቷል፡

፡ በምስራቅ አፍሪካ ከሌሎች የአህጉሪቱ ቀጠናዎች በተለየ ፕሬስ ነጻነት ወደኋላ የቀረው በዋናነት በፖለቲካ ልሂቃኑ የፖለቲካ ፍላጎት ማጣት መሆኑን የጠቀሰው እስክንድር “ለፕሬስ ነጻነት በተናጥል የሚደረግ ትግል የትም አይደርስም፤ ለዴሞክራሲ ሁለገብ ትግል መደረግ አለበት” በማለት ነው አጽንዖት ሰጥቶ ነው ያብራራው፡፡

ለአርቲክል 19 ዳይሬክተር  ሚስተር ጆን ስለ ኢትዮጵያ ፕሬስ ነጻነት በተናጥል ላቀረብንላቸው ጥያቄ እንዲህ ሲሊ መልሰዋል፤

የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ያለበትን ሁኔታ እንዲነግሩን የሜዲያው ያለበት ሁኔታ አሳዛኝ ነው፡፡ መንግስት ጋዜጠኞችን ጦማሪዎችን መብት እንዲጠበቅና የሕዝቡን መረጃ የማግኘትና ሃሳብ ነጻነት መብት እንዲያከብር እንጠይቃን፡፡ ባለፉት ዐመታት እንዳየነው የፕሬስ ነጻነት እና ብዙ ጋዜጠኖች እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከመንግስት አደጋ ተጋርጦባቸው ነው የቆዩት፡፡ አዲሱ አመራር አወንታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ግን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ድርጅታቸው አርቲክል 19 ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አሁን ስላለው ግንኙነትም በግል ጠይቄያቸው ሲመልሱ፤

በአዲሱ አመራር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለን ግንኙነት እንደሚሻሻል ተስፋ አለን፡፡ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባለፉት ዐመታት በጣም አስቸጋሪ ግንኙነት ነው የነበረን፡፡ አሁን በታየው የአመራር ለውጥ ግን በሀገሪቱ የሃሳብ ነጻነት፣ የሜዲያ ነጻነትን እና በጠቅላላው ሰብዓዊ መብትን በማስፋት ረገድ አወንታዊ ሚና እንድንጫወት እንደሚፈቀድልን ተስፋ አናደርጋለን፡፡

በስብሰባው መጨረሻ ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር በነበረኝ የተናጥል ቆይታ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን ለማስከበር ከአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ በአስቸኳይ ምን ርምጃዎችን እንደሚጠብቅ ጠይቄዋለሁ። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ዛሬ ምሽት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ይበራል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እስክንድር የህሊና እስረኛ መሆኑን አውቆ ከአስር እንዲፈታ ለዐመታት ዘመቻዎች ሲያደርግለት የቆየ ስለሆነ ነው በናይሮቢው የዐለም ፕሬስ ነጻነት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኝ የጋበዘው፡፡

ቻላቸው ታደሠ

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic