የፓን አፍሪቃ ፊስቲቫልና ዋጋዱጉ | ባህል | DW | 09.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የፓን አፍሪቃ ፊስቲቫልና ዋጋዱጉ

«ጉዞዉ የተደረገዉ ከጀርመን ቦን ከተማ በባቡር ወደ ፍራንክፈርት ከፍራንክፈርት ወደ ካዛብላንካ ሞሮኮ ነበር ያረፍኩት ከዝያ ዋጋዱጉ ቡርኪናፋሶ የሄድኩት፤ ግን ካዛብላንካ ላይ የነበረን ቆይታ ጥሩ አልነበረም። በተረፈ ግን የዋጋዱጉ የፊስፓኮ ዉሎዉ ቆይታዉ የማይታሰብ ጊዜ ነበር።»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:15

የፓን አፍሪቃ ፊስቲቫልና ዋጋዱጉ

አፍሪቃዉያን የፊልም አዋቂዎች ፊልሞቻቸዉን በየሁለት ዓመቱ ወደሚያቀርቡበት ወደ መዲና ዋጋዱጉ በአጫጭር ፊልሞች ዘርፍ የተጓዘዉ ጋዜጠኛ ማንተጋፍቶት ስለሺ ነበር። ማንተጋፍቶት ወደ ዋጋዱጉ ለመድረስ የመተላለፍያ በረራዉን ያደረገባት የምዕራብ የሞሮኮዋ ከተማ ካዛብላንካ  ወደ ዋጋዱጉ የሚጓዙ የፊስፓኮ ታዳሚዎችና የፊልም ሰራተኞች በቅጡ እንዳላስተናገደች ነዉ የገለፀልን። የሞሮኮ የንግድ ከተማ የሆነችዉ ካዛ ብላንካ ንግዱን እንጂ የአዉሮፕላን የበረራ መስመር ቅንጅትን አላጤነችበም ተብላ ተተችታለች። እንድያም ሆኖ ካዛ ብላንካ ላይ የተንገላቱት አፍሪቃዉያኑ የፊልም ስራ አዋቂዎች እና የፊስፓኮ እድምተኞች ምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ሃገር መዲና ዋጋዱጉ ላይ ሲደርሱ የጠበቃቸዉ ደማቅ አቀባበል፤ ደማቅ መስተንግዶ፤ ደማቅ የፊልም ዉድድር፤ ነበር። በዚህ ዝግጅታችን የዘንድሮዉን የፓን አፍሪቃ ፊልም ፊስቲቫል እና በዚሁ የአፍሪቃ የፊልም ዉድድር መድረክ ላይ በአጭር ፊልሞች ዘርፍ የተሳተፈዉ ጋዜጠኛ ማንተጋፍቶት ስለሺ የቡርኪና ፋሶ ምልከታን ያስቃኘናል፤

 

የአትላንቲክ ዉቅንያኖስን የምትዋሰነዉ የምዕራብ ሞሮኮዋ ካዛብላንካ ከተማ ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራትና ከዓለም ሃገራት በቡርኪና ፋሶዉ የአፍሪቃዉያኑ የፊልም መድረክ ላይ ለመገኘት አዉሮፕላን ጉዞ ለጀመሩ የአዉሮፕላን መቀየርያ መሸጋገርያ ከተማ ነበረች። ለአስር ቀናት በሚዘልቀዉና በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደዉ በዚህ የፓን አፍሪቃ ፊልም መድረክ ላይ ፊልሞቻቸዉን ለማቅረብ ለማቅረብ ብሎም ከመክፈቻዉ ሥነ-ስርዓት ጀምሮ ለመገኘት ያለሙት በርካታ ታዳሚዎችና የፊልም ሥራ አዋቂዎች ካዛ ብላንካ አዉሮፕላን ጣብያ አጣብቂኝ ገብተዉ የመክፈቻዉን ሥነ- ስርዓት መታደም አልቻሉም። 

