የፓሪሱ ጥቃት፤ የሽብርና ፀረ-ሽብሩ ጦርነት | ዓለም | DW | 16.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የፓሪሱ ጥቃት፤ የሽብርና ፀረ-ሽብሩ ጦርነት

ከጥቅም 2001 ጀምሮ ድፍን ዓለም የተሳተፈበት ፀረ-ሽብር ዘመቻ ዛሬም በአስራ-አምስተኛ ዓመቱ ደካማዉን አይደለም ሐያሉንም ዓለም ከመሸበር አላዳነም።ለሠዓታት ረቃ ላይ የወረደዉ ቦምብ---የብቃላ ጥማትን ለማስታገስ ይጥቅምም ይሆናል። የአስራ-አራት ዓመቱ ዘመቻ ዉጤት በዜሮ እየተጣፋ- አሸባሪን ያጠፋል ብሎ ማሰብ ግን በርግጥ ያሳስታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:47
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:47 ደቂቃ

ፓሪስ፣ ጥቃት እና ሽብር

የኤፍራተንስን ወንዝ ሰሜናዊ ዳርቻ የተንተራሰችዉ የሶሪያዋ ጥንታዊ ከተማ አል-ራቃ በርግጥ ለምዳዋለች።ከ2013 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከአየር፤ ከምድር በሚወነጨፍ ቦምብ-ሚሳዬል እያረረች ነዉ።ዛሬም አልቀረላት።እስከ 1970ዎቹ ማብቂያ ድረስ የመከካከለኛዉ «ምሥራቅ ፓሪስ» ትባል ለነበረችዉ ለሊባኖስዋ ርዕሠ ከተማ ቤይሩትም በቦምብ ጥይት መሸበር እንግዳ አይደለም።ሐሙስ ተደገመባት።ከ1920 እስከ 1946 በነበረዉ ዘመን የሶሪያና የሊባኖስ ጥንታዊ አንድነት፤የግዛት ሥፋትና ጥበት እየተሸነሸነ የዛሬ መልክ እና ቅርፃቸዉን የተሠራባት ፓሪስ ግን ከ1945 በሕዋላ ረስታዋለች።ባለፈዉ ጥር አስደነገጣት። አርብ ደገማት። ሽብር።

ቅኝ ግዛት የአብዮት፤ አመፅ አስተሳሰብ መፍለቂያቱ፤ የዉበት-መዝናናት፤የፍቅር-ሥልጣኔ አብነቲቱ ከተማ አምና ጥር ከደረሰባት ሽብር በቅጡ አላገገመችም።ማቅ-ከሏን ሳታወልቅ ዳግም ተሸበረች።ፓሪስ።

ምግብ ቤት፤ መጠጥ ቤት፤ ሙዚቃ አዳራሽ፤ ኳስ ሜዳ አልቀረም።ቦምብ፤ ጥይት ዘነበባበቸዉ።እስከሬን ቁስለኛ ተለቀመበት።ፓሪስ የአንድ መቶ-ሃያ ዘጠኝ ዜጎችዋን ሕይወት አጣች።ከ300 መቶ በላይ ቆሰሉ።ሟች ቁስለኛዉ እንደ ሁሌዉ የአርብ ምሽት የፓሪሶች ወግ ዘና፤ለቀቅ፤ ፈንጠዝ ለማለት ያለመ ነበር።በጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት በወይዘሮ አንጌላ ሜርክል አገላለፅ በዉቢቱ ከተማ በነፃነት ሕወይትን ለማጣጠም ያሰበ ነበር።

«የምንዘክራቸዉ ሰዎች ቡና ቤት፤ምግብ ቤት፤ሙዚቃ አዳራሽ እና አዉራ መንገድ ላይ ነዉ የተገደሉት።ሕይወትን በምታዝናናዉ ከተማ የነፃ ሰዎችን ሕይወት ማጣጣም የሚሹ ነበሩ።ግን ተገደሉ።ይሕን የነፃነት ሕይወት በሚጠሉ ሰዎች (እጅ ጠፉ።)»

መጋቢት 2004 የስጳኝዋ ርዕሠ-ከተማ ማድሪድ በአሸባሪዎች ቦምብ ከተጠቃች ወዲሕ አዉሮጳ ዉስጥ አሸባሪዎች በጣሉት አደጋ በርካታ ሰዉ ሲገደል የፓሪሱ የመጀመሪያዉ ነዉ።ያኔ ማድሪድን፤ በዓመቱ ለንደንን፤ ያሸበሩት የአል-ቃኢዳ አባላት ወይም ጀሌዎች ናቸዉ ተብሎ ነበር።የዩናይትድ ስቴትስ በሸባሪዎች ከተመታች ከመስከረም 2001 ጀምሮ በአሸባሪነት ሥራ-ምግባሩ በዓለም ስሙ የናኘዉ አል-ቃኢዳ ዛሬ ብዙም አይጠራም።

