የፓሪስ ሁለት ጥቃት ፈፃሚዎች | ዓለም | DW | 15.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የፓሪስ ሁለት ጥቃት ፈፃሚዎች

በፓሪሱ ጥቃት ከሞቱት አሸባሪዎች ሁለቱ የቤልጄም ነዋሪ የነበሩ ፈረንሳዊያን መሆናቸው መረጋገጡን የቤልጄም አቃቢ ህግ ዛሬ ይፋ አደረገ። ሁለቱ ወንዶች ነዋሪነታቸው ብራስልስ ከተማ ነበር፤ እንዲሁም ለፓሪሱ ጥቃት ከዋሉት ሁለቱ ተሽከርካሪዎች የቤልጄም የኪራይ መኪናዎች እንደነበሩ ተገልጿል።

በሌላ ዜና ቤልጄም መዲና ብራስልስ ውስጥ ሞለንቤል በተባለው አካባቢ አምስት በሽብር ጥቃት የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ። የከተማዋ ከንቲባ ፍራንሶኢሰ ሼፕማንስ ምናልባትም ተጠርጣሪዎቹ የአንድ ቡድን አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም በማለት የበለጠ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ትናንት ምሽት በሞልንቤክ አካባቢ ፖሊስ ምርመራ ካካሄደ በኋላ ፓሪስ የደረሰው ጥቃት ከቤልጄም ጋር ተያያዥ መረጃ በመገኘቱ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን፤ አቃቤ ህግ ገልፆ ነበር። በዚህም መሠረት ፓሪስ የሚገኘው የሙዚቃ አዳራሽ ባታክላን አካባቢ የተገኘው የጥቃት ፈፃሚ አንዱ መኪና ፤ የቤልጄም ታርጋ ያለው የኪራይ መኪና መሆኑ ታውቋል።

ፓሪስ ውስጥ በአሸባሪዎች የደረሰው ጥቃት በአውሮፓ የስደተኞች ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ድርድር አስነሳ። አዲሱ የፖላንድ መንግሥት ከፓሪሱ ጥቃት በኋላ ፖላንድ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ስደተኞችን በጋራ ለመከፋፈል በሚያደርጉት ጥረት እንደማትካፈል አስታወቀ። የስሎቫካይ መንግሥት በበኩሉ፤ «በፀጥታ ጉዳይ ላይ ሀገሪቱ የነበራትን ስጋት ጥቃቱ በግልፅ አመላክቷል» ብሏል። የጀርመን ምክትል መራሄ መንግሥት ዚግማር ጋብሬኤል የደረሰው ጥቃት እንዳለ ሆኖ ለስደተኞች ድጋፍ መስጠቱ እንዳይቋረጥ አሳስበዋል። የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ቶማስ ዴ ሚዢየር በበኩላቸው «ችኩል ውሳኔ እንዳይወሰን እና በስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚደረገው ድርድር እንዳይፋፋም» ገልጸዋል። ከፓሪሱ ጥቃት ፈፃሚ አንዱ የሶርያ ፓስፖርት እንዳለው እና በጥቅምት ወር ሌሮስ በተሰኘው የግሪክ ደሴት አድርጎ በስደተኝነት የገባ እና በበርካታ የአውሮፓ ሀገራት ያለፈ ሰው መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ወደ አውሮፓ የሚገቡ የስደተኞች ጉዳይ ብዙ ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