ከሴኔጋል እስከ ናይጀርያዋ የወደብ ከተማ ሌጎስን ሁሉ አካቶ የሚያሳየዉ ፍሮንቲስ የተሰኘዉ ፊልም አራት ከተለያዩ ሃገራት የመጡና ሳያዉቁት የተገናኙ ሴቶች ከባድ በሆነዉ ጉዞ ምን ያህል አንድነት እንደፈጠሩ ይተርካል። ከነዚህ ሴቶች መካከል ከኮት ዲቯር የመጣችዉ ኤማ ትገኝበታለች። በፊልሙ ላይ ናኪ ሴ ሳቫኔ የሚል መጠርያን የያዘችዉ ኤማ ፍሮንቲስ የተሰኘዉ ፊልም ሴቶች ዋናዉን ገፀ-ባሕሪ ይዘዉ በመጫወታቸዉ ኩራት እንደሚሰማት ትናገራለች።  

«በሴቶች የተሰራ ፊልም ለመጀመርያ ጊዜ የፊስቲቫሉ የመጀመርያ መሆኑን በማየቴ ክብር ይሰማኛል።  ይህ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነዉ ለማይታዩት ለበርካታ ሴት የአፍሪቃ የፊልም ሥራ አዋቂዎች ትልቅ እዉቅና ነዉ። ፊስፓኮ ይህን ተረድቶ እንዲህ አይነት ርምጃን በማድረጉ እናመሰግናለን። በአፍሪቃ የሚገኙ የፊልም ሰራተኞችም በጣም ከባድና ጥሩ ፊልሞችንም  ይሰራሉ።»

በርግጥ በሴቶች በተሰራ ፊልም የዘንድሮዉ የአፍሪቃዉያኑ የፊልም ፊስቲቫል ተጀመረ እንጂ በአስሩ ቀን ፊልም እይታ ወቅት ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት በመጡ የፊልም ሥራ አዋቂዎች የተሰሩ ሁለት መቶ ፊልሞች በተለያዩ ፊልም ቤቶች ቀርበዋል። በዋጋዱጉ የፓን አፍሪቃ ፊልም ፊስቲቫል ላይ የተገኘዉ ማንተጋፍቶት ስለሺ እንደሚለዉ ፊልሞቹ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ፊልም ቤቶች ነዉ የታየዉ። 

በቡርኪና ፋሶ ዋና መዲና ላይ በየሁለት ዓመቱ የሚዘጋጀዉ የፊስፓኮ ማለት የፓን አፍሪቃ ፊልም ፊስቲቫል እንደ ጎርጎረሳዉያኑ 1969 ዓ,ም የተጀመረ ሲሆን አፍሪቃዉያን የፊልም ባለሞያዎችን ለማበረታታት የአፍሪቃን ባህል ለዓለም ለማስተዋወቅ አፍሪቃዉያንም የፊልም ሰራተኞችም እርስ በርስ ለማማር ሃሳብ ለመለዋወጥ በሚል ዋና አላማን ይዞ ነዉ።   ለቡርኪና ነዋሪዎች በተለይ ደግሞ ለዋጋዱጉ ነዋሪዎች ፊስፓኮ በጉጉት የሚጠበቅ ነዉ ያለን ማንተጋፍቶት የፊልም ፊስቲቫሉ ዋና ማዕከል የሚደነቅ ነዉ።

በዚህ ፊልም ሥነ-ስርዓት ላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት በኩል ደንብ ልብሳቸዉን እንደለበሱ ፊልም ለማየት መምጣታቸዉንና ስለፊልሙ ቃለ ምልልስ እንደነበር ማንተጋፍቶት ተናግሮአል። በዋጋዱጉ ኤንባሲ የሚሰሩ አልያም ኢትዮጵያ አየርመንገድ የሚሰሩ አንዳንድ ሰዎች በስተቀር በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን እንዳላገኘም ነግሮናል።

በዚህ ፊልም ሥነ-ስርዓት ላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት በኩል ደንብ ልብሳቸዉን እንደለበሱ ፊልም ለማየት መምጣታቸዉንና ስለፊልሙ ቃለ ምልልስ እንደነበር ማንተጋፍቶት ተናግሮአል። ማንተጋፍቶት ቡርኪናዎች ላይ ያስተዋለዉ አንድ ነገር አለ፤ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ይወዳሉ። ሙሉ መሰናዶዉን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

 

 

Audios and videos on the topic