ከሶማሊያ-እስከ የመን፤ ከናጄሪያ እስከ ኒዠር፤ ከማሊ እስከ አልጄሪያ ከቱኒዚያ እስከ ሊቢያ፤ ከሲና እስከ ኩዌት፤ ከአፍቃኒስታን እስከ ፓኪስታን ከኢራቅ እስከ ሶሪያ ቦምብ ከፈነዳ አንድም አል-ቃኢዳ፤ አለያም የአል-ቃኢዳ ተባባሪዎች ናቸዉ-ሲባልለት የነበረዉ ዓለም፤ ከ2013 ጀምሮ ካዲስ ሥም ጋር መለማመድ ግድ ሆኖበታል።የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት።(ISIL፤ ISIS) ወይም ዳዓሽ።

ኒዮርክና ዋሽግተን ከተሸበሩበት ከ2001 ፓሪስ ዳግም እስከተሸበረችበት እስካለፈዉ አርብ በተቆጠረዉ አስራ-አራት ዓመት የዓለም ሐያል፤ ሐብታም፤ ዘመናይ ምርጥ ጦር አሸባሪዎችን ለማጥፋት አፍቃኒስታን፤ ኢራቅ፤ ሊቢያ፤ አሁን ደግሞ ሶሪያ ዘምቷል።የሐያል ሐብታሙን ዓለም ትዕዛዝ፤ፍላጎትና ጥቅም ለማስፈፀም የቆሙት መንግሥታት ፓኪስታን፤ ሶማሊያ፤ምዕራብ አፍሪቃ ጦራቸዉን አስፍረዋል።

አስራ-አራት ዓመት ባለፈዉ፤ አብዛኛዉን ዓለም ባሳተፈዉ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች በየሐገሩ አልቀዋል።ዛሬም ዕለት-በዕለት እያለቁ ፤የተረፉት እየተሰደዱ ነዉ።መንግሥታት ፈርሰዋል።የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ትርጉም ያጣባቸዉ ሐገራት አሉ።ከ2013 ጀምሮ የዓለም አስጊ አሸባሪነቱ ጧት ማታ የሚነገርለት ISISን ለማጥፋት ሶሪያና ኢራቅ ላይ የተከፈተዉ ዘመቻ ጥሩ ዉጤት ማምጣቱን የዘመቻዉ የበላይ መሪና አስተባባሪ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ባለፈዉ ሐሙስ አስታዉቀዉ ነበር።

«(ISISL) እየተጠናከሩ ነዉ ብዬ አላምንም።እዉነቱ ምንድነዉ፤- ከመጀመሪያዉ ጀምሮ ዓላማችን መጀመሪያ ባሉበት ማቆም ወይም ማቀብ ነዉ።አቅበናቸዋል።ኢራቅ ዉስጥ ተጨማሪ ግዛት አልያዙም።ሶሪያ ዉስጥም ከቦታ ቦታ መግባትና መዉጣት ይችሉ ይሆናል። ISIL በተለመደዉ ዓይነት ዘመቻ ተጨማሪ አካባቢዎችን መቆጣጠር ግን አልቻለም።እስካሁን ማድረግ ያልተሳካልን የዕዝና የቁጥጥር መዋቅሩን ማሽመድመድ ነዉ።የዉጪ ተዋጊዎች (ቡድኑን) እንዳይቀላቀሉ በማድረጉ ረገድ የተወሰነ እመርታ አሳይተናል።የዓላማችን አንዱ አካል መሆን ያለበት በቀጥታ ከመዋጋት ይልቅ ኢራቅ ዉስጥ ይበልጥ ዉጤታማ የሆኑ የሱኒ ተዋጊዎችን መመልመል ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት መግለጫ በዓለም በሚናኝበት መሐል የአሜሪካ ሰዉ አልባ ተዋጊ ጄቶች (ድሮን) «ጂሐዲ ጆን» በሚል ቅፅል የሚጠራዉን አሜሪካዊ የአይ ሲ ስ አባል መግደላቸዉን የአሜሪካ መገናኛ ዘዴዎች ዘገቡ።አሜሪካ መራሹ ጦር ሶሪያና ኢራቅ ግዛቶችን ዉስጥ «አቅቦታል» የተባለዉ ቡድን ከኢራቅም ከሶሪያም አልፎ ቤይሩትን ያሸበረዉ የፕሬዝደንት ኦባማን መግለጫ የትላልቁ ዓለም ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች በሚቀባበሉት መሐል ነበር።

የሊባኖሱን ሺዓ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የሒዝቡላሕን አባላትና መሪዎች ለማጥፋት ባለመዉ ሁለት ተከታታይ ጥቃት 44 ሊባኖሳዊ ተገደለ።240 ቆሰለ።ፈረንሳዮች ከሶሪያ ቆርጠዉ እንደ ሐገር የሠሯት ሊባኖስ፤ ፈረንሳዮች ከፓሪስ ቀድተዉ ያስዋቧት ቤይሩት ይሕን መሠሉን ጥቃት፤ ጥፋት፤ሽብር በርግጥ ለምዳዋለች።የሐያሉ ዓለም ሐያል መገናኛ ዘዴም ከጨርፋታ ዜና ባለፍ የቤይሩትን እልቂት የሚያራግብበት ፍላጎት፤ ጥቅም፤ሐዘኔታም አልነበረዉ።በማግስቱ አርብ ፓሪስ ላይ የደረሰዉ ሽብር ግን ሐያሉን ዓለም ከዳር እስከ ዳር አነቃነቀ።ተራዉን ሰዉ በተለይ ፓሪሳዊዉን በርግጥ ድንጋጤ፤ ሥጋት፤ ሐዘንና ፍራቻ ነዉ ያሸመቃቀዉ።

«እዚሕ የመጣነዉ ሁላችንም ከጎናቸዉ መቆማችንን ለማሳየት ነዉ።»ከየመሪዎቹ የተሰማዉ መልዕክት ግን ከሐዘን፤ድንጋጤ ትብብሩ እኩል የ«እንዴት ተደፍርን» ንዴት፤ እልሕ፤ ቁጣ ከሁሉም በላይ ብቀላ ነበር።«አይን ላጠፋ-አይን----» ይላል አሉ መጣፉ።ፕሬዝደንት ፍሯንሷ ኦሎንድም ሌላ-አላሉም።

«ወገኖቼ ሆይ ትናንት ፓሪስ እና ስታደ ደ ፍራንስ አጠገብ፤ ሳ ዴኒ የደረሰዉ የጦርነት እርምጃ ነዉ።ጦርነቱን ለመጋፈጥ ሐገሪቱ ተገቢዉን እርምጃ ትወስዳለች።ፈረንሳይ፤ በመላዉ ዓለም በምታወቅበት እሴቶቻችን፤ በእምንነታችን፤ በነፃ ሐገራችን፤ በመላዉ ዓለም በምትናገረዉ ሐገራችን ላይ ዳዓሽ በተባለዉ የአሸባሪ ጦር---የጂሐዲስት ጦር የተወሰደ የጦነት እርምጃ ነዉ።»

የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥትም አንጌላ ሜርክልም መንግሥታቸዉና ሕዝባቸዉ ከፈረንሳይ ሕዝብ እና መንግሥት ጎን እንደሚቆሙ አረጋገጡ።«ይሕ በነፃነት ላይ የተፈፀመዉ ጥቃት በፓሪስ ላይ ብቻ የተፈፀመ አይደለም።በሁላችንም ላይ የደረሰ ሁላችንንም የጎዳ ጥቃት ነዉ።ሥለዚሕ ሁላችንም በጋራ አፀፋ (መልስ) መስጠት አለብን።»

ከሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እስከ ብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን፤ ከቱርኩ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻን እስከ እስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ያሉ መሪዎችም ከፈረንሳይ ጎን መቆማቸዉን አረጋግጠዋል።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ-እንዲሁ

«ይሕ በፓሪስ ላይ ብቻ የተፈፀመ ጥቃት አይደለም።በፈረንሳይ ሕዝብ ላይ ብቻ የተፈፀመ ጥቃት አይደለም።በመላዉ ሰብአዊ ፍጡር እና በምንጋራቸዉ ዓለም አቀፍ እሴቶቻችን ላይ የተቃጣ ነዉ።የፈረንሳይ መንግሥትና ሕዝብ የሚፈልጉትን ድጋፍ ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ ነን፤ በተጠንቀቅ ቆመናልም።እነዚሕን አሸባሪዎች ለፍርድ ለማቅረብ እና ሕዝባችንን የሚያድኑ አሸባሪዎችን ለማደን ከፈረንሳይና ከመላዉ ዓለም መንግሥታት ጋር ለመሥራት አስፈላጊዉን ሁሉ እናደርጋለን።»

አሉ-ተባባሉ ና የመጀመሪያዉን የብቀላ እርምጃ ዛሬ ከሶሪያዋ ስድስተኛ ትልቅ ከተማ ላይ አሳረፉ።ራቃ።ከመጋቢት 2013 ጀምሮ ISIS የሚቆጣጠራት ጥንታዊ ከተማ የአዉሮፕላን ቦምብ፤ሚሳዬል፤ የታንክ መድፍ አረር ብርቋ አይደለም።ዕለት በዕለት ያሸብራላታል።ዛሬም የፈረንሳይ ዘመናይ የጦር ጄቶች የISIS ማሰልጠኛና ማዘዢያ ጣቢያ ያሉትን አካባቢ ሲያወድሙት ዋሉ።

የደረሰዉ ጉዳት መጠን በዉል አልታወቀም።ከጥቅም 2001 ጀምሮ ድፍን ዓለም የተሳተፈበት ፀረ-ሽብር ዘመቻ ዛሬም በአስራ-አምስተኛ ዓመቱ ደካማዉን አይደለም ሐያሉንም ዓለም ከመሸበር አላዳነም።ለሠዓታት ረቃ ላይ የወረደዉ ቦምብ-ወትሮም የወደመችዉን ከተማ ይበልጥ ለማጥፋት ይጠቅም ይሆናል።የብቃላ ጥማትን ለማስታገስ ይጥቅምም ይሆናል። የአስራ-አራት ዓመቱ ዘመቻ ዉጤት በዜሮ እየተጣፋ- አሸባሪን ያጠፋል ብሎ ማሰብ ግን በርግጥ ያሳስታል።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic